ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"እግራቸውን በጥይት በሏቸው" ፕሬዚዳንት ሩቶ ፖሊስ ሁከትን እንዲቀለብስ ያሳለፉት ትዕዛዝ
ወጣቶች ሥልጣን እንዲለቁ በሕዝባዊ ተቃውሞ የተነሱባቸው የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ በንግድ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ተቃዋሚዎችን ፖሊሶች "እግራቸውን በጥይት እንዲመቱ" ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ፕሬዚዳንቱ እነዚህ ተቃዋሚዎች እንዳይገደሉ ነገር ግን መሰናከላቸውን አረጋግጡ ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በኬንያ ሰኞ፣ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም. በተካሄደው ፀረ-መንግሥት ተቃውሞ 31 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል።
ተቋማቱ ፖሊስ ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅሟል ሲሉ ከሰዋል።
"የሌላ ሰው የንግድ ተቋምን ወይም ንብረት ሲያቃጥል የተያዘ ማንኛውም ሰው ፖሊስ እግሩን በጥይት መትቶ ሆስፒታል እንዲያስገባው እና ከዚያም ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት። አትግደሏቸው፤ ነገር ግን መሰናከላቸውን አረጋግጡ" ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ለፀጥታ ኃይሎቻቸው አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የኬንያው መሪ ለፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ለተቃውሞዎች ድጋፍ እንዳያደርጉ፤ ሁከት የተሞላባቸው ተቃውሞዎች እና "ሕገ ወጥ" መንገዶችን በኃይል ከሥልጣን ለማንሳት እንዳይጠቀሙበት አስጠንቅቀዋል።
ናይሮቢን ጨምሮ በታላላቅ ከተሞች በተደረገው ሕዝባዊ ተቃውሞ ከተገደሉት 31 ሰዎች በተጨማሪ ከ100 በላይ ኬንያውያን ቆስለዋል፤ እንዲሁም 532 ደግሞ ለእስር መዳረጋቸውን የኬንያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገልጿል።
የኬንያ ፖሊስ ደግሞ የሟቾችን ቁጥር 11 ነው ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እነዚህ ግድያዎች በጣም እንዳሳሰቡት ገልጾ፤ የኬንያ ፖሊስ በተቃዋሚዎች ላይ "ገዳይ መሳሪያዎችን ተጠቅሟል" ሲል ትችት አቅርቧል።
ሆኖም ፕሬዚዳንት ሩቶ ረቡዕ ዕለት ባደረጉት ንግግር የፀጥታ ኃይሎቻቸውን እርምጃ ተከላክለው በእነሱ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በአገሪቱ ላይ የተላለፈ "የጦር አዋጅ ነው" ሲሉ ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።
"ኬንያ በዛቻ፣ በሽብር ወይም በሁከት አትመራም። እኔ እያለሁ ይሄ አይሆንም" ሲሉ አጽንኦት የሰጡት ፕሬዚዳንቱ፣ ከተቃውሞው ጀርባ አሉ ባሏቸው አካላት ላይ "የጠነከረ " እርምጃ እወስዳለሁ ሲሉ ዝተዋል።
ማንኛውም የመንግሥት ለውጥ የሚመጣው በምርጫ እንጂ በተቃውሞ አይደለም ያሉት ሩቶ፤ ተፎካካካሪዎቻቸውንም በመጪው፣ የአውሮፓውያኑ 2027 የሚደረገውን አገራዊ ምርጫ እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
"ይህች አገር ትዕግስት ባጡ እና ኢ-ሕገ መንግሥታዊ መንገዶችን በመጠቀም የመንግሥት ለውጥ በሚፈልጉ ጥቂት ሰዎች ምክንያት አትፈርስም። በጭራሽ አይደረግም" ብለዋል ሩቶ።
የመንግሥት ቃል አቀባይ ገብርኤል ሙቱማ ፖሊስ ከመጠን ያለፈ ኃይል የተጠቀመባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን እና አንዳንድ ፖሊሶችም ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሆኖም ሩቶ ተቃዋሚዎች እግራቸው በጥይት እንዲመታ ያስተላለፉት መልዕክት "በአሁኑ ወቅት ፖሊስ ጣቢያዎችን፣ ንብረቶችን የሚያቃጥሉ አልፎ ተርፎም በፖሊስ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎች ከመኖራቸው አንጻር" በተለየ ሁኔታ ሊታይ ይገባል ብለዋል።
በአንድ ወቅት የሩቶ አጋር የነበሩት የኬንያ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪጋቲ ጋቻጉዋ ተቃዋሚዎች ሩቶን ከሥልጣን ለመገርሰሰስ አቅደዋል መባላቸውን አስተባብለዋል።
"ማንም ቢሆን ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ከሥልጣን ሊያነሳህ አይፈልግም። በመጪው ምርጫ ልንፎካከርህ እንፈልጋለን። ስለዚህ ተረጋጋ" ብለዋል ከሦስት ዓመታት በፊት ከሩቶ ጋር አጋር ሆነው በምርጫ የተወዳደሩት እና በኋላም መጣላታቸውን ተከትሎ ከሥልጣን እንዲወርዱ የተደረጉት ጋቻጉዋ።
ባለፈው ወር ጦማሪው አልበርት ኦጃዋንግ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለ ሕይወቱ ማለፉ በርካቶች ወደ አደባባይ ተቃውሞ እንዲመለሱ አድርጓቸዋል።
ኬንያውያን የፋይናንስ ሕግ ረቂቅ መነሻ በማድረግ የአገሪቱን ፓርላማ ጭምር ጥሶ የገባውን ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ አንደኛ ዓመት በቅርቡ ዘክረዋል።
የአገሪቱን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ባሸበረው ባለፈው ዓመት በተካሄደው ሕዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል ከ60 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ሥራ አጥነት፣ የዋጋ ግሽበት እና ዘርፈ ብዙ የሆኑ የምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች ለወጣቶቹ ቁጣ መንስዔ ናቸው።
ሩቶ በአገሪቱ የሰፈነው የወጣቶች ሥራ አጥነት የአገሪቱ ቀውስ እንደሆነ ቢያምኑም፤ ነገር ግን እሳቸው ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸውም በፊት የነበረ ነው ብለዋል።
ሆኖም የእሳቸው አስተዳደር ለችግሩ እልባት ለመስጠት እርምጃዎችን በመውሰድ የመጀመሪያው እንደሆነ ነው ሩቶ የተናገሩት።
የ58 ዓመቱ መሪ ከቀደምት መሪዎች ጋር ሲነጻጸር አስተዳደራቸው ላይ የበለጠ ትችቶች እና ተቃውሞዎችን ከኬንያውን ዘንድ ለምን ይሰማል ሲሉ ጠይቀዋል።
"በእኔ አስተዳደር ወቅት ይህንን ሁሉ ሁከት መፍጠር ለምን አስፈለገ?" ሲሉ የጠየቁት ሩቶ የብሔር ፖለቲካም ላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
"የፈለጋችሁትን ስም ልትሰጡኝ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን በኬንያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን አደርጋለሁ" ብለዋል።
ሰኞ ዕለት የተጠራው ሕዝባዊ ተቃውሞ "ሳባ ሳባ" የተሰኘው በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ለመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ በአገሪቱ የተደረገውን ትግል ለማስታወስ ቢሆንም ግጭቶች አገርሽተው የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈ ሆኗል።
ተቃዋሚዎች "ሩቶ ሥልጣን መልቀቅ አለበት" አንዲሁም "አንድ የሥልጣን ዘመን ብቻ" በሚሉ መፈክሮች፤ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከኃላፊነት እንዲነሱ ጠይቀዋል።
የኬንያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማክሰኞ፣ ሐምሌ 1/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ "በጣም አሳሳቢ ነው" ብሏል።
"የኬንያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን አጥብቆ ያወግዛል፤ በሁሉም ተሳታፊ አካላት በፖሊስ፣ በሲቪሎች እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ተጠያቂነት እንዲመጣ አሳስቧል።
ኮሚሽኑ ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች በመንግሥት እና በግል ንብረቶች ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋ እና ውድመት መድረሱንም መዝግቧል።
ከተገደሉት መካከል ከናይሮቢ ወጣ ብላ በምትገኘው ኪያምቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተባራሪ ጥይት የተገደለች የ12 ዓመት ታዳጊ እንደምትገኝበት የኬንያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
"በናይሮቢ እና በሌሎች አካካቢዎች ከ15 ተቃዋሚዎች በላይ ተገድለው እንዲሁም በርካቶች የቆሰሉበት ሁኔታ ሁለት ሳምንት እንኳን ሳይሞላው ይህ መከሰቱ በጣም አሳሳቢ ነው" ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ ተናግረዋል።
ቃል አቀባይዋ በነዚህ ተቃውሞዎች ላይ ጥይቶች፣ የጎማ ጥይቶች፣ አስለቃሽ ጭስ እና የመበተኛ ውሃ ጥቅም ላይ ውሏል ብለዋል።
ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ ሁለት ሆስፒታሎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
ግለሰቦቹ ተቋማቱን ሰብረው በመግባት የሕክምና መሳሪያዎችን መዝረፋቸውን እንዲሁም ሠራተኞችን ማዋከባቸው ተነግሯል።
የሃይማኖት እና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች የተፈጸሙት ግድያዎች፣ የንብረት መውደመቶች እና የዘፈቀደ እስሮች በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቀዋል።
ማክሰኞ ዕለት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የእነሱ ጠንካራ ይዞታዎች በሚባሉ ስፍራዎች ላይ መንግሥት ምልክት በሌላቸው የፖሊስ ተሸከርካሪዎች የታጠቁ ወሮበሎችን በማጓጓዝ አሰማርቷል ሲሉ ከሰዋል።
በቅርቡ በተካሄዱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ሰርገው የገቡ "ተቀጣሪ ወሮበሎች" ዝርፊያዎችን እንዲሁም ተቃዋሚዎች ላይ ጥቃቶች ፈጽመዋል የሚሉ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
የሲቪል ማኅበራት በእነዚህ ወሮበሎች እና በፖሊስ መካከል ትብብር እንዳለ ክስ የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ፖሊስ የቀረበበትን ክስ በጥብቅ አስተባብሏል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ከፕሬዚዳንት ሩቶ አስተዳደር ጋር ግንኙነት ያላቸው የንግድ ተቋማት በሙሉ ብሔራዊ እቀባ እንዲደረግባቸው ለሕዝቡ ጥሪ አድርገዋል።
ሩቶ መንግሥታዊ ጥቃቶችን እና የዘፈቀደ ግድያዎች በኬንያውያን ላይ እየፈጸመ ነው ሲሉ እኚሁ ፓርቲዎች ከሰዋል።
"ይህ አገዛዝ በጥላቻ የተሞላ ነው። ምክንያታዊነት የሚገባው አይደለም። ልንቃወመው ይገባል። አናርፍም፤ አናፈገፍግም፤ እጅ አንሰጥም" ሲሉ ተቃዋሚዎቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል።
የኬንያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማርታ ኩሜ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጡ ሁከት የተሞላባቸው ተቃውሞዎች የአገሪቱን ዲሞክራሲያዊ መዋቅር አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉ አሳስበዋል።