በትግራይ በጦርነት የተሳተፉ “አርበኞች” በነጻ የቤት መሥሪያ እና የሥራ ቦታ እንዲያገኙ የሚያደርግ ደንብ ሥራ ላይ ዋለ

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ በተካሄዱ ጦርነቶች ውስጥ የተሳተፉ እና ሕይወታቸውን ያጡ ተዋጊዎች ቤተሰቦች በነጻ የቤት መሥሪያ መሬት እና የሥራ ቦታ እንዲያገኙ የሚያስችል ሕግ በሥራ ላይ ማዋል ጀመረ።

በተጨማሪም አዲሱ ሕግ ነጻ ህክምና እና የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ እንዲሁም በሥራ ቅጥር ላይ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የሚያደርግ ነው።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት ጽህፈት ቤት፤ “የትግራይ አርበኞች፣ የተሰዉ አርበኞች ቤተሰብ እና የአርበኞች ቤተሰብ መብት እና የተጠቃሚነት ደንብ” የተባለውን ይህንን ሕግ ወደ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሐምሌ 16/ 2016 ዓ.ም. ነው።

አዲሱ የመብት እና የተጠቃሚነት ደንብ፤ “የተሰዉ” እና በህይወት ያሉ “አርበኞች” እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን ያካተተ እንደሆነ የትግራይ ክልል አርበኞች ኮሚሽን የአርበኞች መብት እና ጥቅም ዳይሬክተር አቶ አዲስዓለም ገብረሥላሴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ አዲስዓለም እንደሚያስረዱት አዲሱ ደንብ ተጠቃሚ የሚያደርገው ከደርግ ዘመነ መንግሥት ከ1967 ዓ.ም. አንስቶ በነበሩ የተለያዩ የትጥቅ ትግሎች ውስጥ የተሳተፉ ግለሰቦችን ነው።

የቃላት ትርጓሜ በተቀመጠበት የደንቡ ክፍል ላይ “አርበኛ” በሚለው ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ሰዎችን ምን ዓይነት ተሳትፎ የነበራቸው እንደሆነ አስፍሯል። “አርበኛ”ን በተመለከተ በቀዳሚነት የተጠቀሰው “የትግራይ ሕዝብ ፀረ ጭቆና ትግል” የሚል ነው።

ይህ ትርጓሜ በደርግ ዘመነ መንግሥት የነበረውን “የ17 ዓመትን የትግል ምዕራፍ” የሚያመለክት እንደሆነ የአርበኞች መብት እና ጥቅም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በዚህ ምድብ ውስጥ የሚካተቱ “ጥቂት የማይባሉ አርበኞች” ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ መብቶች ተጠቃሚ እንደሆኑ እና በአዲሱ ደንብ ውስጥ የማይካተቱባቸው ጥቅሞች እንደሚኖሩ አቶ አዲስዓለም አመልክተዋል።

ደንቡ ላይ በሁለተኝነት የተጠቀሰው፤ “በትግራይ ሕዝብ የዘር ማጥፋት ወረራ ትግል” የሚለው አገላለጽ ደግሞ በ2013 ዓ.ም. የተጀመረውን ጦርነት የሚያመለክት እንደሆነ አብራርተዋል።

አቶ አዲስዓለም እንደሚያስረዱት፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የተሳተፉ እና “ሕገ መንግሥቱን ሲጠብቁ የነበሩ” የትግራይ ተወላጆችም “አርበኛ” በሚለው ትርጓሜ ውስጥ ተካትተዋል።

ከዚህም ባሻገር ሚሊሻ ሆነው የታገሉ እና መረጃ ሊያቀርብ የሚችል እንዲሁም “ከትግራይ ሕዝብ መሠረታዊ ጥቅም ተቃራኒ ሆኖ ያልተሰለፈ” ግለሰብም እንደሚካተት ደንቡ ይገልጻል።

አቶ አዲስዓለም እንደሚገልጹት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይህንን ደንብ ያወጣው “አርበኞች ለከፈሉት መስዋዕትነት እውቅና ለመስጠት” ነው።

“የመጀመሪያው ፍላጎታችን እነዚህ አርበኞች በቀረ አካላቸው፣ ባላቸው አቅም ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ነው” በማለት፤ ለዚህም ሲባል ደንቡ “አንድ ሰው ሕይወቱን ለመምራት የሚያስችሉ ነገሮችን” ለማካተት እንደተሞከረ ጠቅሰዋል።

በመብት እና ተጠቃሚነት ደንቡ ላይ “አርበኞች” 20 ገደማ ጉዳዮች ላይ “ነጻ” ተጠቃሚነት እንደሚኖራቸው ዘርዝሯል። ከጥቅሞቹ ውስጥ በቀዳሚነት የተጠቀሰው ህክምናን የተመለከተ ነው።

“አርበኞች” በመንግሥት የህክምና ተቋም ውስጥ እና “እንደ የጤናው ችግር ክብደት በውጭ አገር” በነጻ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ደንግጓል። ህክምናው በመንግሥት ተቋም ባለመኖሩ አገር ውስጥ ባለ የግል ህክምና ተቋማት የሚታከሙ ከሆነ ደግሞ “ወጪው በመንግሥት እንደሚተካ” አስፍሯል።

“አርበኞቹ የተሰዉ” ከሆነ ቤተሰቦቻቸው በአገር ውስጥ በሚገኙ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ የጤና ተቋማት በነጻ ህክምና የማግኘት መብት በደንቡ ተሰጥቷቸዋል። በደንቡ “የተሰዉ አርበኞች” ቤተሰብ በማለት የሚጠቅሳቸው ባለቤት፣ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች እና “የአርበኞቹ” ወላጆች ናቸው።

የሌሎች “አርበኞች” የቤተሰብ አባላትም መንግሥታዊ የጤና ተቋማት ውስጥ በነጻ ህክምና ማግኘት እንደሚችሉ ደንቡ ላይ ሰፍሯል። ለ“አርበኞች” እና ቤተሰቦቻቸው የተሰጠው ይህ ነጻ ህክምና የማግኘት መብት “የሕይወት ዘመን” የሆነ እና “የትኛውም ዓይነት በሽታ ሲያጋጥም” ተፈጻሚነት ያለው መሆኑን አቶ አዲስዓለም ገልጸዋል።

ይህ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ደንብ፤ ያካተተው ሌላኛው ነጻ ተጠቃሚነት መኖሪያ ቤትን የሚመለከት ነው። ከዚህ ቀደም “በመታገላቸው ምክንያት” የመኖሪያ ቤት ያላገኙ “አርበኞች” “በስታንዳርድ መሠረት” በከተማ የሚሰጥ የቤት መሥሪያ ቤት ወይም በገጠር የሚሰጥ “የጎጆ መውጫ” መሬት በነጻ ማግኘት እንደሚችሉ ደንቡ ያስረዳል።

ይህ የቤት መሥሪያ መሬት በነጻ የማግኘት መብት፤ “ለተሰዉ አርበኞች” ቤተሰቦችም ተሰጥቷል። የቤት መሥሪያ መሬት የሚሰጠው በ“አርበኞቹ” ወይም በቤተሰቦቹ ምርጫ ከትግል በፊት ይኖሩበት በነበረ፣ ትግል በወጡበት አድራሻ ወይም በትውልድ አካባቢው ወረዳዎች እንደሆነ ደንቡ ላይ ተቀምጧል።

“ከፊል ቋሚ የጦር አካል ጉዳተኛ” ከሆኑ “አርበኛ” በአንጻሩ “መኖሪያ ቤት ይራቸውም አይኑራቸው” በመንግሥት ቤት ተሠርቶ እንደሚሰጣቸው ደንቡ ያስረዳል።

“አርበኞቹ ሙሉ ቋሚ የጦር አካል ጉደተኛ” ከሆኑ የጤና ባለሙያዎች “ራሳቸውን ሊንከባከቡ ይችላሉ” እስከሚሉ ድረስ “ለኑሮ የሚያስፈልግ አቅርቦት እና መኖሪያ” በመንግሥት ይቀርብላቸዋል።

የመብት እና ተጠቃሚነት ደንቡ፤ “አርበኞች” የመሥሪያ እና የመሸጫ ቦታ ማግኘት እንደሚችሉም ደንግጓል። “አርበኞች” በአገር ውስጥ እና “እንደ ሁኔታው” በውጭ አገር ነጻ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስፍሯል። ይህ ተጠቃሚነት “እንደ ሁኔታው” “ለተሰዉ አርበኞች” ልጆችም ተፈጻሚ እንደሚሆን ተመልክቷል።

በገጠር “የመሬት ሽግሽግ” ሲደረግም “አርበኞች” ቅድሚያ እንደሚያገኙ ደንቡ ይገልጻል። ደንቡ፤ “አርበኞች” በሌሎች ተጠቃሚነቶች ላይም “ቅድሚያ” የማግኘት መብት እንደሚኖራቸው ይገልጻል።

“አርበኞች” ለሥራ ቅጥር፣ እድገት፣ ዝውውር፣ ትምህርት እና ሥልጠና ሲወዳደሩ “የማለፊያ ነጥብ” ካገኙ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።

በክልሉ ውስጥ በሚገኙ አገልግሎት ሰጪ የመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም በቅድሚያ አገልግሎት የማግኘት መብት “ለአርበኞች” እና “ለተሰዉ አርበኞ” ቤተሰቦች ተሰጥቷል።

በተጨማሪም፤ “አርበኞች” እና “የተሰዉ አርበኞች” ቤተሰቦች “እንደ ሁኔታው በገንዘብ ወይም በዓይነት መልሶ ማቋቋሚያ” የማግኘት መብት በደንቡ ተሰጥቷቸዋል። እንዲሁም የተቸገሩ “አርበኞች” እና ቤተሰቦቻቸው ድጎማ እንደሚያገኙ ተገልጿል።

የትግራይ ክልል “ለአርበኞች” በዚህ ደንብ የተሰጣቸው መልሶ ማቋቋሚያ የማግኘት ጉዳይ የፌደራል መንግሥት ባቋቋመው የተሃድሶ ኮሚሽን ይሰጣል ተብሎ ከሚጠበቀው ተመሳሳይ ጥቅም ጋር ተመሳሳይ እንዳልሆነ የአርበኞች መብት እና ጥቅም ዳይሬክተሩ አቶ አዲስዓለም አብራርተዋል።

“[የኮሚሽኑ] ሥራ የሚሆነው አንዴ ወይም ለተወሰነ ጊዜ በዘላቂነት ሊደግፋቸውም፣ ሊያቋቁማቸውም ይችላል። ምን ያህል ሊሰጥ እንደሚችል በራሱ [የሚወሰን] ነው። [ደንቡ ላይ ያለው] ግን ያንን ታሳቢ ያደረገ አይደለም” ብለዋል።

በአዲሱ ሕግ ላይ የተቀመጡትን መብት እና ተጠቃሚነቶች የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ከጸደቀበት ሰኔ 24 ጀምሮ ተፈጻሚ መሆን እንደጀመረ አቶ አዲስዓለም ገልጸዋል።

ይሁንና ከህክምና አገልግሎት እንዲሁም ከመሬት ተጠቃሚነት ጋር የተያያዙትን ጨምሮ አንድ ጉዳዮች ሌላ ማስፈጸሚያ ሕግ እንደሚያስፈልጋቸው አስረድተዋል። እነዚህ ሕጎች እንደወጡ መብት እና ተጠቃሚነቶቹ መከበር እንደሚጀምሩም አክለዋል።

በዚህ ደንብ አማካኝነት ተጠቃሚ የሚሆኑ ግለሰቦች ቁጥራቸው “ሰፊ” እንደሆነ የገለጹት አቶ አዲስዓለም፤ ደንቡ ላይ የተካተቱት ጥቅሞች እና መብቶች “ከትግራይ ሕዝብ፣ ካለው አጠቃላይ አቅም ይበልጣል ብለን ስለማናስብ ተግባራዊነቱ ፈተና ይገጥመዋል ብለን አናስብም” ብለዋል።