ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማረጥ ምንድን ነው? ምልክቶቹስ?
ለበርካታ ሴቶች የማረጥ ምልክቶች በ40ዎቹ አጋማሽ ላይ መታየት ይጀምራል።
የወር አበባ መቆምን የሚያበስረው የህይወት ደረጃ በየአመቱ የአለም ማረጥ ዕለት ተብሎ ይከበራል።
ይህችን ዕለት በማስመልከት ስለ ማረጥ ምንነት፣ እንዲሁም ያሉትን ደረጃዎችን እንመለከታለን።
ማረጥ ምንድን ነው?
ማረጥ የሴቶች የወር አበባ የሚቆምበት ወቅት ሲሆን ይህም በአብዛኛው በ 51 አመት አካባቢ ይከሰታል።
ይህም ወቅት ሴቶች ልጆች የሚያፈሩበት ጊዜ የሚያከትምበትና አዲስ የሕይወት ምዕራፍ መጀመሩን ያሳያል።
የወር አበባ መደበኛ አለመሆን፣ መቆራረጥ በአማካይ በ46 አመት የሚጀምር ሲሆን ይህም ቅድመ ማረጥ ይባላል።
በዚህም ወቅት የወር አበባቸው መምጫ መለዋወጥ፣ ወይም ከባድ መሆን የሚያጋጥማቸው ሲሆን በተጨማሪም ከዚህ በፊት አይተውት በማያውቅ ሁኔታ ስሜታቸው ሲቀያየር ወይም አካላዊ ችግሮች ያጋጥማቸዋል።
የወር አበባ ለአስራ ሁለት ወራት ወይም ለአንድ አመት ያህል ካልመጣ ማረጥ ተከስቷል ማለት ነው።
በአንዳንዶች ላይ በተፈጥሮ፣ ወይም ለሌላ በሽታ ካደረጉት ህክምና ጋር ተያይዞ ቀደም ብሎ ሊከሰት ይችላል።
መንስኤው ምንድን ነው?
በተለይም የወር አበባ ዑደትን የሚቆጣጠረው ኤስትሮጅንን ጨምሮ የሆርሞን መጠን የሚቀየርበት ነው።
ሴቶች በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ እንቁልጢ (ኦቫሪ) ጥቂት እንቁላሎችን ያመርታሉ። ኤስትሮጅን የተሰኘው ሆርሞን መጠን ይለዋወጣል ከዚያም ቀስ በቀስ ይቀንሳል፤ ይህ ደግሞ ወደ ማረጥ ምልክቶች ያመራል።
ይህ ግን በአንድ ጀምበር አይከሰትም።
ይህ ወሳኝ ሆርሞን መጠኑ ዝቅተኛ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ብዙ አመታትን ሊወስድ የሚችል ሲሆን በዚያም መንገድ ለተወሰነ ጊዜ ይቆያል፤ በሰውነት ላይም ለውጦችን ያመጣል።
እንቁልጢዎች (ኦቫሪ) ሙሉ በሙሉ እንቁላል ማምረት ሲያቆሙ እርግዝና የማይቻል በመሆኑ ማረጥ ይከሰታል።
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
የወር አበባ መቋረጥ ከዚያ በፊት ባሉት ቀደምት ዓመታት ሴቶች ላይ በተለያየ መንገድ ተፅእኖ ያሳርፋል።
የኤስትሮጅን መጠን በሰውነት ውስጥ መቀነስም የስሜት መለዋወጥን ጨምሮ በአእምሮ፣ በወር አበባ፣በቆዳና ጡንቻዎች ላይ የተለያዩ ለውጦችን ያስከትላል።
ከዚህም በላይ በርካታ ምልክቶች ያሉ ሲሆን አንዳንዶች ሁሉንም፣ወይም አንዳንዶቹም ወይም ምንም ምልክቶች ላያዩ ይችላሉ። እነዚህም ምልክቶች የሚቀያየሩ ሲሆን ለተለያዩ የጊዜ እርዝማኔዎችም ይቆያሉ።
ሆኖም በጣም የተለመዱት ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፦
- ከባድ ወይም መደበኛ ያልሆነ የወር አበባ
- ሙቀት ሙቀት ማለት
- በሌሊት ማላብ
- መደበት
- የሴት ብልት መድረቅ
- የፊኛ ችግሮች
አብዛኛውን ጊዜ የአዕምሮ ጭጋግ ተብሎ የሚጠራው ደካማ የማስታወስ ችሎታ እና ትኩረት ማጣት የሚከሰቱ ሲሆን በተጨማሪም የመገጣጠሚያዎች ህመም እና የቆዳ መድረቅም ይገጥማል።
ሁሉም ሴቶች ባይሆኑም 75 በመቶ የሚሆኑት እነዚህ ምልክቶች ይታዩባቸዋል።
ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አንድ አራተኛ የሚሆኑት ከበድ ያሉ ምልክቶች እንዳጋጠሟቸው ይናገራሉ።
እነዚህ ምልክቶች በአማካይ ለሰባት አመታት ሊቆዩ የሚችሉ ሲሆን ከሶስቱ ሴቶች አንዷ ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ያጋጥማታል።
የማረጥ ምርመራ አለ?
ማረጥን ለመርመር የሚጠቅሙ መሳሪያዎች ገበያ ላይ ውለዋል፤ ነገር ግን ባለሙያዎች ከ45 ዓመት ዕድሜ በኋላ ጠቃሚ እንዳልሆነ ይስማማሉ።
ማረጥን ለማወቅ የተሻለው መንገድ ስለ የወር አበባዎ ሁኔታ እና እያጋጠመዎት ያሉትን ምልክቶች ለጤና ባለሙያ በመንገር መወያየት ነው።
ምርመራው ፎሊክል ስቲሙሌቲንግ የተባለውን የሆርሞን መጠን ይለካል። ይሁን እንጂ የሆርሞን መጠን በአንድ ቀን ውስጥ እንኳን ቢሆን ስለሚቀያየር ምርመራው በሰውነት ውስጥ ምን እየተካሄደ እንዳለ በትክክል ማወቅ አይችልም።
ሴቶች የወር አበባቸው መደበኛ ባይሆንም እንኳ መጸነስ ይችላሉ።
ለዚያም ነው ባለሙያዎች እስከ 55 አመት እድሜ ድረስ የእርግዝና መከላከያዎችን እንዲጠቀሙ የሚመክሩት።
የእርጣትን ምልክት ለመቀነስ ህክምናዎች ይኖሩ ይሆን?
ማረጥ በሚጀምርበት ወቅት እንደ ኤስትሮጅን ያሉ ሆርሞኖች በከፍተኛ ሁኔታ ዝቅ ስለሚሉ ይህንን ለመተካት ሆርሞን ሪፐሌስመንት ቴራፒ የሚባለው ህክምና በማረጥ ወቅት የሚያጋጥሙ ህመሞችን እፎይታ ለመስጠት ይረዳሉ።
ነገር ግን ካንሰር፣ የደም መርጋት እና የደም ግፊት የህመም ታሪክ ላላቸው ሰዎች ተስማሚ ላይሆን ይችላል።
ሴቶች በእርጣት ወቅት የሚሰሟቸውን ስሜቶችም ለማሻሻል፦
- አጥንትን ለማጠንከር እና የልብ ጤናን ለመጠበቅ የተመጣጠና ከፍተኛ ካልሲየም ያላቸውን ምግቦችን መመገብ፣ የስብ ይዘት ያላቸውን ምግቦች ማስወገድ
- ጭንቀትንና የልብ ህመምን መከላከል አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ
- ሙቀት ሙቀት የሚለው ስሜትና የልብ ህምምን ለመከላከል ሲጋራ ማጨስ ማቆም እንዲሁም አልኮል አለመጠጣት
ኦስትሮጅን ዕፅዋትን የያዙ እንደ አኩሪ አተር ምግቦችን መመገብ የእርጣት የህመም ምልክቶችን ለመቀነስ ከመርዳት በተጨማሪ፣ ቫይታሚን ዲ የያዙ ተጨማሪ ምግቦችን መመገብ የአጥንትን ጤንነትን እንደሚያሻሽሉ የሚጠቁሙ ጥናቶችም አሉ።
ከማረጥ በኋላ ምን ይሆናል?
የመጨረሻ የወር አበባዎትን ካዩ ከአንድ አመት በኋላ ድህረ ማረጥ የሚባለው ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል ይባላል።
ኤስትሮጅን በሰውነት መመረት ሙሉ በሙሉ ካቆመ፣ በአጥንት እና በልብ ላይ የረጅም ጊዜ ተፅእኖ ያሳድራል።
ይህ ሁኔታ አብዛኛው የእርጅና አካል ነው።
የሴቶች አማካኝ እድሜ እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት በርካቶች ከእርጣት በኋላ ከሕይወታቸው አንድ ሦስተኛውን በላይ እየኖሩ ነው።