በሰሜን ጎጃም የፋኖ ታጣቂዎች ፈጸሙት ስለተባለው ማሰቃየት እና ግድያ እስካሁን የምናውቀው

በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ ሜጫ ወረዳ በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም. ‘ከመንግሥት ጋር ስብሰባ ተቀምጠው ነበር’ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪዎች በታጣቂዎች ማሰቃየት እና ግድያ እንደተፈጸመባቸው ነዋሪዎች እና የዞኑ አመራሮች ተናገሩ።

ገርጨጭ (መሀል ገነት) በተባለው የወረዳው ከተማ 16 ሰዎች ከመንግሥት ጋር ‘የሰላም ጉባኤ’ ተሰብስበዋል በሚል “ተጠርጥረው” በፋኖ ኃይሎች ተይዘው፣ ተንበርክከው እንዲጓዙ ከተደረገ በኋላ አራቱ ሲገደሉ፤ ቀሪዎቹ በታጣቂዎቹ መታሰራቸውን ቢቢሲ ለቀናት ባደረገው ማጣራት ለመረዳት ችሏል።

አንድ የአካባቢው ነዋሪ ተጎጂዎቹ “እንደተጠረጠሩበት ጉዳይ” ሳይሆን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትን በሚመለከት ሥልጠና ላይ ለመገኘት ወደ ክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር ደርሰው ሲመለሱ ጥቃቱ እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ የጥቃቱ ሰለባዎች ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም. በዞን ደረጃ አለ በተባለ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ላይ በተዘጋጀ መርሃ ግብር የአሠልጣኞች ሥልጠና ላይ ከተሳተፉ በኋላ ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ማንገላታት እና ግድያ እንዳጋጠማቸው ገልጸዋል።

አንድ ዓመት ለሚሆን ጊዜ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኙት የፋኖ ታጣቂዎች አካባቢውን ለረጅም ጊዜ ተቆጣጥረውት እንደሚገኙ ቢቢሲ ከነዋሪዎቹ ተረድቷል።

ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ነገር አጋጥሞ እንደማያውቅ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ በአካባቢው የተከበሩ ናቸው በሚባሉት የሃይማኖት አባት፣ ሽማግሌዎች እና ሴቶች ላይ የተፈጸመው ድርጊት በእጅጉ አሳዝኗቸዋል።

ቢቢሲ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ የሆኑትን እና በስፋት የተዘወወሩትን ምሥሎች እንዲሁም የክልሉ መስተዳደር ያወጣውን መረጃ መሠረት በማድረግ የክስተቱን ዝርዝር ሁኔታ ለመረዳት ለቀናት የቆየ ጥረት አድርጓል።

ለመሆኑ በግለሰቦቹ ላይ ስቃይ እና እንግልት እንዲሁም ሞት ምክንያቱ ምንድን ነው? ተሳተፈውበታል የተባለውስ ስብሰባ በማን የተዘጋጀ ነበር? መረጃውስ ከየት መጣ? የቀሩትስ ሰዎች ዕጣ ፈንታ ምን ሆነ? ለሚሉት ጥያቄዎች ቢቢሲ ምላሽ አግኝቷል።

ስብሰባው በማን ተዘጋጀ? ዓላማውስ?

ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ነዋሪዎች ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ተሳትፈው ነበር የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ ነገር ግን ግለሰቦቹ የታደሙበት ስብሰባ ከዚህ የተለየ መሆኑን ቢቢሲ ከነዋሪዎች እና ከስብሰባው አዘጋጆች ለመረዳት ችሏል።

ሥልጠናውን ያዘጋጀው ‘አምሬፍ ኽልዝ አፍሪካ’ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲሆን፣ ቆይታውም የግማሽ ቀን ነበር። የሰበሰባው ዓላማም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከል ላይ ያተኮረ ሥልጠና እና ውይይት እንደነበር አዘጋጁ ለቢቢሲ አረጋግጧል።

ባለፈው አርብ ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም. ባሕር ዳር ላይ በተካሄደው ሥልጠና ላይ የተሳተፉት ሰዎች በሙሉ በጊዜ ሥልጠናውን አጠናቀው “በሰላም ወደመጡበት ተመልሰዋል” ያለው አዘጋጁ የተሳታፊዎቹን ማንነት ከመግለጽ ተቆጥቧል።

መንግሥታዊ ባልሆነው በጤና ጉዳዮች ላይ በሚሠራው በዚህ ድርጅት በተዘጋጀው ሥልጠና ላይ የተሳተፉት በአካባቢያቸው ተሰሚነት ያላቸው ሴቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ናቸው።

ነገር ግን በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የፋኖ ቡድን ነዋሪዎቹ በመንግሥት በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል በሚል ጥርጣሬ ለጥቃት መዳረጋቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

እንግልት በሕዝብ ፊት

ከባሕር ዳር ወደ ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ ሜጫ ወረዳ የተመለሱት የሥልጠናው ተሳታፊዎች በአካባቢያቸው የጠበቃቸው ግን ያላሰቡት ነገር እንደሆነ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ይህም የታደሙበት ስብሰባ በመንግሥት የተዘጋጀ ነው በሚል በሥልጠናው ላይ የነበሩትን ግለሰቦች በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የፋኖ ቡድን ጥርጣሬ ውስጥ አስገብቷቸዋል።

“የተጠረጠሩት ግለሰቦቹ” ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው ከተመለሱ በኋላ በታጣቂዎቹ ከየቤታቸው ተይዘው እንዲሰባሰቡ ተደረገ። በሕዝብ ፊትም ረጅም ርቀት ባለው መንገድ ላይ በሚያዋርድ እና በሚያሰቃይ ሁኔታ ተንበርክከው እንዲጓዙ ስለመገደዳቸው አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ፋኖ ብልጽግና ሰብስቧቸው ነበር ብሎ አገታቸው [አሰራቸው]” ሲሉ ክስተቱን የገለጹት ሌላ ነዋሪ፤ እርምጃው “ቅጣት ይሁን ማስተማሪያ አላወቅሁም” ብለዋል።

ክስተቱን በሚያሳየው እና በማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጾች በተጋራው ተንቀሳቃሽ ምሥል ላይ፤ አራት ሴቶች እና 12 ወንዶች በአጠቃላይ 16 ሰዎች ተንበርክከው እንዲጓዙ ሲገደዱ ታይተዋል።

“ሥርዓቱ የፈጠረው ምስለኔ ካውንስል ሰብስቧቸው የቆዩ ባንዳዎች በዚህ መልኩ አቀባበል ተደርጎላቸዋል” በሚል ርዕስ የወጣው ምሥል ሴቶች፣ ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶችን በሕዝብ ፊት ተንበርክከው ሲጓዙ ያሳያል።

ቢቢሲ መነጋገሪያ ስለሆነው ክስተት በአካባቢው የሚንቀሳቀሰውን የፋኖ ቡድን በማናገር ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳክም።

የተከተለው ግድያ

የሰሜን ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ጥላሁን በታጣቂዎቹ ማሰቃየት እና ጥቃት የተፈጸመባቸው ነዋሪዎች ከመንግሥት አካላት ጋር ስብሰባ አድርገዋል በሚል በታጣቂዎቹ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“ሰዎቹ የሰላም ጉባኤ ተሳታፊ ሆነው ከመንግሥት ጋር ሲመክሩ እንደነበር አድርገው በመገንዘብ 17 የስብሰባውን ተሳታፊዎች አምበርክከው ነው ወደ ቅጣት የወሰዷቸው” ብለዋል።

በተጨማሪም ከመካከላቸው አራቱን ጎድጓዲት (መገንጠያ) በሚባል ከከተማው በግምት ከሦስት እስከ አራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ስፍራ የዚያኑ ዕለት ማታ ላይ መገደላቸውን እና አስከሬናቸው በማግስቱ ማክሰኞ ጠዋት መገኘቱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“‘ይህን ያየህ ተቀጣ እያሉ፣ ባንዳ እያሉ፣ ወንድማችንም ቢሆን አንምርም’ እያሉ መልሰው እስር ቤት ካስገቧቸው በኋላ አራቶቹን ማታውን ወስደው ረሸኗቸው” ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

በታጣቂዎቹ በተወሰደ እርምጃ የተገደሉት ሦስት ወንዶች እና አንዲት ሴት እንደሆኑ ነዋሪዎች እና የአካባቢው አስተዳደር ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በታጣቂው ቡድን ተይዘው ከነበሩት ሰዎች መካከል ተለይተው ስለተገደሉት ዝርዝር መረጃ እና ምክንያቱን ለማወቅ ቢቢሲ ያደረገው ጥረት ይህ ነው የሚባለ ተጨባጭ መልስ አላስገኘም።

በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የፋኖ ኃይሎች እጅ ነበሩ የተባሉት ነዋሪዎቹ ከተያዙ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ አራቱ “በግፍ ተገድለዋል” ያሉት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ጥላሁን፤ አስተዳደራቸው ስለ አገዳደላቸው ዝርዝር መረጃ እንደሌለው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ነገሩ ያሳዝናል” ሲሉ ስለ ግድያው እና እስራቱ የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ በፋኖ እጅ ነበሩ የተባሉ 13ቱ ሰዎች ከቀናት እስር በኋላ ረቡዕ ዕለት መለቀቃቸውን ተናግረዋል።

ሌላ የአካባቢው ነዋሪ ተይዘው የነበሩት ሰዎች መለቀቃቸውን አረጋግጠው፤ ነገር ግን ገንዘብ ከፍለው እንደተለቀቁ ከሰዎች መስማታቸውን ገልጸዋል።

ስለተገደሉት ሰዎች ነዋሪዎች የሚሉት

በታጣቂዎቹ የተገደሉት ሰዎች “የአካባቢው ዐይን ናቸው። በወረዳውም በክልል ደረጃም የሚታወቁ ሰዎች ነበሩ። የልማት አርበኛ የነበሩት” በማለት ስለ ሟቾቹ ማንነት የተናገሩት አንድ ነዋሪ፤ ቀብራቸውም ማክሰኞ ዕለት ገርጨጭ ጊዮርጊስ በተባለ ቤተ ክርስቲያን መፈጸሙን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት ማክሰኞ ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ክስተቱን “ጭካኔ የተሞላበት” ሲል የገለጸው ሲሆን፤ በፋኖ ኃይሎች ተገደሉ ያላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝርም ይፋ አድርጓል።

የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መርጌታ ግሩም፣ አቶ አዘነ አድማሱ፣ አቶ አስማማው አቤ እንዲሁም ወ/ሮ የኔአየሁ ዳኛው የተባሉ የከተማው ነዋሪዎች እንደተገደሉ አስታውቋል።

አስተዳዳሪው ስለ ተገደሉት ሰዎች ማንነት ሲያብራሩ “በሕዝብ ተቀባይነት ያላቸው እና ሕዝቡም ይወክሉናል” ብሎ የሚያስባቸው ናቸው ብለዋል።

“ትግል ማለት ውሃ ሙላት ነው፤ ያገኘውን ይበላል። ቢያንስ ማኅበረሰቡ ለምን? እንዴት ብሎ ይጠይቃል የሚል ሀሳብ ነበረኝ” ሲሉ ክስተቱን የገለጹ አንድ ነዋሪ፤ ጥቃቱ በተሳሳተ መረጃ ምክንያት ተፈጽሟል የሚል እምነት አላቸው።

“ባልተጣራ ነገር እውነት ነው ብለው ግርግር ፈጠሩ።. . . የዋሉበት በደንብ ቢጣራ ኖሮ [ግድያው እና እገታ ] ይህ ላይፈጸም ይችል ነበር” ብለዋል።

“ምን ሰይጣን እንደገባብን ግራ ገብቶኛል። እነዚህን ሰዎች ለማስበላት ሴራውን የሠራው ሰው እግዚአብሔር የእጁን ይስጠው። ሴራ ነው የሰሩብን። ጥፋቱን የፈጠረው ቧልተኛው ነው” የሚሉት የአካባቢው ነዋሪ በክስተቱ ሁሉም ማዘኑን ተናግረዋል።

“‘ብልጽግና ወስዶ እንዲህ አድርጎ አወያያቸው፤ እንዲህ አድርገው አገር ሽጠው ገቡ’ ብሎ ቧልት የነገራቸው ሰው ነው” ለተፈጸመው ማሰቃየት እና ግድያ ጣታቸውን በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች ይልቅ ሐሰተኛ መረጃ ሰጥተዋል ወዳሏቸው “ጠቋሚዎች” ቀስረዋል።

የተፈጠረው ሐዘን እና ስጋት

በቅርቡ የተቋቋመው ሰሜን ጎጃም ዞን ካሉት 10 ወረዳዎች ውስጥ አንዱ ሆነው በደቡብ ሜጫ ወረዳ፤ በመንግሥት እና በፋኖ ኃይሎች መካከል የትጥቅ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ወረዳው ለረጅም ጊዜ በፋኖ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ይገኛል።

አካባቢውን አንድ ዓመት ገደማ ፋኖ ባዋቀረው ‘ሕዝባዊ ኮሚቴ’ እያስተዳደረው ነው ያሉት ነዋሪዎች፤ ከዚህ ቀደም እንደዚህ ዓይነት ችግር አጋጥሞ እንደማያውቅ በመጥቀስ በተፈጠረው ነገር ነዋሪው እንደተደናገጠ ገልጸዋል።

“ሌባ የለ፤ ድብደባ የለ፤ ወንጀል የለ፤ ጸጥ ለጥ ያለ አስተዳደር ነበር የነበረው። ኮሽ የምትል ነገር የለችም ነበር። አሁን ግን መቼም አጥፊ እና ጠፊ ባለ ቀጠሮ ነው፤ ይህ ነገር ተፈጸመ” ያሉት ሌላ ነዋሪ፤ “አቀነባባሪ” ያሏቸው ሰዎች የተሳሳተ መረጃ በመስጠታቸው ጥቃቱ ተፈጽሟል ብለዋል።

የዞኑ አስተዳዳሪም “እንደዚህ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እና ጦርነት በአካባቢው ሳይኖር እንዲሁ በጥርጣሬ [በፋኖ] እርምጃ ሲወሰደ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ይመስለኛል” ብለዋል።

አካባቢው አሁንም በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር እንደሆነ የተናገሩት ነዋሪዎች፤ በአካባቢው ታዋቂ ሰዎች ላይ ማሰቃየት እና ግድያ መፈጸሙን ተከትሎ ስጋት ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ጥላሁን በበኩላቸው ታጣቂዎቹ “ተጨማሪ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል በሚል ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት የተፈጠረ ሲሆን፣ በአካባቢው ማኅበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና ስብራት፣ ፍራቻ፣ አካባቢውን የመልቀቅ” ሁኔታ መኖሩን አመልክተዋል።

ቢቢሲ በአካባቢው የተፈጠረውን ሁኔታ ከነዋሪዎች እና ከዐይን እማኞች ለመረዳት ለቀናት ባደረገው ጥረት ውስጥ ወደ 15 የሚጠጉ ሰዎችን ያነጋገርን ቢሆንም አብዛኞቹ የደኅንነት ስጋት እንዳለባቸው በመግለጽ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ቢቢሲ ከእስር ተለቀዋል ከተባሉት ሰዎች መካከል የተወሰኑትን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ካሉበት ፍርሃት እና ስጋት የተነሳ ምንም ነገር መናገር እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።

በዚህ ዘገባ ውስጥ የተካተቱት ነዋሪዎችም ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እና ማንነታቸውን የሚያመለክቱ ነገሮችን እንዳንጠቀም በመጠየቃቸው ስም አልጠቀስንም።