ከሥራው የተባረረ ፖሊስ 37 ሰዎችን ከገደለ በኋላ በታይላንድ ድንጋጤ እና ሐዘን ሰፍኗል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በታይላንድ በሚገኝ የህጻናት ማቆያ በጦር መሣሪያ እና በስለታማ ነገር በተፈጸመ ጥቃት 37 ሰዎች ተገደሉ። ከመካከላቸውም 23ቱ ህጻናት መሆናቸው ታውቋል።
ከጥቃቱ በኋላ ወላጆች የልጆቻቸውን የመጫወቻ አሻንጉሊቶች በመያዝ በማቆያው በር ላይ ሲያለቅሱ ታይተዋል።
የቀድሞ የፖሊስ አባል ወደ ማቆያው በመግባት ነው የሁለት ዓመት ልጅን ጨምሮ 37 ሰዎችን መግደሉ ተገልጿል። ግድያው ሲፈጸም አብዛኞቹ ልጆች ተኝተው ነበር ተብሏል።
በመላው ታይላንድ ሕዝቡ ሐዘኑን እየገለጸ ሲሆን፣ የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እየተውለበለበ ይገኛል።
የ34 ዓመቱ ጥቃት ፈጻሚ ክትትል በሚደረግበት ወቅት የራሱን እና የቤተሰቡን ሕይወት ማጥፋቱን ፖሊስ አስታውቋል።
የግድያው ምክንያት ምን እንደሆነ አልተገለጸም። አደንዛዥ ዕጽ በመጠቀሙ ምክንያት ግለሰቡ ከሥራ መሰናበቱን ፖሊስ አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፕራዩት ቻን-ኦቻን ጨምሮ የአገሪቱ ንጉሥ እና ንግሥት ጥቃቱ በተፈጸመበት ስፍራ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሟቾቹ አስከሬን ኡዶን ታኒ ወደ ሚገኝ ሆስፒታል መወሰዱ ታውቋል።
የሟቾች አስከሬን ቤተሰቦቻቸው ወደሚገኙበት ፖሊስ ጣቢያ አቅንቶ ነበር። በዜናው የተደናገጡ ቤተሰቦች በህጻናት ማቆያው እስከ ምሽት ድረስ መረጃ ለማግኘት ሲጠባበቁ ታይተዋል።
ታጣቂው ሐሙስ ከሰዓት በመንገዱ ያገኛቸውን መምህር እና ወላጅ በማጥቃት ወደ ህንጻው መግባቱ ታውቋል።
አንድ የዐይን እማኝ እንደተናገረው ግለሰቡ መጀመሪያ ላይ አንዲት ነፍሰ ጡር ሠራተኛ ላይ ጥቃት በማድረስ ተማሪዎች ወደተኙበት ክፍል አቅንቷል።
ከአካባቢው ከመሰወሩ በፊት አብዛኛዎቹን መውጋቱን ፖሊስ አክሏል።
ርዕሰ መምህር የሆኑት ናንቲቻ ፓንቹም ለቢቢሲ እንዳስረዱት ልጆቹን ወደ መኝታ ክፍላቸው ከሸኙ በኋላ የተኩስ ድምጽ ሰምተዋል።
ተቋሙ 92 ልጆችን የሚያስተናግድ ቢሆንም በዕለቱ በነበረው መጥፎ የአየር ንብረት እና የተማሪዎቹ ማመላለሻ አውቶብስ በመበላሸቱ 24ቱ ብቻ ናቸው በዕለቱ የተገኙት።
በማቆያው ውስጥ ከነበሩት ተማሪዎች መካከል ከጥቃቱ አንድ ብቻ መትረፉን ርዕሰ መምህሯ ተናግረዋል።
“ይህንን አልሜውም አላውቅም. . . ቀጥሎ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም። አሁንም ምንም ማሰብ አልችልም” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከጥቃቱ በኋላ የታይላንድ ፖሊስ ግለሰቡን ለመያዝ ኅብረተሰቡ እንዲተባበረው ጥሪ አስተላለፎ ነበር። ግለሰቡ የቀድሞ የፖሊስ መኮንን እና በአደንዛዥ ዕጽ ምክንያት ባለፈው ሰኔ ወር ከሥራ መባረሩ ታውቋል።
ወደ ስፈራው ያቀኑ ፖሊሶች አስከሬኖችን ማየታቸውን ተናግረዋል።
“ግለሰቡ ወደ ስፍራው በመግባት ህጻናቱን ለማጥቃት በዋነኝነት ስለታማ ነገር ተጠቅሟል” ብለዋል የፖሊስ ኃላፊው ዳምሮንሳክ ኪቲፕራፓት።
“ወደ ቤቱ እየተመለሰ ደግሞ በመንገዱ ያገኛቸውን በጦር መሣሪያ እና በስለታማ ነገር አጥቅቷል።”
ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ ከጥቃቱ በኋላ ወደ እራሱ ቤት ተመልሶ ሚስቱን እና ወንድ ልጁን ገድሏል።
ጥቃቱን በፈጸመ ዕለት ጠዋት አደንዛዥ ዕጽ ይዞ ከመገኘት ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር። ለውሳኔም ለዛሬ አርብ ተቀጠሮ ነበር።
ታይላንድ ውስጥ የጦር መሣሪያ በስፋት ቢገኝም ተመሳሳይ ጥቃት ብዙም አይስተዋልም። በአገሪቱ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ መያዝም የተለመደ መሆኑን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ከሳምንታት በፊት ሌላ የፖሊስ መኮንን ሁለት የሥራ ባልደረቦቹን በዋና ከተማዋ ባንኮክ ውስጥ ተኩሶ ገድሏል።
እአአ በ2020 ደግሞ ናኮን ራቻሲማ በምተባል ከተማ አንድ ወታደር 29 ሰዎችን ገድሎ በርካቶችን ደግሞ አቁስሏል።












