በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ኬንያ የገቡ 44 ኤርትራውያን ስደተኞች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ

የኬንያ ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሕገ ወጥ መንገድ ኬንያ የገቡ 44 ኤርትራውያን ስደተኞች በምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍል መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

ቡንጎማ በተባለው የኬንያ ግዛት ትናንት እሑድ ጥቅምት 23/2018 ዓ. ም. የተያዙት ስደተኞቹ ሚቲ ምቢሊ በሚባል ገጠራማ መንደር በሚገኝ የአንድ ግለሰብ መኖሪያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፖሊስ መረጃ ይጠቁማል።

ቡንጉማ ግዛት ኤርትራውያን ስደተኞች ከኢትዮጵያውያ ወደ ኡጋንዳ እና ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የሚተላለፉበት መስመር ነው።

ስማቸው ያልተጠቀሰ የዓይን እማኞች እንዳሉት፤ ስደተኞቹ ትናንት ጠዋት በወታደራዊ ተሽከርካሪ ወደ አካባቢው ደርሰዋል።

ኤርትራውያኑ በብሪጋደር ፖሊስ ጣቢያ የተያዙ ሲሆን፤ ምርመራ ተደርጎባቸው ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ተገልጿል።

በኤርትራ ያለውን አፈና እና ጭቆና የሚሸሹ ስደተኞች ከዚህ ቀደም በሱዳን በኩል ያልፉ የነበረ ቢሆንም፤ በእርስ በእርስ ጦርነቱ ምክንያት ይህንን መንገድ መጠቀም አልቻሉም።

የሱዳን ጦርነት ሲነሳ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ተሻግረዋል። ስደተኞቹ በኢትዮጵያ ለተወሰነ ጊዜ ቆይተው ወደ ኡጋንዳ እና ኬንያ ያቀናሉ።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ዳግም የተጀመረው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት ግንኙነት በትግራይ ጦርነት ወቅት ተጠናክሮ ነበር። በዚህ ወቅት ኤርትራውያን ስደተኞች ለደኅንነታቸው በመስጋት በዋናነት ኡጋንዳን፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኬንያን አማራጭ አድርገዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ሰነድ ያላቸው ስደተኞች በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት እንዳሰጋቸው እና ከኢትዮጵያ ይልቅ ወደ ኡጋንዳ መሰደድን እንደሚመርጡ ይናገራሉ።

በኡጋንዳ፤ የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን እና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ስደተኞች ይኖራሉ።

ኡጋንዳ ከጥር ጀምሮ የስደተኞች ምዝገባ እንደቋረጠች ማስታወቋን ተከትሎ ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ኬንያ እየተጓዙ ነው።

ሆኖም ግን የኬንያ መንግሥትም የስደተኞች ምዝገባ ለማቆም በመወሰኑ ስደተኞቹ ወደ ሊቢያ እየተሻገሩ እንደሆነ የቢቢሲ ምንጮች ገልጸዋል።

ስምዖን የተባለ ኤርትራዊ ስደተኛ ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ የፖላንድ ኤምባሲ የቪዛ ጥያቄውን ውድቅ ካደረገ በኋላ ለሁለት ዓመታት ገደማ በኬንያ ኖሯል።

"በጋብቻ ወደ ፖላንድ ለመሄድ ሞክሬ የቪዛዬ ጥያቄዬ ውድቅ ተደረገ። ይግባኝ ብልም በድጋሚ ውድቅ አደረጉት።በዚህም ምክንያት እንደ አማራጭ የወሰድኩት በሊቢያ አድርጎ ወደ አውሮፓ መግባትን ነው" ይላል።

አክሎም፤ "ኬንያ ውስጥ በርካታ ስደተኞች ስለሚኖሩ [አገሪቱ] የስደተኞችን ሰነድ ለማደስም ፈቃደኛ አይደለችም። ወደ ሊቢያ የሄድኩት አማራጭ ስላጣሁ ነው" ብሏል።

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ በመምጣቱ ኤርትራውያን ስደተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ እንደሚታሰሩ እና እንግልት እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ።

በዚህም ምክንያት ከኢትዮጵያ ለመውጣት ይገደዳሉ።

ከዚህ ቀደም ኡጋንዳ ለኤርትራውያን ስደተኞች ምቹ እንደነበረች ይነገራል። አንጻራዊ ነጻነት እና የሥራ ዕድል ያገኙም ነበር። አሁን ግን ስደተኞቹ ወደ ኬንያ ለመሄድ ተገድደዋል።

ከዚህ በፊት ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ኬንያ ለመግባት ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የጥገኝነት ጥያቄያቸው በፍርድ ቤት ከታየ በኋላ ከእስር የተለቀቁም አሉ።

ኬንያ ስደተኞችን መመዝገብ ማቆሟን ካስታወቀች በኋላ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውት የኬንያ መንግሥት ውሳኔ ተቀልብሷል።

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ኬንያ ከቀናት በፊት ጥቂት ስደተኞችን ብቻ መመዝገብ መጀመሯን ቢቢሲ ለማረጋገጥ ችሏል።