በብራዚል ባሕር ዳርቻ ያሉ ሻርኮች ኮኬይን ተገኘባቸው

በብራዚል ባሕር ዳርቻ ያሉ ሻርኮች በተደረገላቸው ምርመራ ሰውነታቸው ውስጥ ኮኬይን መገኘቱን ተመራማሪዎች ገለጹ።

የባሕር ተመራማሪዎች 13 ሻርፖንስ በመባል የሚታወቁ ሻርኮች ላይ ምርመራ አድርገዋል። እነዚህ የዓሣ ዓይነቶች በሪዮ ደ ጀኔሮ ባሕር ዳርቻ አቅራቢያ የተገኙ ናቸው።

በጡንቻቸው እና ጉበታቸው ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ኮኬይን እንደተገኘም ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም በሌሎች የባሕር ውስጥ እንስሳት ላይ ከተገኘው የኮኬይን መጠን ጋር ሲነጻጸር ይሄኛው በ100 እጥፍ እንደሚልቅ ተገልጿል።

ኦስዋልዶ ክሩዝ ፋውንዴሽን በተባለ ተቋም የተሠራው ጥናት በሻርኮች ሰውነት ውስጥ ኮኬይን ሲገኝ የመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ኮኬይን በሻርኮቹ ሰውነት ውስጥ ሊገኝ የቻለው ከሕገ ወጥ አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች የኮኬይን ማምረቻ ቤተ ሙከራ ተረፈ ምርት ወይም ኮኬይን ከሚጠቀሙ ሰዎች አይነ ምድር ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

ተመራማሪዎቹ እንዳሉት ሕገ ወጥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ኮኬይን ባሕር ውስጥ ጥለው ወይም ጠፍቶባቸው ሊሆን የሚችልበት ጠባብ ዕድል አለ።

በፓሊቴክ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሊሪያ ውስጥ በሚገኘው የማሪን ኤንድ ኢንቫይሮመንታል ሳይንስ ሴንተር ውስጥ ባለሙያ የሆነችው ሳራ ኖቪያስ ለሳይንስ መጽሔት እንዳለችው ይህ ግኝት “በጣም ጠቃሚና እጅግ አሳሳቢ” ነው።

ምርመራ የተደረገባቸው ሁሉም ሻርኮች ነፍሰ ጡር የነበሩ ሲሆን፣ በሰውነታቸው ውስጥ የተገኘው ኮኬይን ጽንሳቸው ላይ ምን ተጽዕኖ እንዳሳደረ ገና አልታወቀም።

ኮኬይን የሻርኮችን ባህሪ እየለወጠ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ለማወቅ ተጨማሪ ምርምሮች መደረግ አለባቸው።

ሆኖም ግን ከዚህ ቀደም የተሠሩ ጥናቶች እንደሚጠቀሙት አደንዛዥ ዕፆች ሰዎች ላይ ያላቸው ተጽዕኖ በእንስሳት ላይም እንደሚስተዋል ጠቁመዋል።

አምና በኢንግላንድ ባሕር ዳርቻ የተሠራ ጥናት እንዳሳየው ውሃው ውስጥ ቤንዞሊክጎይን የተባለው ንጥረ ነገር ተገኝቷል። ይህ ንጥረ ነገር ሰዎች ኮኬይን ከወሰዱ በኋላ ከጉበት የሚመነጭ ኬሚካል ነው።