ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መንግሥት ዝምታን የመረጠበት 'በፀጥታ ኃይሎች' የሚፈጸመው አፈና
"መንግሥት በሕዝቡ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በራሱ ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ጭምር ስጋትን ለመፍጠር በሚል የሚወስደው እርምጃ ሊሆን ይችላል" አደም ካሴ።
"በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ ታጣቂዎችን ይፈራል፤ በተጨማሪም ይጠብቀኛል የሚለውን መንግሥትንም ይፈራል" ያሬድ ኃይለ ማሪያም።
"ይህ ድርጊት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሥርዓት አልበኝነት መኖሩን የሚያሳይ ምልክት ነው" ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሕግ ባለሙያ።
እነዚህ አስተያየቶች እየተደጋገመ የመጣውን ዜጎችን ከሕግ ውጪ አፍኖ በኃይል የመሰወር ድርጊትን በተመለከተ የተሰነዘሩ ናቸው። ትኩረታቸውም ክስተቱ በሕዝቡ ውስጥ ስጋት የሚፈጥር እየሆነ መሄዱ ላይ ነው።
በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በታጣቂዎች የሚፈፀሙ እገታዎች የዕለት ከዕለት ክስተት ወደ መሆን እየደረሱ ነው። ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ አንጻራዊ ደኅንነት ያለባት ብትሆንም ከስጋት ግን ነጻ አይደለችም።
አዲስ አበባ ውስጥ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ የመብት ተከራካሪዎች፣ ጋዜጠኞች እና ተራ ዜጎች በማይታወቁ ኃይሎች ተይዘው ለቀናት ወይም ለሳምንታት ተሰውረው የሚቆዩበት ሁኔታ አነጋጋሪ ሆኗል።
ሰዎች የፀጥታ ኃይል ነን በሚሉ ታጣቂዎች ነገር ግን የሕግ ሥርዓትን ባልተከተለ ሁኔታ ከቤታቸው፣ ከሥራ ቦታቸው እና ከመንገድ ላይ ታፍነው መወሰዳቸው ፍርሃት እና ግራ መጋባትን ፈጥሯል።
የፖሊስ እና የመከላከያ የደንብ ልብስ ወይም ሲቪል በለበሱ ሰዎች የሚፈጸመው አስገድዶ የመሰወር ክስተት የተደጋገመ ከመሆኑ በተጨማሪ የሚመለከታቸው የፀጥታ አካላትም "የማያውቁት" መሆኑ የበለጠ አሳሳቢ ሆኗል።
ቢሆንም ግን የሚታፈኑት ሰዎች በሥራቸው እና በእንቅስቃሴኣቸው የሚታወቁ መሆናቸው ድርጊቱ በመንግሥት አካላት እንደተፈጸመ ይታመናል። ታጋቾቹም ከቀናት ወይም ከሳምንታት በኋላ ሲለቀቁ መሰወራቸው ከመንግሥት አካላት ጋር የተያያዘ መሆኑን ይናገራሉ።
ይህ እየተደጋገመ ያለ እና በፖለቲካው፣ በሲቪል ማኅበረሰብ እና በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ያሉ ሰዎችን ላይ ያነጣጠረው አፈና የሚፈጸመው ምን ለማሳካት ነው? ወደ የትስ ሊያመራ ይችላል?
ዓላማው ምንድን ነው?
'በፀጥታ ኃይሎች' ታፍነው የሚሰወሩት በአብዛኛው ጋዜጠኞች፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ትችት እና አስተያየት የሚሰነዝሩ ዜጎች ናቸው። ይህ ደግሞ የትኛውን ወገን ሊያስቆጣ እና ለእርምጃ ሊያነሳሳው እንደሚችል መገመትን አስቸጋሪ አያደርገውም።
በሕገ መንግሥታዊ እና የዓለም አቀፍ ጉዳዮች የፖለቲካ ምሁር የሆኑት አደም ካሴ (ዶ/ር) በዋነኛነት በፀጥታ ኃይሎች በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ሰዎችን እገታ የሚመስል ሁኔታ አፍኖ መያዝ "መንግሥታዊ ሕገ ወጥነት እየተስፋፋ የመምጣቱ ማሳያ ነው" ይላሉ።
ዋነኛ ዓላማው በጋዜጠኞች፣ በተቃዋሚዎች፣ በሲቪል ማኅበረሰብ አባላት፣ በአጠቃላይ ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ ፍራቻ ከመፍጠርም ያለፈ መሆኑን አደም ይናገራሉ።
"ምናልባትም በዋናነት መንግሥት ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ፍራቻን የመፍጠር ዓላማ ሊኖረው ይችላል።...የራሱ ሰዎች ሥልጣናቸው ምንም ይሁን ምን የመንግሥትን ምሥጢር ቢያወጡ ወይም ከመንግሥት ፍላጎት ቢያፈነግጡ እንዲህ ዓይነት ዕጣ እንደሚገጥማቸው ለማስፋራራት ያለመ ሊሆን ይችላል።"
የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አማካሪ የሆኑት ያሬድ ኃይለማሪያም እንደሚሉት ሰዎችን በማፈን የመሰወሩ እርምጃ ለመንግሥት ሥጋት የሆኑ ሰዎችን እና ቤተሰባቸውን በማስደንገጥ ጫና መፍጠር ሲሆን፤ የሚቀጥሉ ከሆነ የከፋ ነገር እንሚገጥማቸው መልዕክት ለማስተላለፍ ነው።
ይህ እገታ እና የመሰወር ድርጊት የሚፈጥረው ስጋት በሰለባዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎችም ሊጋባ የሚችል ነው። ስለዚህም መልዕክቱ ከታፈኑት ባሻገርም በተመሳሳይ መስክ ላይ ለሚገኙ ሌሎች ዜጎች ጭምር ከመሆኑ በተጨማሪ በሕዝቡ ውስጥም ፍርሃት እና ስጋትን የሚፈጥር ነው ይላሉ።
ከመደበኛው የሕግ ሥርዓት ውጪ ታግተው የተለቀቁ ሰዎች ስለገጠማቸው ሁኔታ በዝርዝር ለመናገር አለመፍቀዳቸው የደረሰባቸው እንግልት ውጤት ሊሆን ይችላል።
ለዚህ ዘገባ ታፍነው ጠፍተው ከቆዩ ሰዎች መካከል ቢቢሲ የተወሰኑትን ለማነጋጋር ቢሞክርም ከገጠማቸው እንግልት እና ጫና የተነሳ ለጊዜው ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል ወይም ስለዚህ ጉዳይ ከማንም ጋር ማውራት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
ምን ሊያስከትል ይችላል?
በመደበኛው አሠራር በሕግ አስከባሪዎች የሚፈለጉ ዜጎች በግልጽ እና በሚታወቅ ሁኔታ ተይዘው ሕጋዊ ሂደትን በሚጠብቅ መንገድ ተጠያቂ የሚደረጉ ቢሆንም፣ ይህ የአፈና ድርጊት ግን ከሕግ በተቃራኒ የመብት ጥሰት የሚፈጸምበት ነው።
"እንዲህ ያለውን የማፈን እና የመሰወር አካሄድ ተግባራዊ የሚሆነው፣ በመደበኛው የሕግ ሥርዓት ቢሄዱ ዜጎችን የማያስጠይቅ እና መንግሥትንም የማያስኬድ መሆኑን በሚያውቁ አምባገነኖች የሚፈጸም ነው" ይላሉ ያሬድ።
አክለውም "ወደ አፈና ሲገባ የሕግ የበላይነት አያሳስብም። ወንጀልን መቆጣጠር ያለበት አካል ወንጀልን ራሱ ሲፈጽም ሕግ ሲጥስ ለሥርዓት አልበኝነት በር ይከፈታል።"
ጥቂት የማይባሉ በሕዝብ የሚታወቁ ዜጎች ከቤታቸው ወይም ከሥራ ቦታቸው ማንነታቸውን በማያውቋቸው "የፀጥታ ኃይሎች" ተይዘው መሰወራቸው መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ ስጋት እና መፈራራትን ይፈጥራል።
አደም ካሴ ይህ ድርጊት የሚፈጥረው ፍራቻ "ሕገወጥነትን ያስፋፋል፤ ሥርዓትን ያፈርሳል፣ ለወንጀል መበራከት በር ይከፍታል፣ በሕግ ላይ ያለ መተማመንን የሚያጠፋ ይሆናል" ይላሉ።
"ይህ ክስተት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሥርዓት አልበኝነት እንዳለ የሚያሳይ ምልክት ነው" የሚሉት ደግሞ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ እና መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የሕግ ባለሙያ ናቸው።
ምንም እንኳን መንግሥት ተቃዋሚዎቹን እና ተቺዎቹን ለማስፈራራት ዜጎችን የመሰወር እርምጃን ቢመርጥም ሁኔታው ስር እየሰደደ ለራሱም ቢሆን አደገኛ ፈተናን ማስከተሉ እንዳማይቀር የሕግ ሙያተኛው ይናገራሉ።
"ይህ ሥርዓት አልበኝነት ለራሱ ለመንግሥት ሳይቀር በጣም አደገኛ አካሄድ ነው። በአጠቃላይ በአገሪቱ ላይ ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሥርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን የሚያደርግ ክስተት ነው" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አደም ካሴ በበኩላቸው እንዲህ ዓይነቱ አፈና እና መሰወር በተበራከተ ቁጥር "ሕገ ወጥነት እና የዘፈቀደ አካሄድን በማስፋፋት አደገኛ ሁኔታን የሚፈጥር ድርጊት ነው" ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሕግ እና የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ይህ እየተደጋገመ የመጣው ከሕግ ውጪ ሰዎችን የመሰወር ድርጊት ሕግ እና ሥርዓትን በማፍረስ፣ ሥርዓት አልበኝነትን ሊያስከትል እንደሚችል በአጽንኦት አስጠንቅቀዋል።
አፈናውን የሚፈጽመው ማን ነው?
"በፀጥታ ኃይሎች" ታፍነው ወዳልታወቁ ስፍራዎች የተወሰዱ ሰዎች እና ይህንን የተመለከቱ የዓይን እማኞች እንደሚሉት ከአለባበስ እና ከንግግራቸው የመንግሥት ኃይሎች መሆናቸውን ይናገራሉ።
ነገር ግን የሚፈልጉትን ሰው ለመያዝ የሚከተሉት መንገድ በአገሪቱ ሕግ ከሚፈቀደው ውጪ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የያዟቸውን ሰዎች የሚወስዱበት ቦታም በመደበኝነት የሚታወቁ እስር ቤቶች ወይም የማቆያ ስፍራዎች አይደሉም።
ይህ ደግሞ በሚያዙት ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ከባድ ሥነ ልቦናዊ ጫናን የሚያስከትል ነው።
የታፈኑት ሰዎች የት እና በማን እጅ መሆናቸውን የማያውቁ ቤተሰቦች ለመደበኛዎቹ የፀጥታ ተቋማት ለሚያቀርቡት ጥያቄ የሚሰጣቸው ምላሽ "የምናውቀው ነገር የለም" የሚል መሆኑ ደግሞ ተስፋ መቁረጥ ያነግሳል።
ያሬድ ኃይለማሪያም ከአንድ የፀጥታ ኃላፊ ጋር ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በነበራቸው ንግግር መደበኛው የፖሊስ እና የፀጥታ ኃይል ታገቱ ስለተባሉት ሰዎች ከመስማት ባሻገር የሚያውቁት ነገር እንደሌለ እንደነገሯቸው ገልጸዋል።
በዚህም የተነሳ አፈናውን እና ስወራውን የሚፈጽም የተለየ ኃይል እንዳለ እንደሚያምኑ የሚጠቅሱት ያሬድ፣ እነሱም "ታፋኞቹን ወዳልታወቀ ቦታ ወስደው ለቀናት ካቆዩ በኋላ ጥያቄ እና መነጋገሪያ ሲሆኑ መንገድ ላይ ወይም ፖሊስ ጣቢያ አምጥተው ይጥሏቸዋል" ይላሉ።
ማንነታቸው የማይታወቁ፣ ፊታቸውን የሚሸፈኑ፣ የፖሊስ ወይም የወታደር የደንብ ልብስ የሚለብሱ፣ በመንግሥት ወይም በግል ተሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚፈጽሙት አፈና ግራ መጋባትን በመስከተል ስጋትን ይፈጥራሉ።
ያሬድ እንደሚሉት የመንግሥት አካል መሆናቸው ቢታወቅ እንኳን ሕጋዊውን ሥርዓት ስለማይከተሉ በሕዝቡ ውስጥ በተቋማት ላይ ያለውን ዕምነት የሚያሳጣ "አደገኛ የሆነ የመንግሥታዊ ሥርዓት ውድቀት ማሳያ ነው።"
እነዚህ ሁሉ ድርጊቶች አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሲከሰቱ የመንግሥት አካላት ዝምታን መምረጣቸው ደግሞ ግራ አጋቢ ሆኗል።
ይህ ደግሞ የመንግሥት እጅ እንዳለበት እና ይሁንታውን የሰጠው ድርጊት ነው የሚያስብል ከመሆኑ በተጨማሪ በሕጋዊ ተቋማት ሚና እና ተቀባይነት ላይ ተስፋ መቁረጥ እያስከተለ መሆኑን ያሬድ ኃይለማሪያም ይናጋራሉ።
ይህንን እገታ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ያሉ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ እየፈጸሙ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን አስፈሪ አድርገውታል። ተመሳሳይ ስጋት በከተሞች ውስጥ መኖሩ ደግሞ ዜጎች ደኅንነት እንዳይሰማቸው ያደርጋል።
"በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ ታጣቂዎችን ይፈራል፤ በተጨማሪም ይጠብቀኛል የሚለውን መንግሥትንም ይፈራል" የሚሉት አቶ ያሬድ፣ "ሕገወጥ ቡድኖች ሲያፍኑ መፍትሔው መንግሥት ነው ይባል ነበር። አፋኙ መንግሥት ሲሆን ወደ የት ይኬዳል?" ሲሉ ይጠይቃሉ።