በእስራኤል እና ሔዝቦላህ መካከል እየተባባሰ የመጣው ግጭት ሌባኖሳውያንን አስጨንቋል

ካለፈው ጥቅምት ጀምሮ በእስራኤል እና በኢራን በሚደገፈው የሌባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሔዝቦላህ መካከል ያለው ውጥረት እና ግጭት እየተባባሰ መጥቷል።

በግጭት ምክንያት በሁለቱም ወገን የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ በርካታ ሺዎች ደግሞ ቤት ንብረታቸው ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል።

ይህ ግጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረረ የመጣ ሲሆን ወደለየለት ጦርነት ይገባል የሚል ስጋት አለ።

ምንም እንኳ ሁለቱ ኃይሎች በጥቃትና በመልሶ ማጥቃት ቢወጠሩም ከባድ የሚባል ጦርነት ውስጥ ላለመግባት ጥንቃቄ ሲያደርጉ ይስተዋላል።

ነገር ግን ባለፈው ቅዳሜ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ባለችው ጎላን ሀይትስ በተሰኘችው ሥፍራው የደረሰው ጥቃት ሁለቱ ኃይሎች ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ይገባሉ የሚል ጥርጣሬ ጭሯል።

እስራኤል ድሩዝ ከተማ ባለ አንድ የእግር ኳስ ሜዳ ላይ ደርሶ ሕፃናትን ጨምሮ 12 ሰዎችን የገደለውን ጥቃት ያደረሰው ሔዝቦላህ ነው ስትል ትወቅሳለች። እስራኤል ለዚህ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ቃል ገብታለች።

“እስራኤል ይህን ጥቃት በዋዛ የምታልፈው አይደለም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በቢሯቸው በኩል በለቀቁት መግለጫ አስታውቀዋል።

“ሔዝቦላህ እስከዛሬ ድረስ ከፍሎት የማያውቀውን ዋጋ ይከፍላታል” ሲሉም ዝተዋል።

ነገር ግን ሔዝቦላህ የተባለው የሌባኖሱ ታጣቂ ኃይል ጥቃቱን አላደረስኩም ሲል ያስተባብላል።

ቢሆንም ቡድኑ ሔርሞን የተባለውን ብሪጌድ በኢራን ሰራሽ ፋላቅ ሚሳዔል መምታቱን የገለጠ ሲሆን ቅዳሜ ዕለት ከደረሱ በርካታ ጥቃቶች አንዱ ነው።

ድሩዝ የምትባለው ከተማ ከሔርሞን ተራራ 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ሔዝቦላህ ምናልባት ዒላማውን ስቶ ሊሆን ይችላል የሚሉ መላ ምቶች እየተሰሙ ነው።

የእስራኤል ጦር ሠራዊት ቃል አቀባይ ዳንኤል ሐጋሪ፤ ቡድኑን ጥቃቱን ማስተባበሉ “ሐሰት” ነው ብለው የስለላ መረጃዎች የሚያሳዩት ጥቃቱ የተሰነዘረው በሔዝቦላህ ነው ሲሉ ገልጠዋል።

“ሁሉም ነገር የሚጠቁመው” ሚሳዔሉ የተተኮሰው በሔዝቦላህ ነው ሲሉ የተናገሩት የዩኤስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በበኩላቸው “እስራኤል በምታደርገው ራሷን የመከላከል እርምጃ አሜሪካ ከጎኗ ትቆማለች” ብለዋል።

በዚህ ምክንያት ሌባኖስ ከእስራኤል የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ይሰነዘራል በሚል ፍራቻ ላይ ትገኛለች።

ሔዝቦላህ እስራኤል ላይ ጥቃት ማድረስ የጀመረው በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 8 ሲሆን ከአንድ ቀን በፊት የፍልስጤሙ ሐማስ ያደረሰውን ጥቃት በመደገፍ እንደሆነ አስታውቋል።

እስካሁን በሁለቱ ኃይሎች መካከል በተከሰተ ግጭት 450 ሌባኖስ ውስጥ ሲገደሉ 350ዎቹ የሔዝቦላ ታጣቂዎች ሲሆኑ 100 ደግሞ ሰላማዊ ነዋሪዎች ናቸው። በእስራኤል በኩል ደግሞ 23 ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ 17 ወታደሮች በጥቃቱ ሞተዋል።

ሌባኖስ ውስጥ የደረሱት ጥቃቶች አብዛኛዎቹ ጥቃቶች የሀገሪቱን ደቡባዊ ክፍል ዒላማ ያደረጉ ናቸው። በተለይ ሔዝቦላህ በሚንቀሳቀስባቸው ቤካ ስምጥ ሸለቆ በተባለው አካባቢ እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት መንደሮች ሲወድሙ በርካቶች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ሸሽተዋል።

እስራኤል እስካሁን ዒላማ ያልተደረጉ ዋና ከተማዋ ቤይሩትን ጨምሮ ትላልቅ የሚባሉ ከተማዎችን ልትመታ ትችላለች የሚለው ሐሳብ ግጭቱ ወደለየለት ጦርነት እንዳያመራ ስጋት ሆኗል።

ከሐማስ የበለጠ የተደራጀ ኃይል አለው የሚባለው ሔዝቦላህ በአውሮፓውያኑ 2006 ከተከሰተው ግጭት በኋላ ከእስራኤል ጋር ከባድ ጦርነት ለመግጠም ዝግጅት እያደረገ ቆይቷል።

ምዕራባዊያን ሀገራት እንደሚሉት ቡድኑ 150 ሺህ ሮኬቶች እና ሚሳዔሎች የታጠቀ ሲሆን የእስራኤልን የተወሳሰበ የአየር መከላከያ ሊፈትነው ይችላል የሚል ግምት አለ። ቡድኑ፤ የእስራኤል ዋና ዋና ከተማዎች ማጥቃት የሚችሉ ዒላማቸውን የማይስቱ ሚሳዔሎች እንዳሉት ይነገራል።

በሁለቱ መካከል የሚነሳ ግጭት ሁለቱንም ሀገራት የሚጎዳ እንደሆነ ባይካድም በተለይ ባለፉት አስርት ዓመታት አለመረጋጋት ላይ ላለችው ሌባኖስ አደጋ ሊሆን ይችላል።

ዲፕሎማቶች በሁለቱ ኃይሎች መካከል ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ጥረት እያደረገ ይገኛሉ። የሌባኖሱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብደላህ ቦ ሐቢብ፤ ባለሥልጣናት ሔዝባላህ “መልሶ ማጥቃት እንዳይፈፅም እየጠየቁ ነበር” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።