ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለሩሲያ በመሰለል የተጠረጠሩ ሦስት ሰዎች ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋሉ
ለሩሲያ በመሰለል የተጠረጠሩ ሦስት ሰዎች በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው ቢቢሲ ከምንጮቹ አረጋገጠ።
እነዚህ ሦስት ሰዎች የቡልጋሪያ ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ፣ ከየካቲት ወር ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ይገኛሉ ተብሏል።
ግለሰቦቹ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል አንዱ “ላልተገባ ዓላማ” ለማዋል በማሰብ ሐሰተኛ ሰነዶችን መያዝ የሚል ይገኝበታል።
ግለሰቦቹ እጅ ላይ ከተያዙ ሐሰተኛ ሰንዶች መካከል የዩናይትድ ኪንግደም፣ የቡልጋሪያ፣ የፈረንሳይ፣ የጣልያን፣ የስፔን፣ የክሮሺያ፣ የስሎቬኒያ፣ የግሪክ እና የቼክ ሪፐብሊክ ፓስፖርቶች፣ መታወቂያ ደብተሮች እና ሌሎች ሰንዶች ይገኙበታል።
ከሦስቱ ተጠርጣሪዎች አንዷ ሴት ስትሆን ሁለቱ ደግሞ ወንዶች ናቸው። ካትሪን ኢቫኖቫ 31 ዓመቷ ሲሆን ኦርሊን ሩሴቭ እና ቢዜር ድዝሃምባዞቭ የ45 እና የ41 ዓመት ጎልማሶች ናቸው።
ሦስቱም ግለሰቦች በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ለበርካታ ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠሩ የኖሩ ሲሆን፣ ሩሴቫ የተባለው ግለሰብ በሩሲያ ውስጥ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ነበር።
ሩሴቫ እአአ 2009 ላይ ወደ ዩኬ ጠቅልሎ ከገባ በኋላ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ይሠራ ነበር። በአንድ ወቅት ደግሞ የቡልጋሪያ የኢነርጂ ሚኒስቴርን የማማከር አገልግሎት ይሰጥ ነበር።
ሊንክደን ገጹ ላይ ማየት እንደሚቻለው ሩሴቫ የግንኙነት ደኅንነት ላይ የሚሰራ የግሉን ድርጅት ማቋቋም ችሏል።
ቀሪዎቹ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ደግሞ ጥንዶች እንደሆኑ የቀድሞ ጎረቤቶቻቸው ይገልጻሉ።
ቢዜር ድዝሃምባዞቭ ለአንድ ሆስፒታል አሸከርካሪ ሆኖ እንደሚሠራ የተገለጸ ሲሆን፣ ፍቅረኛው የ31 ዓመቷ ካትሪን ኢቫኖቫ ደግሞ በሊንክደን አካውንቷ ላይ እራሷን የምትገልጸው የአንድ የግል የጤና ተቋም የላብራቶሪ ባለሙያ እንደሆነች ነው።
ወደ ዩኬ ከገቡ አስርት ዓመታትን ያሳለፉት ጥንዶቹ አዲስ የቡልጋሪ ዜጎች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሲመጡ የአገሩን ባሕል እና ወግ የሚያላምድ ድርጅትን በበላይነት ይመራሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ ጥንዶች ከቡልጋሪያ ውጭ ያሉ ዜጎች በአገሪቱ በሚካሄዱ ምርጫዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ በአገሪቱ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚሽን ተቀጥረው እንደሠሩ ይፋዊ የቡልጋሪያ መንግሥት ሰነድ ያሳያል።
ለሩሲያ በመሰለል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ጥንዶች የቀድሞ ጎረቤቶች በስጦታ መልክ ጣፋጭ ምግቦችን ይሰጧቸው እንደነበረ ተናግረዋል።
ጥንዶቹ በቁጥጥር ሥር ከዋሉም በኋላ ፖሊስ በመኖሪያ ቤታቸው ለቀናት የዘለቀ ጥብቅ ብርበራ ማካሄዱን ጎረቤቶች ጨምረው ተናግረዋል።
ሦስቱ ተከሳሾች በመጪው ጥር ወር ላይ ለንደን ከሚገኝ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ለቀረቡባቸው ክሶች የጥፋተኝነት ቃላቸውን እስካሁን አልሰጡም።
የዩኬ የፀረ ሽብር ፖሊስ በተለይ ለሩሲያ በመሰለል በሚከሰሱ ተጠርጣሪዎች ላይ የሚያደርገው ምርመራ ረዥም ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ይገልጻል።
የአገሪቱ ፖሊስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዩኬ የተሰማሩ የሩሲያ ሰላዮች ቁጥር ከፍ ማለቱ አሳስቦታል።
እአአ 2018 ላይ የሩሲያ ሰላይ ሆኖ ሳለ ለዩኬ ምሥጢራዊ ሰነዶችን አሳልፏል የተባለን የቀድሞ የደኅንነት ሰው እና ሴት ልጁን የሩሲያ ሰላዮች በዩኬ የግድያ ሙከራ ፈጽመውባቸው ነበር።
የሩሲያ ሰላዮች አባት እና ልጅን ኖቪቾክ በተባለ የደም ቧንቧ ሥርዓትን በሚያጠቃ አደገኛ መርዝ ለመግደል ሙከራ አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርተዋል።
ይሁን እንጂ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላት ሴት በሽቶ ብልቃጥ ውስጥ ከነበረው መርዛም ንጥረ ነገርን በመንካቷ ሕይወቷ አልፏል።
እአአ 2006 ላይ ደግሞ አሌክሳንደር ሊትቪኔንኮ የተባለ የቀድሞ የሩሲያ ሰላይ ለንደን ውስጥ በሩሲያ ሰላይ ከተመረዘ በኋላ በጠና ታሞ ሕይወቱ አልፏል።