ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን የተወሰነ የጦር መሳሪያ ድጋፍ አቋረጠች
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመው ጥቃት እየተባባሰ በመጣበት በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ለኪየቭ የምትሰጠውን የተወሰነ የጦር መሳሪያ ማቆሟን ዋይት ሐውስ አስታወቀ።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ አና ኬሊ ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቁት ውሳኔው ላይ የተደረሰው የመከላከያ ሚኒስቴር አሜሪካ "ለሌሎች አገራት የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ " መገምገሙን ተከትሎ "የአሜሪካን ጥቅም ለማስቀደም ነው" ብለዋል።
ሩሲያ ዩክሬን ላይ እአአ የካቲት 2022 ሙሉ ጥቃት ከከፈተችበት ጊዜ አንስቶ አሜሪካ በአስር ቢሊዮ ዶላሮች የሚገመቱ ወታደራዊ ድጋፎችን ስትሰጥ የቆየች ሲሆን፣ የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ክምችት በጣም አነስተኛ ነው ሲል ቅሬታውን ማሰማት ጀምሮ ነበር።
የዩክሬን መንግሥት በዚህ መግለጫ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም። የአሜሪካ ባለሥልጣናት የትኞቹ መሳሪያዎች ወደ ዩክሬን እንዳይጓጓዙ እንደተደረጉ ያሉት ነገር የለም።
የሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የአየር መከላከያ ሚሳዔሎች እና አነጣጥረው ዒላማቸውን የሚመቱ ተተኳሾች ክምችታቸው ከቀነሱ መሳሪያዎች መካከል ይገኙበታል።
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ኤልብሪጅ ኮልቢ "የመከላከያ ሚኒስቴር ለዩክሬን የሚያደርገውን ወታደራዊ ዕርዳታ ለመቀጠል ለፕሬዚዳንቱ ጠንካራ አማራጮች መስጠቱን ቀጥሏል" ብለዋል።
ኮልቢ አክለውም፣ "ሚኒስቴሩ ይህንን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ አካሄዱን በጥብቅ እየፈተሸ እና እያስተካከለ ሲሆን፣ በተጨማሪም የአሜሪካ ኃይሎች ለሌሎች መከላከሎች ቅድሚያ ሰጥተው ዝግጁ የሚሆኑበትንም በማስጠበቅ ላይ ነው" ብለዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣን እርምጃው የተወሰደው የአሜሪካ ወታደራዊ መሳሪያዎች ክምችት በጣም እየቀነሱ መምጣታቸውን ተከትሎ መሆኑን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።
ባለፈው ወር አሜሪካ በሦስት የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ላይ የፈፀመችውን ጥቃት በመጥቀስ "የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ጥንካሬ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ኢራንን ጠይቁ" ብለዋል።
ይህ ውሳኔ የተላለፈው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬን አቻቸው ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጋር ባለፈው ሳምንት በኔዘርላንድስ በተካሄደው የኔቶ ጉባኤ ላይ ከተገናኙ በኋላ ነው።
በወቅቱ ትራምፕ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተጨማሪ የፀረ ሚሳዔሎችን ለዩክሬን ትሰጥ እንደሆን በቢቢሲ ለጠየቁት ሲመልሱ "አንዳንዶቹን ማቅረብ እንችል እንደሆነ የምናየው ይሆናል" ብለው ነበር።
ከዜሌንስኪ ጋር ያደረጉትን ውይይቶች በመጥቀስ ትራምፕ "አንዳንድ ጊዜ ትንሽ አለመግባባቶች ነበረን፤ ግን ያ የበለጠ ጥሩ ሊሆን አይችልም" ብለዋል።
ትራምፕ እና ዜሌንስኪ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር በትራምፕ ጽህፈት ቤት ውስጥ የተካረረ ውዝግብ ገጥመው ነበር።
ከዚያ በኋላ ትራምፕ በባይደን አስተዳደር ለዩክሬን ወታደራዊ ዕርዳታ የተፈቀደውን ማስቆማቸውን ተናግረዋል።
በማስከተልም ከዩክሬን ጋር የደኅንነት መረጃዎች መጋራታቸውንም አቁመዋል። ነገር ግን የአገራቱ ግንኙነት መሻሻላቸውን ተከትሎ እገዳዎቹ ተነስተዋል።
በሚያዝያ ወር መገባደጃ ላይ አሜሪካ እና ዩክሬን በወታደራዊ ድጋፍ ምላሽ አሜሪካ የዩክሬን የማዕድን ክምችት አውጥታ መጠቀም የሚያስችላትን ስምምነት ተፈራርመዋል።
የአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ እገዳ የመጣው ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ በቀጠለችበት ወቅት ነው።
በሳምንቱ መጨረሻ ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዩክሬን ላይ ካደረሰችው ትልቁ ነው የተባለ የአየር ላይ ጥቃት ፈጽማለች።
በዚህ ጥቃት ከ500 በላይ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ማለትም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ባሌስቲክ እና የክሩዝ ሚሳዔሎችን ተጠቅማለች።
ሞስኮ በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓውያኑ 2014 በግዴታ የወሰደቻትን ክራይሚያን ጨምሮ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ትቆጣጠራለች።