ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩክሬን እና ሩሲያ እህል ወደ ውጭ እንዲላክ ምን ለማድረግ ተስማሙ?
ዩክሬን እና ሩሲያ ኪዬቭ በጥቁር ባሕር በኩል እህል ወደ ውጭ እንድትልክ የሚያስችላትን ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱ በጦርነቱ ምክንያት በዩክሬን ውስጥ ታግቶ የቆየውን በሚሊዮኖች ቶን የሚቆጠር እህልን ወደ ውጭ ለመላክ ያስችላል።
የካቲት ወር ላይ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈፀሟን ተከትሎ ከዩክሬን ወደ ውጭ የሚላከው እህል በመስተጓጎሉ በዓለም የእህል እጥረት እንዲያጋጥም አድርጓል።በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችንም የረሃብ አደጋ ላይ ጥሏል።
ሆኖም ኪዬቭ " ሩሲያ አሁንም ጸብ አጫሪነቷን ላትተው ትችላለች" በሚል ከሞስኮ ጋር ቀጥተኛ ስምምነት ለመፈረም ፈቃደኛ ያልነበረች ሲሆን፣ በኋላ ላይ ግን ስምምነቱን ፈርማለች።
በቱርክ፣ ኢስታንቡል በተካሄደው በዚህ የስምምነት ሥነ ሥርዓት ላይ ግን ሁለቱ ወገኖች በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ አልተቀመጡም።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ መጀመሪያ ላይ በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያስቀመጡ ሲሆን፣ የዩክሬን መሠረተ ልማት ሚኒስትር ኦሌክሳንድር ኩብራኮቭ አገራቸው መስማማቷን በፊርማቸውን አረጋግጠዋል።
ሁለቱ አገራት እዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሁለት ወራትን የፈጀ ሲሆን ስምምነቱም ለሦስት ወራት ይቆያል ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት፣ የቱርክ፣ የሩሲያ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት ያሉበት የማስተባባሪያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከልም በኢስታንቡል እንደሚቋቋም ተነግሯል።
ስምምነቱ በሁለቱ ወገኖች ስምምነትም እንደገና ሊታደስ ይችላል።
ዩክሬን የእህል ምርቶቿን ወደ ውጭ መላክ አለመቻሏ በዓለም ላይ የምግብ ቀውስን አስከትሏል።
በስንዴ የሚዘጋጁ እንደ ዳቦ እና ፓስታ ያሉ የምግብ ምርቶች ዋጋም እንዲንር ምክንያት ሆኗል። የምግብ ዘይት እና የአፈር ማዳበሪያ ዋጋም አሻቅቧል።
ሩሲያ በዚህ ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንድትወስድ አሜሪካ ጥሪ አቅርባለች። የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢይ “በዓለም ላይ በጣም ተጋላጭ የሆኑ አገራት ወደ የከፋ ስጋት እና የተመጣጠነ ምግብ እጦት ውስጥ እንዳይገቡ ለመከላከል ስምምነቱ አስፈላጊ ነው” ብለው ነበር።
ቃል አቀባዩ ከስምምነቱ ቀደም ብሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ ስምምነቱ “በሚቀጥሉት ቀናት የመፍትሄው ሂደቶች እንዲጀመሩ ይፈቅዳል” ሲሉም ተናግረው ነበር።
“እያወራሁ ያለሁት ከዩክሬን ወደቦች የግብርና ውጤቶችን ወደ ውጭ መላክ ስለመጀመር ብቻ አይደለም። ይህ ከሩሲያ ወደቦችም የግብርና ውጤቶችን እና ማዳበሪያዎችን ለመላክ ያስችላል” ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ምን ላይ የተስማሙት?
እንደ ዲፕሎማቶች ከሆነ ሩሲያ እና ዩክሬን በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
- ሩሲያ ጭነት በሚጓጓዝበት ወቅት ወደቦችን ኢላማ አታደርግም።
- የዩክሬን ትላልቅ ጀልባዎች እቃ ጫኝ መርከቦችን ፈንጂ በተቀበረባቸው የውሃ ክፍሎች ይመራሉ።
- ቱርክ በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ የሩሲያን የጦር መሣሪያ ዝውውር ስጋት ለማስወገድ በመርከቦች ላይ ፍተሻ እና ቁጥጥር ታደርጋለች።
- ሩሲያ እህል እና ማዳበሪያ በጥቁር ባሕር በኩል ወደ ውጭ እንድትልክ ይመቻችላታል።
በቱርክ፣ ኢስታንቡል በተካሄደው የስምምነት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ እና የቱርክ ፕሬዚደንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን፣ የቱርክ መከላከያ ሚኒስትር ሁልሲ አካር ተገኝተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ ዓለም አቀፉን ተቋምን እየመሩ ባሉበት ወቅት ይህ ምንአልባትም የከወኑት ወሳኙ ተግባር እንደሆነ ለቢቢሲ ዘጋቢ ተናግረዋል።
ዋና ጸሐፊው በኢስታንቡል ባደረጉት ንግግር “ዛሬ በጥቁር ባሕር ላይ የተስፋ ብርሃን አለ” ብለዋል።
በዩክሬን የተከማቸውን ከ20 ሚሊዮን ቶን በላይ እህል ወደ ውጭ እንዲላክ የማድረግ ተስፋው ብቻ አርብ ዕለት በስንዴ ዋጋ ላይ የ2 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።
የዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ አርብ ምሽት ላይ ባደረጉት ንግግር አገሪቷ 10 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያለው ለሽያጭ የሚቀርብ እህል እንዳላት ተናግረዋል።
ሆኖም ሞስኮ “ቅስቀሳዎች በማድረግ ፣ የዩክሬንን እና ዓለም አቀፉን ጥረት ለማጣጣል ልትሞክር ትችላለች” ሲሉ ያስጠነቀቁ ሲሆን፣ “ነገር ግን በተባበሩት መንግሥታት እምነት አለን። ለስምምነቱ ዋስትና መስጠት ያለበትም የተባበሩት መንግሥታት ነው” ብለዋል።
ጉቴሬዝ በበኩላቸው ሩሲያ ስምምነቱን ባታከብር የተባበሩት መንግሥታት ሩሲያ ላይ ቅጣት የሚወስድበት ምንም አማራጭ አለመኖሩን ለቢቢሲ አምነዋል። ነገር ግን “ይህ ምንም ተቀባይነት የሌለው ቅሌት ነው። ለዚህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጠንካራ ምላሽ ይሰጣል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ በበኩላቸው፣ ሩሲያ በስምምነቱ መሠረት ግዴታዋን እንደምታከብር ከስምምነቱ በኋላ ለጋዜጠኞች አረጋግጠዋል።
ሩሲያ ብዙውን ጊዜ ወደቦችን ዘግታለች በሚል የሚቀርብባትን ክስ ያስተባበለች ሲሆን፣ዩክሬን በባህር ላይ ፈንጂ በማስቀመጧ እና ምዕራባውያኑ በሩሲያ ላይ በጣሉት ማዕቀብ ሳቢያ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት እንዲቀንስ እንዳደረገው ገልጻለች።
ዩክሬን በበኩሏ መርከቦቿ እንዳይንቀሳቀሱ ያገደችው ሩሲያ እንደሆነችና ወታደሮቿም ከዩክሬን ማሳ እህል ይሰርቃሉ ስትል ትከሳለች።
አሁን እህል ወደ ውጪ ለመላክ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት በተለይም በድርቅ፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ፣ በአንበጣ መንጋ ወረራ እና በዩክሬን ጦርነት ሳቢያ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው የአፍሪካ ቀንድ አገራት ትልቅ እፎይታን ይሰጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።