ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ካሜሮን የ91 ዓመቱ ፕሬዚዳንቷ ጤናን የሚመለከቱ ሪፖርቶችን አገደች
የካሜሮን ባለስልጣናት የ91 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ፖል ቢያን ጤናን የሚመለከቱ ሪፖርቶች ሚዲያዎች እንዳይዘግቡ አገዱ።
ባለስልጣናቱ ይህንን እግድ ያስተላለፉት አዛውንቱ ፕሬዚዳንት ሞተዋል የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።
የአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፖል አታንጋ ንጂ ለክልል አስተዳዳሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት እንዲህ ያሉ ዜናዎች “የካሜሮናውያንን መንፈስ የሚረብሹ ናቸው” ብለዋል።
“በዚህም የተነሳ የፕሬዚዳንቱን ጤንነት አስመልክቶ በሚዲያ የሚቀርቡ ማንኛውም ውይይቶች በጥብቅ የተከለከለ ነው” ያሉት ፖል አታንጋ ይህንን ማስጠንቀቂያ የሚተላለፉ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አስፈራርተዋል።
ከአራት አስርት ዓመታት በላይ በስልጣን የቆዩት የ91 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ከጥቂት ሳምንታት በፊት በቤጂንግ በተካሄደው የቻይና- አፍሪካ ጉባኤ በኋላ በአደባባይ አልታዩም።
የአገሪቱ ባለስልጣናት ፕሬዚዳንቱ በጄኔቫ ስዊዘርላንድ እረፍት እያደረጉ እንደሆነ እና በመልካም ጤንነት ላይ እንዳሉ በመግለጽ የእረፍታቸውን ዜና አሉባልታ ሲሉ አስተባብለዋል።
ፖል አታንጋ የፕሬዚዳንቱ የጤና ሁኔታ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ መሆኑን ገልጸው የተለያዩ ክልል አስተዳዳሪዎች የግል እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያዎች ይህንን ጥብቅ ትዕዛዝ እየተከተሉ መሆኑን የሚያረጋግጡ ኮሚቴዎችን እንዲያቋቋሙ አሳስበዋል።
የአገሪቱ በርካታ ጋዜጠኞች እግዱ የፕሬስ ነጻነትን የሚጥስ ነው ሲሉ ተችተውታል።
“የፕሬዚዳንቱን የጤና ሁኔታ መጥቀስ አይቻልም ማለት መብታችንን የሚጥስ ጉዳይ ነው” በማለት ስማቸውን እንዳይገለጽ የጠየቁ ጋዜጠኛ ለቢቢሲ ተናግረው አክለውም “ከመንግሥት አካላት ጋር ችግር ውስጥ መግባት ስለማንፈልግ በሪፖርቶቻችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር እርግጥ ነው” ብለዋል።
በመገናኛ ብዙኃን ላይ የተጣለው እገዳ ጋዜጠኞች በአገሪቱ ባለስልጣናት እና አማጺ ቡድኖች ዒላማ በሆኑበት ሁኔታ ተጨማሪ የደህንነት ስጋትን ጋርጧል።
ከዚህ ቀደም የአገሪቱ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ (አንግሎፎን) ተገንጣዮች ጋዜጠኞችን ሲያግቱ መንግሥት በበኩሉ ያስራል።
“ይከታተሉኛል ብየ ብሰጋም ፕሬዚዳንቱ ያሉበትን ወይም ምን ደርሶባቸው ይሆን? በሚለው ጉዳይ ላይ ሪፖርት ማቅረቤን አላቆምም። ስራዬን መስራቴን እቀጥላለሁ” ሲል ሌላ ጋዜጠኛ ተናግሯል።
የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ የካሜሮን መንግሥት “የፕሬዚዳንት ፖል ቢያን ጤንነት ሁኔታ እና ያሉበትን ስፍራ በሚዘግቡ የግል ሚዲያ ጋዜጠኞች ላይ የጣለውን እገዳ እንዲቀለብስ” አሳስቧል።