ቡና መቀነስ አስፈሪ ሕልም እንድናይ ያደርጋል?

ቡና ሲቀዳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንዳንዶች የሚጠጡትን ቡና መጠን ከቀነሱ በኋላ ጥርት ያለ ሕልም ማየት መጀመራቸውን ይናገራሉ።

ቡና መቀነስ ጥርስ እንዲነጣ ከማድረግ ባሻገር ሌሎችም የጤና ጥቅሞች እንዳሉት ይነገራል። በተቃራኒው ቡና መቀነስ አስፈሪ ሕልሞችን ያስከትላልም ይባላል።

ቡና የቀነሱ ሰዎች ሕልማቸው ጥርት ከማለቱ በተጨማሪ ሕልሞቻቸው አስፈሪ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

የሚጠጡትን ቡና መጠን በቀነሱ በቀናት ውስጥ የሕልማቸው ይዘት መለወጡን ነው የሚናገሩት።

ለመሆኑ የቡና መጠን የሕልም ጥናትና ይዘት ላይ ለውጥ ያመጣል?

ቡና እና እንቅልፍ

ቡና ወደ አንጎል የሚሄደውን አዴኖሲን የተባለ ንጥረ ነገር በማገድ እንድንነቃቃ ያደርጋል።

ንጥረ ነገሩ ቀኑን ሙሉ ሰውነት ውስጥ ሲከማች ይውላል። ምሽት ላይ እንቅልፋችን እንዲመጣ የሚያደርገውም ይሄው ንጥረ ነገር ነው።

እንቅልፍ ሲወስደን ንጥረ ነገሩ ከሰውነት ስለሚወጣ ጠዋት ስንነሳ እንነቃቃለን። ጠዋት ላይ ንጥረ ነገሩ እንደ አዲስ መከማቸት ይጀምራል።

ቡና ሰውነት ውስጥ ያለውን አዴኖሲን ይገታል። ስለዚህ ቡና ከጠጣን እንቅልፍ እንቅልፍ አይለንም።

ቡና ውስጥ ያለው ንጥረ ነገር ካፊን ከሰውነት ሲወጣ ግን የመተኛት ፍላጎት ይቀሰቀሳል። እንዲያውም ቡና ከመጠጣት በፊት ካለው በበለጠ የእንቅልፍ ስሜት ይጫጫናል።

ወደ ሰውነት ከሚገባው ካፊን ግማሹ ከሦስት እስከ ስድስት ሰዓት በሰውነት ውስጥ ይቆያል። ስለዚህ አዴኖሲን ላይ ጫና ማሳደሩን ይቀጥላል።

ከሰዓት ወይም አመሻሽ ላይ ቡና መጠጣት እንቅልፍ የሚከለክለውም ለዚህ ነው።

ካፊን እንቅልፍ ከመከልከል አልፎ እንቅልፍ ያዛባል፣ የምንተኛበትን ሰዓት ሊያሳጥርም ይችላል።

እንቅልፍ የተለያዩ ደረጃዎች አሉት። ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ የሚገባበት የእንቅልፍ ክፍል (non-rapid eye movement (NREM) sleep) በካፊን ምክንያት መስተጓጎል ይገጥመዋል።

ቡና ስናበዛ ወይም ከሰዓት አዘውትረን ቡና ስንጠጣ እንቅልፋችን መዛባቱ አይቀርም።

ቡና መቀነስ ጥርት ያለ ሕልም እንድናይ ያደርጋል የሚለውን በተመለከተ እምብዛም ጥናቶች አልተሠሩም።

ብዙ ጥናቶች ያሉት ካፊን እንዴት እንቅልፍን ያዛባል በሚለው ነው። ቡና እና የሕልም ይዘት ያላቸው ትስስር ላይ ጥናቶች ማግኘት ከባድ ነው።

ሆኖም ግን ካፊን እና ሕልም መካከል ስላለው ተዛምዶ የተወሰነ መረጃ አለ።

ቡና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቡና መቀነስ አስፈሪ ሕልም ያስከትላል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቡና በቀነሱ በቀናት ውስጥ ሕልማቸው ጥርት ያለና እንግዳ ይዘት ያለው እንደሆነ የሚናገሩ ቢኖሩም ይህንን የሚያረጋግጥ መረጃ የለም።

ካፊን ሲቀነስ በቀጥታ ጥርት ያለ ሕልም ባይታይም በሁለቱ መካከል አንዳች ትስስር አለ።

ካፊን ከከሰዓት ሲወሰድ እንቅልፍ ማስተጓጎሉ እሙን ነው። ስለዚህ ካፊን ስንቀንስ ሰውነታችን የሚያገኘው የእንቅልፍ መጠን ይጨምራል።

የምንተኛው እንቅልፍ ሲጨምር በጥልቀት በእንቅልፍ ውስጥ የምንቆይበት ጊዜም ይጨምራል።

በጥልቅ እንቅልፍ ወቅት ሰውነት ቢያርፍም አእምሮ ግን ሥራውን ይቀጥላል።

ጥልቅ እንቅልፍ ላይ የምንሆንበት ወቅት ሕልም የምናይበት ጊዜ ነው። ስለዚህም የጥልቅ እንቅልፍ ርዝማኔ ዘለግ ወደሚል ሕልም ይወስዳል።

በዚህ ወቅት አእምሮ ጥርት ያለ ሕልም ለመፍጠር ጊዜ ያገኛል።

ሌሊት ላይ ከእንቅልፍ የምንነቃው ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ ነው። ከጥልቅ እንቅልፍ ስንነቃ ሕልማችንን የማስታወስ ዕድላችን ይጨምራል።

ሕልማችንን የምናስታውሰው አእምሯችን ውስጥ አዲስ መረጃ ሆኖ ስለሚቀመጥ ነው።

እናም የካፊን መጠን ቀንሶ ዘለግ ላለ ጊዜ ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ስንቆይ ብዙ የማለምና ሕልማችንን የማስታወስ ዕድል ይኖረናል።

እንቅልፍና ሕልም ውስብስብ ጉዳዮች ናቸው። የሚጠጡትን ቡና የቀነሱ ሰዎች ሁሉ ድንገት ጥርት ያለ ሕልም ማየት ይጀምራሉ ማለት አይደለም። ለተወሰነ ቀን ብቻ ጥርት ያለ ሕልም ሊያዩም ይችላሉ።

ካፊን ያለው ቡና ውስጥ ብቻ አይደለም። በቸኮሌት፣ ሻይና ሌሎችም የምግብ ዓይነቶች ውስጥ ካፊን ይገኛል።

ካፊን ሰውነትን የማንቃትና አእምሮ በሰላ ሁኔታ እንዲያሰላስል የማድረግ ጠቀሜታ አለው።

ቡና የሚጠጡ ሰዎች ለድባቴ የሚጋለጡት መጠን እንደሚቀንስ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

እንደ ፓርኪንሰንስ ያሉ ከአእምሮ ሕዋሳት መሞት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱና አስተውሎትን የሚቀንሱ መድኃኒት አልባ ሕመሞችን ለመከላከልም ካፊን ሚና አለው።

ቡና ቫይታሚን ቢ እንዲሁም ሌሎችም ከጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ጋር የሚተሳሰሩ ንጥረ ነገሮችን ለሰውነት ይሰጣል።

ምሽት ላይ የሚሠሩ ሰዎች ድካምን የሚከላከሉት በቡና ነው። ጠዋት ላይ ለሚኖር ሥራ ለመነቃቃትም ቡና ይመከራል።

ቡና መቀነስ የሚፈልጉ ሰዎች እንቅልፋቸው ላይ የሚያሳድረው ጫና የሚያሳስባቸው ከሆነ መፍትሔው ቀላል ነው።

ቡና ከእንቅልፍ ስምንት ሰዓት አስቀድሞ መጠጣት እንዲሁም ከእንቅልፍ 12 ሰዓት በፊት ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና አለመውሰድን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በዚህ መንገድ የተሻለ እንቅልፍና ሕልም ይኖረናል።