በኤርትራ ከ10 ዓመት እስር በኋላ ሕይወታቸው ያለፈው ፓስተር ቀብራቸው እንዳይፈጸም ተከለከለ

ከዓመታት እስር በኋላ ሕይወታቸው ያለፈ ወንጌላዊ የቀብር ሥነ-ስርዓታቸው እንዳይከናወን መከልከሉ ተነገረ።

በአሥመራ ሕይወታቸው ያለፈው የወንጌላውያን አማኞች ፓስተር እንዳይቀበሩ ክልከላውን ያደረጉት የኤርትራ ባለስልጣናት መሆናቸውን ለቤተሰቡ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለቢቢሲ ትግርኛ ገልጸዋል።

ከ10 ዓመታት እስር በኋላ ከቀናት በፊት ሕይወታቸው ያለፈው ፓስተር ተስፋይ ሥዩም እስከ ዛሬ ረቡዕ ሚያዚያ 11/2015 ዓ.ም. ድረስ ግብዓተ መሬታቸውን ሳይፈጸም አስክሬናቸው በሆስፒታል እንደሚገኝ ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸውን የምንጠቅሳቸው ምንጮች ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከምንጮቹ እንዳረጋገጠው ፓስተር ተስፋይ ሥዩም ከ11 ቀናት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም የቤተሰብ አባላት ቀብራቸውን ለመፈፀም የሚያስችል ፈቃድ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ማግኘት አልቻሉም።

በኢትዮጵያ የመሰረት ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ፓስተር ሚካኤል ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ፓስተር ተስፋይ በኤርትራ ከቤተክርስቲያኑ መስራቾች አንዱ እንደሆኑ እና በእምነታቸው የተነሳ ከ10 ዓመታት በላይ በእስር መቆየታቸውን ይናገራሉ።

በሁኔታው የተጨነቁት የሟች ቤተሰቦች “የደህንነት ከፍተኛ ባለስልጣናትን” ጨምሮ የተለያዩ ኃላፊዎችን ቢያነጋግሩም መፍትሄ አለማግኘታቸውንም ፓስተር ሚካኤል ተናግረዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ የማነ ገብረመስቀልን ምላሽ እንዲሰጡ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።

ፓስተር ተስፋይ አስር ዓመት በእስር ቤት ከቆዩ በኋላ በጠና በመታመማቸው የተነሳ ከሁለት ወራት በፊት ከእስር መፈታታቸውን ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ።

ፓስተር ተስፋዬ ከእስር ከተፈቱ በኋላ በሆስፒታል ህክምና ሲከታተሉ ቆየተው ሚያዝያ 1 2013 ዓ.ም ሕይወታቸው አልፏል።

ነገር ግን በሚከተሉት እምነት ምክንያት የቀብር ስነ ስርዓታቸው በትውልድ ቦታቸው አሥመራ በሃዝዝ መካነ መቃብር ለማድረግ ፍቃድ ማግኘት እንዳልቻሉ ፓስተር ሚካኤል አስረድተዋል።

በ60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት ፓስተር ተስፋዬ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነበሩ።

በኤርትራ ውስጥ በመንግሥት እውቅና የተሰጣቸው ሃይማኖቶች ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ ካቶሊክ፣ ወንጌላዊ ሉተራን እና ሱኒ እስልምና ብቻ ሲሆኑ የሌላ እምነት ተከታዮች እውቅና አይሰጣቸውም።

የሌላ የእምነት ተከታዮች በእምነታቸው ምክንያት ለእስር ለስደትና እንደሚዳረጉ ይነገራል።

በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ በከረን ከተማ በድብቅ በጋራ ለማምለክ ወደ 30 የሚጠጉ ወንጌላውያን አማኞች ከተሰባሰቡ በኋላ መታሰራቸው ተዘግቦ ነበር።

በወቅቱ ከታሰሩት መካከል ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ተማሪዎች እንደሚገኙበት ተገልጿል።

ኤርትራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ብትሆንም የሰብአዊ መብቶችን እና የእምነት ነፃነትን በመጣስ ትከሰሳለች።

በኤርትራ ጉዳይ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ልዩ ራፖርተር ሞሃመድ አብዱልሰላም ባቢከር ከወራት በፊት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባቀረቡት ሪፖርት በኤርትራ ያለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ እየከፋ መምጣቱን ገልጸው ነበር።

የኤርትራ ባለስልጣናት የመብት ጥሰት ውንጀላውን “ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ነው” ሲሉ የሚተቹ ሲሀን እውቅና ከተሰጣቸው ሃይማኖቶች ውጪ ያሉ እምነቶች የምዕራባውያን አጀንዳ ማስፈጸሚያ ናቸው ይላሉ።