በምዕራብ ሸዋ ሰርገኞችን ዒላማ ባደረገ ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች ተገደሉ

ጥቃቱ የተፈጸመበት ስልክ አምባ የገጠር ከተማ ከምዕራብ ሸዋ ዞን መቀመጫ አምቦ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል።
የምስሉ መግለጫ, ጥቃቱ የተፈጸመበት ስልክ አምባ የገጠር ከተማ ከምዕራብ ሸዋ ዞን መቀመጫ አምቦ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ሰርገኞችን ዒላማ ባደረገ ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው አስተዳደር ባለሥልጣን እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የአካባቢው ኮማንድ ፖስት ኃላፊ ጥቃቱን የፈጸሙት “ጽንፈኛ የአማራ ታጣቂዎች” ናቸው ያሉ ሲሆን፣ አንድ ነዋሪ ደግሞ ጥቃቱ በማን እና በምን ምክንያት እንደተፈጸመ ግልጽ አይደለም ብለዋል።

የኖኖ ወረዳ ኮማንድ ፖስት ኃላፊ አቶ ተሾመ ሰቦቃ ቅዳሜ ሰኔ 8/2016 ዓ.ም. ንጋት ላይ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት “ጽንፈኛ የአማራ ታጣቂዎች” ናቸው ያሏቸው ሰርገኞች የነበሩበትን ቤት ከውጪ በመቆለፍ ቤቱን በቦምብ አጋይተዋል ብለዋል።

“ሰርገኞቹ ቤት ውስጥ እያሉ በር ዘግተውባቸው ቦምብ ወረወሩባቸው። ቤት ውስጥ ከነበሩት አንድም በሕይወት የወጣ የለም። እዚያው ተቃጥለው አልቀዋል” ብለዋል።

ኃላፊው ጥቃቱን የፈጸሙት “ጽንፈኛ የአማራ ታጣቂዎች ናቸው” ከማለት ውጪ ስለታጣቂዎቹ ማንነት እና በአካባቢው የፀጥታ ኃይል ስለተወሰደ እርምጃ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ የልፈቀዱ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ደግሞ “የጥቃቱን ምክንያት ለማወቅ አዳጋች ነው። በመሬት ይገባኛል ነው ያሉ አሉ። ነገር ግን እርግጠኛ መሆን አልቻልንም” ብለዋል።

ግድያው በተከሰተበት ቦታ ቤቶች ከመቃጠላቸው በተጨማሪ ዝርፊየ የተካሂደ መሆኑን የገለጹት ነዋሪው፣ በቀጣዩ ቀን ጠዋት የአማራ ተወላጆች የበቀል ጥቃት በመፍራት ቤታቸውን ዘግተው መሄዳቸውን ገልጸዋል።

ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ ቤተሰቦቻቸው የተጎዱባቸው የአካባቢው ሰዎች “በፈጸሙት የበቀል ጥቃት በግምት ከ20 በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል” ሲሉ ነዋሪው የተከሰተውን ሁኔታ አስረድተዋል።

አንድ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ ታጣቂዎቹ ሰርግ ቤቱ ላይ ከአንድ በላይ ቦምብ ወርውረው ሙሽሮቹን እና አብረዋቸው የነበሩ ሰዎችን መግደላቸውን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከኮማንድ ፖስት ኃላፊውም ሆነ ከነዋሪ እንደሰማው በሰርግ ቤት ላይ የተነሳውን እሳት ለማጥፋት የመጡ የአካባቢው ነዋሪዎች በታጣቂዎቹ የተኩስ እሩምታ ተከፍቶባቸው በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።

የአካባቢው ነዋሪ የሟቾች ቁጥር ከ30 እስከ 50 ሊደርስ እንደሚችል ሲናገሩ፤ የወረዳው የኮማንድ ፖስት ኃላፊ አቶ ተሾመ ሰቦቃ ደግሞ በእሳት ተቃጥለው የሞቱ ሰዎችን ቁጥር መለየት አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛውን የሟቾች ቁጥር መለየት አልተቻለም ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ ስለሁኔታው ሲናገሩ ክስተቱን “በጣም ሰቅጣጭ” በማለት ገልጸው፣ በግምት 37 ወይም 39 የሚሆኑ ሰዎች እዚያው ተቃጥለው በመሞታቸው “የተቃጠሉትን የራስ ቅሎች ቆጥረን ነው የሟቾችን ቁጥር ያወቅነው” ብለዋል።

ኖኖ ወረዳ ስልክ አምባ ከተባለችው የገጠር ከተማ ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተፈጸመው ዚህ ጥቃት ሙሽሪ እና ሙሽራውን ጨምሮ የሰርጉ ታዳሚዎች የሆኑ ሰዎች በሙሉ ሕይወታቸው ማለፉን ነዋሪው ተናግረዋል።

አቶ ተሾመ “በአሁኑ ወቅት የአስክሬን ማንነትን መለየት አይደለም፣ አስክሬንን ከተቃጠለ እንጨት መለየት በጣም አስቸጋሪ ሆኖብናል” ብለዋል።

ታጣቂዎች ሰርገኞቹን ለምን ዒላማ እንዳደረጉ ግልጽ አይደለም።

በዚህ ጥቃት ሰርገኞች በነበሩበት ቤት ላይ ከደረሰው ጥቃት በተጨማሪ በስፍራው ያሉ 22 የመኖሪያ ቤቶች በእሳት እንዲያያዙ መደረጋቸውን የኮማንድ ፖስቱ ኃላፊ ተናግረዋል።

በወረዳው የተፈጸመውን ጥቃት የሚያሳዩ ናቸው የተባሉ እና ቢቢሲ ያላረጋገጣቸው ምሥሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተጋርተዋል። ምሥሎች በእሳት በወደሙ ቤቶች ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የተቃጠሉ አስክሬኖችን አሳይተዋል።

አቶ ተሾም እስካሁን ድረስ 24 ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠናል ያሉ ሲሆን፣ በሌሎች በተቃጠሉ ቤቶች ውስጥ ተቃጥለው ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ የማጣራት ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል።

እንደ ኮማንድ ፖስት ኃላፊው ከሆነ በአካባቢው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ሲፈጸም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። “ከሁለት ዓመት በፊት መቱ ሥላሴ በሚባል ቀበሌ የአማራ ጽንፈኞች በፈጸሙት ጥቃት 16 ሰዎችን በአንድ ጉድጓድ ቀብረናል” ብለዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች የመንግሥት ኃይሎች፣ የኦሮሞ እና የአማራ ታጣቂዎች ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል።

በተለይ በአራቱ የወለጋ ዞኖች እና በምዕራብ ሸዋ ዞኖች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች የአማራ ተወላጆችን፣ በሌላ በኩል የአማራ ታጣቂዎች የኦሮሞ ተወላጆችን ዒላማ አድርገው በፈጸሟቸው ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች ሕይወታውን አጥተዋል።