የመንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የመጀመሪያው ዙር ንግግር ያለ ስምምነት ተጠናቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Emerald Resort and Spa
በኦሮሚያ ክልል ለዓመታት የዘለቀውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በፌደራሉ መንግሥትና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ሲካሄድ የቆየው የመጀመሪያ ዙር ንግግር ያለስምምነት ተጠናቀቀ።
ካለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ ለዘጠኝ ቀናት ሲካሄድ የቆየው ንግግር በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ ሁለቱም ወገኖች ገልጸዋል።
በሰሜናዊ ምሥራቅ ዛንዚባር በምትገኘው ሙዩኒ የባሕር ዳርቻ ላይ በሚገኘው ኤምራልድ ሪዞርት እና ስፓ ሲካሄድ የነበረው ውይይት ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 25/2015 ዓ.ም. መጠናቀቁን ተከትሎ ነው የፌደራሉ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በተናጠል ባወጡት መግለጫ ያስታወቁት።
ሁለቱም አካላት በምን አይነት ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ ባይገልጹም፣ የመጀመሪያ መሆኑ የተነገረው ይህ ውይይት በአመዛኙ ገንቢ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቁልፍ በሆኑ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መደረስ አልተቻለም ያለ ሲሆን፣ መንግሥት በበኩሉ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ አልተቻለም ብሏል።
ኬንያና ኖርዌይ በአሸማጋይነት በተሰየሙበት በዚህ የመጀመሪያ ውይይት የተነሱ ጉዳዮች ዝርዝር ባይጠቀሱም፣ ግጭቱን በዘላቂነት እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ ስለመሆኑ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ለግጭቱ ፖለቲካዊ እልባት ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት ገልጿል።
መንግሥት በበኩሉ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እና እስካሁን ሲከተለው በነበሩ መሠረታዊ መርሖች አማካይነት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግሥት የጸና አቋም አለውም ብሏል።
በመንግሥት እና በአማጺው መካከል በቀጣይ የሚካሄደው ንግግር የት እና መቼ ሊሆን እንደሚችል አስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
የሁለቱን አካላት ስድስት-ስድስት ልዑካን እና አሸማጋዮችን የያዘው ይህ ውይይት ማክሰኞ ሚያዝያ 17/ 2015 ዓ.ም. በታንዛኒያ ራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ዛንዚባር ተጀምሮ በሳምንቱ መጨረሻ ይጠናቀቃል የሚል ዕቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን ለተጨማሪ ቀናት ተራዝሞ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።
ይህንን ለሳምንት ያህል የዘለቀውን የመጀመሪያውን ውይይት ኬንያና ኖርዌይ በዋነኝነት የአሸማጋይነት ሚና መጫወታቸውንም ቢቢሲ ለውይይቱ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ሰምቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥትን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዎን ጤሞቴዎስ ተደራዳሪ ሆነው መቅረባቸውንም ቢቢሲ ከምንጮቹ መረጃ አግኝቷል።
ሁለቱ ልዑካን በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተዛምቶ ለበርካቶች እልቂት የሆነውን ጦርነት እልባት ለማግኘት የፌደራሉን መንግሥት ወክለው ከህወሓት ጋር የተደራደሩት ልዑካን አባል መሆናቸው ይታወሳል።
በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኩል ደግሞ የታሪክ ምሁሩና በጆርጂያ ስቴት ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን፣ከኦነግ መስራቾች አንዱና ለበርካታ አመታት አመራር የነበሩት ጣሃ አብዲ እንዲሁም የጦሩ አዛዥ ዋና አማካሪ የሆኑት ጂሬኛ ጉደታ ይገኙበታል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታንዛኒያ ውስጥ ለቀናት ሲካሄድ የቆየውን ንግግር አድንቋል።
አክሎም በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደውን ግጭት ለማስቆም ሁለቱም ወገኖች ለሁሉም ተቀባይነት ያለው ስምምነት ላይ ለመድረስ “በቅን ልቦና” እንዲደራደሩ አሜሪካ ታበረታታለች ብሏል።












