ዩናይትድ ኪንግደም የሩሲያ አልማዝ ወደ አገሯ እንዳይገባ ልታግድ ነው

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ከአንድ ዓመት በላይ በሆነው የዩክሬን ጦርነት ምክንያት ዩናይትድ ኪንግደም የሩሲያ አልማዝ ወደ ሃገሯ እንዳይገባ ዕግድ ልትጥል ነው።
መነሻቸው ከሩሲያ የሆኑ ኮፐር፣ አሉሚኒየም እና ኒኬል የተሰኙ ማዕድናት በዚህ ዓመት ይፋ በሚደረግ ዕግድ መሠረት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንዳይገቡ ይደረጋል።
ለቡድን 7 አገራት ስብሰባ ጃፓን ሂሮሺማ የሚገኙት ሩሺ ሱናክ “አመፅ የሚፈጥሩ ሽልማት ሊያገኙ አይገባም” ሲሉ ሩሲያን ሲናገሩ ተደምጠዋል።
በፈረንጆቹ 2021 የሩሲያ የአልማዝ ኢንዱስትሪ ከውጭ ገበያ 4 ቢሊዮን ዶላር እንዳገኘ ተገልጾ ነበር።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ከዚህ አልፎ ከፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸው 86 ግለሰቦች እና ኩባንያዎች ላይ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችልም ተሰምቷል።
“የተጣሉ ማዕቀቦችን ችላ ያሉ ግለሰቦችም” እርምጃ ሊወስድባቸው ይችላል ተብሏል።
ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት ከ1500 በላይ ግለሰቦችን እና ተቋማትን ዒላማ አድርጎ ከ18 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ንብረት እንዳይንቀሳቀስ አግዷል።
ባለፈው ዓመት ዩኬ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ጃፓን የሩሲያ ወርቅ ወደ አገራቸው እንዳይገባ ማገዳቸው ይታወሳል።
አገራቱ ይህን ያደረጉት ሩሲያ ለዩክሬን ጦርነት የሚሆን ገንዘብ የምታገኝበትን ምንጭ ለማድረቅ ነው።
የዩኬ መንግሥት መቀመጫ የሆነው ዳውንኒንግ ስትሪት እንዳለው 60 በመቶው የሚሆነው የፕሬዝደንት ፑቲን የጦርነት አቅም “እንዳይንቀሳቅ” ተደርጓል። ይህ በገንዘብ ሲሰላ 257 ቢሊዮን ፓውንድ ገደማ ነው።
አልፎም አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት በተመሳሳይ የሩሲያ ምርቶች ላይ ዕግድ ጥለዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ዓመት የሩሲያ አልማዝ፣ የባሕር እንስሳት እና ቮድካ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ የሚያግድ ዕቅድ ማውጣታቸው አይዘነጋም።
ሩሺ ሱናክ፤ በዓለማችን በምጣኔ ሃብት ጡንቻ ያወጡ አገራት በሚሳተፉበት የቡድን 7 ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ሂሮሺማ ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አቻዎቻቸው ወደ ሂሮሺማ ሰላም ፓርክ በማቅናት የመጀመሪያው ኒውክሌር ቦምብ የፈነዳበት ቦታን ይጎበኛሉ።
ከጉብኝቱ በኋላ ዩክሬን እና የዓለም ምጣኔ ሃብትን በተመለከተ ምክክር ያደርጋሉ።
ሩሲያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዩክሬን ውስጥ የምታካሂደውን የሚሳኤል ጥቃት አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን ዩክሬን ደግሞ በቅርቡ የሩሲያን ሚሳኤሎች መትታ መጣል ጀምራለች።
ሩሺ ሱናክ፤ እሑድ ዕለት ከሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር እንደሚመክሩም ታውቋል። ሞዲ የዩክሬን ጦርነትን በተመለከተ ለማንም ያላደላ አቋም ይዘዋል።












