ስድስት የአማራ ክልል ከተሞች ከታጣቂዎች ነጻ መሆናቸው ተነገረ፣ የሠዓት እላፊ ገደብ ተጣለ

ስድስት የአማራ ክልል ከተሞችን ከታጣቂዎች ነጻ የማድረጉ ተግባር እየተጠናቀቀ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በከተሞቹ ላይ ሠዓት እላፊ ገደብ መጣሉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አስታወቀ።

በባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ላሊበላ፣ ጎንደር እና ሸዋ ሮቢት የነበሩ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተግባሩን ገምግሞ ማስታወቁ ተዘግቧል።

የዕዙ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተግባር በእነዚህ ስድስት ከተሞች አካባቢ የተሰባሰበውን “ለዘረፋ እና ጥፋት የተሰማራ” የተባለውን እና በዚህ መግለጫ ስሙ ያልተጠቀሰውን ታጣቂ ቡድን በመምታት እንዲሁም ከተሞቹን ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ እንደነበርም ተገልጿል።

ከተሞቹ በዋነኝነት የተመረጡት በርካታ ሕዝብ የሚኖርባቸው፣ ከፍተኛ የንግድ እና የቱሪስት እንቅስቃሴ ያለባቸው፣ የፖለቲካ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ማዕከላት በመሆናቸው እንደሆነ ተጠቁሟል።

በስድስቱ ከተሞች ዙሪያ ተሰማርተው ነበር የተባሉት እና ዕዙ “የጥፋት ቡድን” ብሎ የጠራቸው ታጣቂዎች መሳሪያቸውን አስረክበው እጃቸውን እንዲሰጡ ዕድል ተሰጥቷቸው ነበር ተብሏል።

ሆኖም ቡድኑ ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ ባለመሆኑ “እርምጃ ተወስዶበታል፣ የሕግ የበላይነትም እንዲከበር ተደርጓል” ተብሏል።

በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ለቀናት በተካሄደው ግጭት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና መጎዳታቸውን ቢቢሲ ከጎንደር እና ከባሕር ዳር የሕክምና ተቋማት ባለሙያዎች ሰምቷል።

በጎንደር ከተማ እና ዙሪያዋ ባለፉት ቀናት በነበረው ግጭት አብዛኞቹ ሰላማዊ የሆኑ ወደ 20 የሚደርሱ ሰዎች እንደሞቱ እና ከ200 በላይ ሰዎችም ቆስለው ወደ ጎንደር ሆስፒታል መምጣታቸውን የሆስፒታል ምንጮች ገልጸዋል።

በባሕር ዳርም በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና የ5 ወር ህጻንን ጨምሮ አረጋውያን እንዲሁም ወጣቶች ጉዳት ደርሶባቸው እንደመጡ የፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያዎች ለቢበሲ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት ከተሞቹ ከታጣቂው ስጋት ነጻ መሆናቸውን የጠቆመው የአስቸኳይ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ መግለጫ፣ የመከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ ሕግ አስከባሪ አባላት “በየስርቻው የተራረፈውን በማጽዳት ላይ ናቸው” ተብሏል።

“ሽንፈት እንደተከናነበ” የተገለጸው ታጣቂ ቡድን በአንዳንድ አካባቢዎች ቅርስ ወዳለባቸው ስፍራዎች እና የእምነት ተቋማት በመግባት ለመደበቅ እየሞከረም እንደሆነም ገልጿል።

ሆኖም “የመከላከያ ሠራዊቱ እና የክልሉ ሕግ አስከባሪ አካላት ሕግ፣ ሥርዓት እና ሞራልን ባከበረ መንገድ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛል” ብሏል መግለጫው።

መምሪያ ዕዙ በቀጣይም የመጨረሻውን “የማጽዳት እና የመልቀም ተግባር በማከናወን ከተሞቹ በአጭር ጊዜ ወደተሟላ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ” ይደረጋል ብሏል።

በዚህም ማኅበረሰቡ መረጃ በመስጠት እና በሌሎች ተግባራትም ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅትም ከተሞቹን “ከዘራፊ የጥፋት ቡድኑ” የማጽዳት ተግባር እየተጠናቀቀ በመሆኑ ከነሐሴ 4/2015 ዓ.ም. ጀምሮ አንዳንድ አገልግሎቶች እንዲመለሱ እንደሚደረግም አመልክቷል።

በዚህም መሠረት በእነዚህ ስድስት ከተሞች ተቋርጠው የነበሩ መደበኛ የአየር በረራዎች ሐሙስ ነሐሴ 4/ 2015 ዓ.ም ይጀምራል ብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች አቋርጦት የነበረውን በረራ ከነገ ሐሙስ ነሐሴ 04/2015 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚቀጥል ቀደም ሲል አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ተከተታይ ቀናት፤ ወደ ኮምቦልቻ፣ ጎንደር፣ ላሊበላ እና ባሕር ዳር የሚደረጉ በረራዎችን መሰረዙን ማክሰኞ ዕለት ማስታወቁ ይታወሳል።

በተጨማሪም ከባጃጅ እና ከሞተር ሳይክል በስተቀር ሁሉም ዓይነት የከተማ የትራንስፖርት አገልግሎቶች የቀደመ አገልግሎታቸውን መስጠት ይጀምራሉ። እንዲሁም የመንግሥት፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ የንግድ፣ የጤና፣ የፋይናንስ የመሳሳሉ ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግም መግለጫው አስፍሯል።

ባለፈው ሚያዝያ ወር የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎች ፈርሰው ወደ ተለያዩ የፀጥታ እና የመከላከያ መዋቅሮች እንዲገቡ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል የተከሰተው ተቃውሞ እየተጠናከረ ሄዶ፣ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭቶች እና የተኩስ ልውውጦች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

ከሰሞኑም እነዚህ ግጭቶች ተባብሰው ከአንድ ሳምንት በላይ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሲካሄድ በቆየው ግጭት እና ፍጥጫ የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት ተስተጓጉሏል፣ የኢንትርኔት አገልግሎት ተቋርጧል፣ አንዳንድ አካባቢዎችም በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ተገልጿል።

ኢሰመኮ በክልሉ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር እየተባባሰ መምጣቱን እና ከሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮም ሁኔታዎች እየተባባሱና በርካታ የክልሉ አካባቢዎች ውስጥ በግጭት ውስጥ መሆናቸውንም አስፍሯል።

በአንዳንድ አካባቢዎችም በሲቪል ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን እና የሰላማዊ ሰዎችና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም የትራንስፖርት እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችም መቋረጣቸውን አስፍሯል።

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሲደረጉ የነበሩ ግጭቶች ተባብሰው መቀጠላቸውን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል።

አርብ ሐምሌ 28/ 2015 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝም ከሰሞኑ በክልሉ ሊተገበሩ ይገባቸዋል ያላቸውን ትዕዛዞችና ክልከላዎችም ጠቅሷል።

በዚህም መሠረት፦

  • በባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሸዋ ሮቢት እና ላሊበላ የሕዝብ የአገልግሎት ሰጪ፣ የመንግሥት፣ የማኅበረሰብ እና የንግድ ተቋማት ከነሐሴ 4/2015 ዓ.ም ጀምሮ ክፍት እንዲሆኑ ትዕዛዝ ተላልፏል።
  • በስድስቱ ከተሞች እስከ ነሐሴ 17/2015 ዓ.ም. የሚቆይ የሠዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል፡፡ በዚህም መሠረት የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ከሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች እና የፀጥታ አስከባሪዎች ውጪ ለማንኛውም ሰው እና ተሽከርካሪ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ መንቀሰሳቀስ ተከልክሏል።
  • ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ፈቃድ ውጪ በአማራ ክልል ከተሞች የአደባባይ ስብሰባ፣ ሰልፍ እና መሰል እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ተከልክሏል። እንዲሁም በማንኛውም መልኩ የሕዝብ እንቅስቃሴን የሚያስተጓጉል እና የትራንስፖርት አገልግሎትን የሚያሰናክል ድርጊት እንዲሁ መከልከሉ ሰፍሯል።
  • በክልሉ ውስጥ ለፀጥታ ሥራ ከሚንቀሳቀሱ የሕግ አስከባሪዎች እና ከእነዚህ አካላት ፈቃድ ውጭ የጦር መሣሪያ ይዞ መዘዋወር የተከከለለ እንደሆነም ተጠቅሷል።
  • በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽፋን ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ትዕዛዝ ውጪ ወቅታዊ ሁኔታን ሰበብ በማድረግ ግለሰቦችን ከመደበኛው ሕግ አግባብ ውጪ ማሰር እና ማቆየት፣ የንግድ ቤቶችን ማሸግ እና መሰል እርምጃዎችን መውሰድም መከልከሉንም አስፍሯል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎም የጠቅላይ መምሪያ ዕዙ እስካሁን 14 ተጠርጣሪዎችን በአዲስ አበባ ከተማ ቁጥጥር ስር ማዋሉን ቢገልጽም ማንነታቸው አልጠቀሰም።

በአዲስ አበባ በርካታ ሰዎች መታሰራቸው የተዘገበ ሲሆን የፌደራል እና የክልል ምክር ቤት አባላት እና የአልፋ ሚዲያ መሥራች ጋዜጠኛ በቃል አላምረው ከታሰሩት መካከል ይገኙበታል።

ባለፈው አርብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ በፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ተይዘው መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ ላይ ውሳኔ ለመስጠት፣ በእረፍት ላይ የሚገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ እንደሚሰበሰቡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።