ህወሓት የቀደመ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ አንጂ እንደ አዲስ መመዝገብ እንደማይፈልግ አስታወቀ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በፖለቲካዊ ውሳኔ የነበረው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስለት እንጂ እንደ አዲስ መመዝገብ እንደማይፈልግ የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ አማኑኤል አሰፋ ተናገሩ።

አቶ አማኑኤል ባለፈው ግንቦት ወር በምርጫ ሕጉ ላይ የተደረገው ማሻሻያ፤ “የተሰረዘውን [የህወሓት] ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል ሳይሆን በልዩ ሁኔታ እንደ አዲስ ለመመዝብ የሚያስችል ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ያጸደቀው ይህ አዋጅ፤ ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጽ ተግባር ተሳትፎ የነበረ የፖለቲካ ቡድን በፓርቲነት የሚመዘገብበትን ሂደት በዝርዝር ያስቀመጠ ነው።

የአዋጅ ማሻሻያው፤ የፖለቲካ ቡድኑ “ሕገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱ በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተረጋገጠ፣ የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል” ሲል ይደነግጋል።

ይህ ማሻሻያ ከጸደቀ ሦስት ሳምንታት በኋላ የፍትሕ ሚኒስቴር ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ “[ህወሓት] በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ እንዲችል” ጠይቆ ነበር።

ፍትሕ ሚኒስቴር በሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ፊርማ በወጣው ደብዳቤ ይህን ጥያቄ ቢያቀርብም ህወሓት ግን እንደ አዲስ መመዝገብ እንደማእፈልግ አቶ አማኑኤል ተናግረዋል።

የትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ሦስት ወራት ገደማ በኋላ የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት በምርጫ ቦርድ መሰረዙ ይታወሳል።

የትግራዩን ጦርነት ያስቆመው ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተፈረመ በኋላ የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ከፌደራል መንግሥት ጋር ንግግር መጀመሩን አቶ አማኑኤል አስታውሰዋል።

አቶ አማኑኤል “ሕጋዊ ሰውነት እንዴት እንደሚመለስ በምርጫ ሕጉ ግልጽ ስላልሆነ ተጨማሪ [የሕግ] ማዕቀፍ በማዘጋጀት የተሰረዘው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ይደረጋል የሚል ንግግር ነበር” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ያንን [የሕግ ማዕቀፍ] እየጠብቅን እያለ ማሻሻያ አዋጁ ወጣ” የሚሉት አቶ አማኑኤል፤ “ማሻሻያ አዋጁ [ግን] የተሰረዘውን [የህወሓት] ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል ሳይሆን በልዩ ሁኔታ እንደ አዲስ ለመመዝብ የሚያስችል ነው” ይላሉ።

ቃል አቀባዩ አክለውም፤ “[ማሻሻያ አዋጁ] በትጥቅ ትግል ያሉ ኃይሎች [የቀደመ] ሕጋዊ ሰውነት ይኑራቸው አይኑራቸው ምንም ታሳቢ አያደርግም። ‘የታጠቁ ቡድኖች ወደ ሰላማዊ ትግል ሲገቡ እንዴት ሆነው በተፋጠነ መንገድ ይመዝገቡ’ የሚል ሌላ አዋጅ ነው የወጣው” ሲሉ አክለዋል።

ይህ የአዋጅ ማሻሻያ፤ “የተሰረዘውን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል ሳይሆን እንደ አዲስ ለመመዝገብ የሚያስችል” መሆኑን የሚያነሱት አቶ አማኑኤል በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ንግግር መጀመሩን ጠቁመዋል።

አቶ አማኑኤል “ወደ ምርጫ ቦርድ አመልክተን በዚያ አዋጅ መሠረት እንድንስተናገድ ነው የሚፈልጉት። እኛ ወደ ምርጫ ቦርድ ቴክኒካል ወደ ሆነው ጉዳይ እንደ አዲስ ለመመዝገብ ማመልከት ሳይሆን ፖለቲካሊ የተሰረዘውን ሕጋዊ ሰውነት ለማስመለስ የሚያስችል ፖለቲካዊ ውሳኔ በሚመለከተው የመንግሥት አካል እንዲሰጠን ነው የምንፈልገው” ሲሉ የፓርቲያቸው ውሳኔ አስረድተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ የህወሓትን የአሸባሪነት ስያሜ ማንሳቱን ያስታወሱት አቶ አማኑኤል፤ “የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ምርጫ ቦርድም የተሰረዘውን ሕጋዊ ሰውነታችንን እንዲመልስ ነው የምንጠብቀው” ሲሉ አክለዋል።

አቶ አማኑኤል ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም ሁለተኛ ዙር ግምገማ በተካሄደበት ጊዜ ይኸው የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት ጉዳይ መነሳቱን ጠቅሰዋል።

በዚህ ግምገማ ላይ፤ “ህወሓት እንደ አዲስ መመዝገብ ሳይሆነ የነበረው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለሰት ነው መደረግ ያለበት” የሚል ሃሳብ መነሳቱን ጠቁመዋል።

አቶ አማኑኤል አክለውም ይኼንኑ ጉዳይም እስከ ሚቀጥለው ኅዳር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመነጋገር እልባት አንዲያገኝ “አቅጣጫ መቀመጡን” ገልጸዋል።

አቶ አማኑኤል “በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ህወሓት የተሰረዘው ሕጋዊ ሰውነቱ ይመለስለታል። ስለዚህ ወደነበረበት ይመለሳል ነው አስተሳሰቡ። ምርጫ ቦርድ ደግሞ ሕግ የለም እንደዚያ የሚፈቅድልኝ ሕገ የለም ብሎ ነበር። ሕግ ሲወጣ ግን በዚያ መንፈስ አልወጣም ነው እያልን ያለነው” ሲሉ ከሕጋዊ ሰውነቱ ጋር በተያያዘ ያለውን ጉዳይ አብራርተዋል።