በሕንድ የተከሰከሰው አውሮፕላን ተጎጂዎች ቤተሰቦች በቦይንግ እና ሀኒዌል በተባለ አምራች ላይ ክስ መሠረቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰኔ ላይ በተከሰከሰው የኤር ኢንዲያ አውሮፕላን ሕይወታቸው ያለፈ አራት ተሳፋሪዎች ቤተሰቦች፤ የአሜሪካውን አምራች ቦይንግ እና የአውሮፕላን ክፍሎችን የሚሠራውን ሀኒዌል የተሰኘ ኩባንያን በቸልተኝነት በመወንጀል ክስ መሠረቱ።
ማክሰኞ ዕለት የተከፈተው እና ቢቢሲ የተመለከተው የክስ መዝገብ፤ አደጋው የተከሰተው ብልሽት ባለበት የነዳጅ ታንክ መቀየሪያ ምክንያት እንደሆነ ያትታል። ኩባንያዎቹም የሚያመርቱት የአውሮፕላን ንድፍ ይህ ስጋት እንዳለበት እያወቁ "ምንም" እርምጃ አልወሰዱም በማለት ከስሰዋል።
ወደ ለንደን ጋትዊክ ለመብረር ተሳፋሪዎችን ጭኖ የተነሳው ቦይንግ 787 አውሮፕላን፤ ከሕንድ አህመዳባድ ከተማ በተነሳ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተከስክሶ 260 ሰዎች ሞተዋል።
የአደጋውን ምክንያት ለማጣራት የተደረገ ምርመራ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት፤ አውሮፕላኑ ከመሬት ከተነሳ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ሞተሩ የሚሄደው ነዳጅ ተቋርጦ እንደነበረ አሳይቷል። ይህንን ተከትሎም ስለ አደጋው የሚደረገው ምርመራ ነዳጅ መቀየሪያን የተመለከተ እንዲሆን ተደርጓል።
የአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም የቦይንግ አውሮፕላኖች የነዳጅ ቁጥጥር መቀየሪያዎች ደኅነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ገልጿል።
ቢቢሲ ክሱን በተመለከተ ከቦይንግ እና ሀኒዌል ምላሽ ለማግኘት ጠይቋል።
አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ጉዳዩን በተመለከተ አስተያየት አልሰጠም። ይልቁንም የሕንድ የአቪዬሽን አደጋ ምርመራ ቢሮ ወዳወጣው የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ሪፖርት ጠቁሟል።
በአደጋው ተጎጂዎች ቤተሰቦች የተከፈተው ክስ፤ ሁሉቱም ኩባንያዎች 787 ድሪምላይነር አውሮፕላንን እንዲሁም ክፍሎቹን ማምረታቸው እና መሸጣቸውን በመጥቀስ፤ አውሮፕላኑ ስላለበት የመከስከስ አደጋ ስጋት ያውቁ ነበር በማለት ይወነጅላል።
የአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን ባለሥልጣን በአውሮፓውያኑ 2018 በሰጠው ምክረ ሀሳብ የአውሮፕላኑ ተጠቃሚዎች የነዳጅ መቀየሪያዎቹ መቆለፊያ ሥርዓት በድንገት ተንቀሳቅሰው የነዳጅን አቅርቦትን የማያቋርጡ መሆኑን እንዲያረጋግጡ ማሳሰቡንም በክስ መዝገባቸው ላይ ጠቅሰዋል።
በኤር ኢንዲያው በረራ ቁጥር 171 ወቅት፤ የነዳጅ መቀየሪያው አቀማመጠጥ "ተንቀሳቀስ" ከሚል "አቋርጥ" ወደሚል ተቀይሯል። ይህም የአውሮፕላኑን ሞተር ጉልበት በመቀነስ እየበረረ እንዳይቆይ እንዳደረገው የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ሪፖርቱ አሳይቷል።
ከሳሽ ቤተሰቦች፤ "የነዳጅ አቅርቦት ሳይታወቅ የተቋረጠው እና አውሮፕላኑን ለመንቀሳቀስ የሚያስፈልገውን ጉልበት ሙሉ በሙሉ ያጣው" በንድፉ ላይ ባለ ጉድለት" ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።
"ሀኒዌል እና ቦይንግ ይንን አይቀሬ አደጋን ለመከላከል ምን አደረጉ? ምንም" ሲሉም ኩባንያዎቹን ከስሰዋል።
ኩባንያዎቹ፤ መቀየሪያዎቹ ምርመራ እና ጥገና እንደሚያስፈልጋቸው ለአየር መንገዶች ማስጠንቀቂያ አለመስጠታቸውን እንዲሁም ደንበኞቻቸው ብልሽት ያለባቸውን የአውሮፕላን ክፍሎች በአዲሱ እንዲተኩ መለዋወጫ አለማቅረባቸውንም ክሱ ላይ ገልጸዋል።
በቴክሳስ በሚገኝ ላኒየር የተባለ የጥብቅና ድርጅት የተወከሉት ቤተሰቦች፤ ቦይንግ እና ሀኒዌል መቀየሪያዎቹ እንዲመረመሩ እንኳ በቅጡ የማያሳስብ አነስተኛ ምክር በመስጠት ብቻ "እጃቸውን አጣጥፈው ተቀምጠዋል" ብለዋል።
በሰኔ ወር የደረሰው አደጋው ሙሉ ዝርዝር ሪፖርት በቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት በ2026 እንደሚወጣ ይጠበቃል።
በዚህ አደጋ 229 ተሳፋሪዎች፣ 12 የበረራ ሠራተኞች እና መሬት ላይ የነበሩ 19 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።














