መንግሥት እና ህወሓት በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ላይ ለምን መስማማት አልቻሉም?

የአፍሪካ ኅብረት አገራት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሲገቡ ጣልቃ በመግባት ሰላም ማስከበር የጀመረው ቡሩንዲ በተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት ነው።

በርካታ የአህጉሪቱ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ በኋላም ቢሆን ጦርነት አልተለያቸውም። ይህም ኅብረቱን እረፍት አልባ ያደረገው ይመስላል።

በሱዳን፣ በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በኡጋንዳ እና በሌሶቶ ጎሳ ተኮር ግጭቶች፤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ እንዲሁም በካሜሩን እና በናይጄሪያ ደግሞ ድንበር ተኮር ግጭቶች አይተናል።

ነገር ግን በእነዚህ ግጭቶች የአፍሪካ ኅብረት ሰላም ለማምጣት ከመሞከር ባለፈ እንደ ቡሩንዲው ስኬታማ የሚባል ሥራ አልሠራም።

የሰላምና ፀጥታ ተንታኞች የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካን ግጭት ችላ ይላል፤ የአፍሪካ ኅብረት ደግሞ አቅም የለውም ሲሉ ይተቻሉ።

ከዐበይት ዓላማዎቹ አንዱ ሰላም ማስከበር የሆነው የአፍሪካ ኅብረት ግጭቶች በድርድር እንዲፈቱ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ የጦር ኃይል በማሰማራት ሰላማዊ ዜጎች መብታቸው እንዳይጣስ ቢሞክርም አህጉሪቱ አሁንም የግጭት ማዕከል ናት።

አይኤስአይኤስ አፍሪካ የተሰኘው የፀጥታ ጥናት ተቋም በፈረንጆቹ 2022 ባወጣው ዘገባ አሁንም አፍሪካ ውስጥ ያልበረዱ ግጭቶች አሉ ይላል።

የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ ያለውን የእርስ በርስ ግጭት በድርድር እንዲፈታ እንደሚሻና ለማደራደር ዝግጁ እንደሆነም ሲናገር ቆይቷል።

ነገር ግን ማዕከላዊው መንግሥትና ህወሓት በአፍሪካ ኅብረት ጉዳይ ከስምምነት የደረሱ አይመስልም። ይህ ለምን ሆነ?

የመንግሥት እና የህወሓት ፍላጎት

የጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከህወሓት ኃይሎች ጋር የገባውን ጦርነት በድርድር ለመፍታት በሚል የሚወክሉትን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይፋ አድርጓል።

ህወሓት ምንም እንኳን ተወካዮቹን ይፋ ባያደርግም ለድርድሩ ተወካዮቹን ለመላክ ዝግጁ መሆነ ገልጧል።

በሁለቱ ኃይሎች መካከል የሚደረገውን ድርድር የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ ተወካዮች በተገኙበት የአፍሪካ ኅብረት እንደሚመራው ተገልጧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ድርድሩን የአፍሪካ ኅብረት እንዲመራው ቢሻም፣ ህወሓት ግን ከኅብረቱ ይልቅ የኬንያ መንግሥት ድርድሩን እንዲመራ ይፈልጋል።

የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪ ሆኖ እንዲቀርብ እንደሚሻ ገልጠዋል።

የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም “መንግሥት ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት በኩል እንዲቀጥል ፅኑ ፍላጎት አለው” ብለዋል።

ሁለቱ የግጭቱ ተሳታፊዎች በአፍሪካ ኅብረት ጉዳይ ከስምምነት አለመድረሳቸው ድርድሩ ስኬታማ እንዳይሆን ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት ጭሯል።

መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪካ ኅብረት ከዚህ በፊት ሦስት የቀድሞ ፕሬዝዳንቶችን አጭቶ በመንግሥትና በህወሓት መካከል ያለውን ግጭት እንዲፈቱ ቢሞክርም አልተሳካለትም።

የቀድሞዎቹ የሞዛምቢክ መሪ ዮዋኪም ቺሳኖ፣ የላይቤሪያዋ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ እና የደቡብ አፍሪካው ክጋሌማ ሞትላንቴ ግጭቱን ለማብረድ ያደረጉት ጥረት አልተሳካም።

ከሦስቱ አሸማጋዮች በኋላ ወደ ማደራደሩ የመጡት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከመቀለ አዲስ አበባ ተመላልሰው በአማፂያኑና በመንግሥት መካከል ያለውን ውጥረት ለማብረድ ጥረዋል።

ህወሓት እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መንግሥት የሚያደርጉት ድርድር መቼና የት እንደሚሆን በግልፅ ባይታወቅም በሚቀጥለው ወር ሊሆን እንደሚችል የአሜሪካ ባለሥልጣናት ገልጠዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት የሚመራ ድርድር እንደሚሻ ሲገልጥ፣ ህወሓት በበኩሉ ድርድሩ በጎረቤት ሃገር ኬንያ መሪነት ናይሮቢ ላይ እንዲካሄድ ይሻል።

የህወሓት መሪዎች የአፍሪካ ኅብረትን አደራዳሪነት በተመለከተ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።

ህወሓት እና መንግሥት በኅብረቱ አደራዳሪነት ለምን አይስማሙም?

ሁለቱም የየራሳቸውን ምርጫ ማስቀመጣቸው በምክንያት ነው የሚሉት ኤርትራዊው የኩንስ ዩኒቨርሲቲው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ዓወት ተወልደሚካኤል ናቸው።

“ማን የተሻለ የእኔን ጥቅም ያስከብርልኛል የሚል እምነት ስላላቸው ነው” ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

“የአፍሪካ ሕብረትም ሆነ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ ለኢትዮጵያ መንግሥት ቀረቤታ አላቸው የሚል ክስ ከትግራይ ኃይሎች ይሰማል። ይህ የሆነው ኅብረቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚስማማ አቋም ይዞ መቆየቱን ማየት እንችላለን።”

በፈረንጆቹ ታኅሣሥ 2020 በጂቡቲው የኢጋድ 38ኛው ጉባዔ ላይ የተገኙት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሕማት የኢትዮጵያ መንግሥት እየወሰደ ያለው “የሕግ የበላይነት የማስከበር ዘመቻ” የኢትዮጵያን ሕገ-መንግሥት ከአደጋ የመጠበቅ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ህወሓት በተደጋጋሚ ባወጣቸው መግለጫዎች የአፍሪካ ኅብረት የሚጠበቅበትን ከመወጣት ይልቅ ዝምታን መርጧል የሚል ስሞታ አሰምቷል።

የአፍሪካ ኅብረት ድርድሩን እንዲመሩ የሰየማቸው ግለሰብ የኅብረቱን አቋም እንዲያንፀባርቁ ይጠበቃል ይላሉ ምሁሩ።

“ኦባሳንጆ እንዲህ ናቸው፤ እንዲያ ናቸው ብሎ መፍረድ አግባብ አይደለም። ኦባሳንጆ ምን ለውጥ ያመጣሉ የሚለውን ዕድል ስንሰጣቸው ነው የምናየው።”

ፕሮፌሰር ዓወት እንደሚሉት ጦርነቱን በድርድር ለመፍታት ሲሞክሩ የነበሩ አገራት የፈጠሩት ክፍተት አለ።

“አደራዳሪ ልሁን የሚል ሲበዛ በጦርነት ውስጥ ላሉ ተፋላሚዎች ‘ይኼኛው አያዋጣኝም፤ ይኼኛው ይሻለኛል’ የሚል ዕድል ነው የሚሰጣቸው።”

የምሥራቅ አፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አብዱራህማን ሰኢድ አቡአ ሽም በበኩላቸው፣ ሁለቱም ኃይሎች “ከጦርነት በኋላ አረፍ አሉ እንጂ ለድርድር የሚሆን ዝግጅት አላደረጉም” ይላሉ።

“ጦርነቱ በአንደኛው ኃይል አሸናፊነት ስላልተቋጨ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እየበረታ የመጣውን ጫና ተከትሎ ነው ወደ ድርድር ለመግባት የወሰኑት እንጂ ወደው የገቡበት አይመስለኝም።”

አብዱራህማን እንደሚሉት የትግራይ ኃይሎችና መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት ጉዳይ ከስምምነት አለመድረሳቸው የድርድሩን ስኬታማነት ጥያቄ ላይ ይጥለዋል።

አክለውም ሁለቱም አካላት ወደ ሰላም ድርድር ሲገቡ ከውይይት የሚያገኙትን ጥቅም በግልፅ ማስቀመጥ እንዳለባቸው ይመክራሉ።

ህወሓት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲጠይቃቸው የነበሩ ቅደመ ሁኔታዎችን ላላ በማድረግ ወደ ሰላም ድርድር መግባት እንደሚሻ መግለጡን የምዕራብ ትግራይ ጉዳይን በማየት መገመት እንችላለን ይላሉ።

ሌላኛው ቅደመ ሁኔታ የነበረው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ነበር፤ ይህም የፌዴራል መንግሥቱ እርዳታ እንዲገባ መፍቀዱን ተከትሎ ረገብ እንዳለ ማስተዋላቸውን ጠቅሰዋል።

“ሆኖም ግን አሁንም ሁለቱም ወገኖች ለሰላም ያላቸው ዝግጁነት ትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ነው። ህወሓት በጦርነቱ ወቅት የላቀ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነበረው። ይህም በፌዴራሉ መንግሥት ላይ ትልቅ ጫና እንዲያሳድሩ አግዞታል” ይላሉ ተንታኙ።

የአፍሪካ ኅብረት ሚና

የአፍሪካ ኅብረት በ40 ዓመት ጊዜ ውስጥ ግጭቶች በንግግር የሚፈቱባት “ሰላማዊና ደኅንነቷ የተጠበቀች አፍሪካ” መገንባትን ያልማል።

ነገር ግን አሁንም የኅብረቱ አባል አገራት በብሔር፣ በሃይማኖት እና በድንበር ምክንያት እርስ በርስ ጠብመንጃ እየተማዘዙ ይገኛሉ።

ኅብረቱ፣ አባል አገራቱ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሲገቡ አደራዳሪ ቡድን በማቋቋም ሰላም ለማምጣት ጥረት ያደርጋል።

ለምሳሌ በሱዳን ዳርፉር የተነሳውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት ያቋቋመው አደራዳሪ ቡድን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲመጣ አስችሏል።

በሶማሊያ ደግሞ ኅብረቱ ከተለያዩ የአህጉሪቱ አገራት የተውጣጡ ወታdሮችን አጣምሮ ሰላም አስከባሪ ኃይል አቋቁሟል።

አሁን ኅብረቱ ፊቱን ወደ ሰሜናዊ የኢትዮጵያ ክፍል መልሷል። ነገር ግን ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በአፍሪካ ኅብረት ጉዳይ የተስማሙ አይመስሉም።

“የትኛውም የሰላም ውይይት ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ ተደራዳሪዎች የሚቀበሉት አደራዳሪ መኖር አለበት” ይላሉ አብዱራህማን ሰኢድ።

“ሁለቱም የሚጠራጠሩት አሊያም አንደኛው የማያምነው ከሆነ ግን ልዩነቱን ያሰፋዋል እንጂ አያጠበውም።”

አብዱራህማን የአፍሪካ ኅብረት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አገራት ግጭቶች ጣልቃ ቢገባም ስኬታማነቱ ውሱን ነው ይላሉ።

“ይህ የሆነው በሁለት ምክንያት ነው። አንደኛው ኅብረቱ ያለው አቅም [ሪሶርስ] ጠንካራ አለመሆኑ፣ ሁለተኛው ደግሞ የኅብረቱ አባላት በሌሎች አገራት ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት አቋም ይዘው መቆየታቸው ነው።”

ተንታኙ እንደሚሉት ኅብረቱ ከዚህ በኋላ የምናየው ካልሆነ በቀር እስካሁን አጥጋቢ የሚባል ሥራ አልሠራም።

“የኅብረቱ ተወካይ እስካሁን ያደረጉት ጉብኝት ውጤት አላመጣም። በመሰል ውጣ ውረድ ውስጥ የሚደረግ ድርድር የመሳካት ዕድሉ የተወሰነ ነው። ነገር ግን ተዋጊዎቹ ኃይሎች ከተቀበሉ ሊሳካ ይችላል።”

አብዱራህማን እንደሚሉት ድርድሩ ጊዜ ይፈልጋል። ምክንያቱም በጦርነቱ የደረሱ ጉዳቶች መተማመን ስለሚያጠፉ ነው።

“ሁለቱም ድርድሩን አምነው ቢሳተፉበትም በጦርነቱ የተፈጠረውን ቁስል ለመፈወስ ጊዜ ያስፈልጋል። በሁለቱም በኩል መተማመን መኖር አለበት። ሳይዋጉ ያልተማመኑ፤ ከተዋጉ በኋላ ሊተማመኑ አይችሉም። ስለዚህ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል።”

የኩንስ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ዓወት በበኩላቸው፣ የአፍሪካ ኅብረት የአቅም እጥረት እንዳለበት በመጥቀስ እንዲሁም የኅብረቱ ሊቀ መንበር የሰጧቸውን አስተያየቶች ከግምት በማስገባት ኅብረቱ “ነፃና ገለልተኛ” ይሆናል ለማለት አልደፍርም ይላሉ።

“ነገር ግን ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ የኅብረቱ ተላላኪ ናቸው ማለት አንችልም። ኦባሳንጆ ያላቸውን ልምድ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለኅብረቱ አቋም ይገዛሉ ማለት የተሳሳተ ፍርድ ነው።”

ማንኛውም ወደ ድርድር የሚገባ አካል ወደ መወያያ ርዕሱ ከመዝለቁ በፊት አሸማጋዩ ማን ነው? ድርድሩ የት ነው የሚካሄደው? እንዴት ነው የሚካሄደው? በሚሉ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ከስምምነት መድረስ እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎቹ ያስረዳሉ።

“ይህ በግልጽ ካልተቀመጠ ንግግሩ ለይምሰል ነው የሚሆነው እንጂ የሆነ ግብ ለማሳካት ያለመ ሊሆን አይችልም። ሁኔታውም ሁለቱም ለሌላ ጦርነት የሚዘጋጁበት ጊዜ መግዣ ይሆናል” ይላሉ አብዱራህማን።

የኬንያ መንግሥት ሚና

በህወሓት እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ከአንድ ዓመት በላይ ሲደረግ የነበረው ጦርነት የአፍሪካ ኅብረት፣ የምዕራባውያን አገራትን እና የተባበሩት መንግሥታትን ሲያሳስብ ቆይቷል።

ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና መፈናቀል ያስከተለውን ግጭት ለማስቆም ተሳትፎ ያደረጉ አካላት ብዙ ቢሆኑም የአሜሪካ መንግሥት፣ የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ኅብረት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

‘የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት’ በሚለው መርኅ የሚታወቀው የአፍሪካ ኅብረት ለሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መፍትሔ ያመጣሉ ሲል የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት በአሸማጋይነት የላከው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ነበር።

ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ግጭቱ እንዲቆምና የተኩስ አቁም ውይይት እንዲደረግ መቀለ የገቡ የመጀመሪያው ልዩ መልዕክተኛ ነበሩ።

ኦባሳንጆ በተደጋጋሚ ከትግራይ እና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው የመወያየት ዕድልን አግኝተዋል።

ነገር ግን አሁንም ድረስ የተፈለገውን ግብ ማሳካት ቀላል አልሆነላቸውም።

ሌላኛዋ ለዚህ የእርስ በርስ ጦርነት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠችውና ተፅዕኖ ስታደርግ የነበረችው አሜሪካ፣ ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሦስት የተለያዩ ልዩ መልዕክተኞችን ሾማለች።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦባሳንጆ እንዲሁም የጎረቤት አገር ኬንያ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ተገናኝተው መክረዋል።

አሜሪካ በተናጠል ሰላም እንዲወርድ ግፊት ብታደርግም በቀጥታ የሰላም ድርድር ውስጥ ሚና አልነበራትም።

አሁን የፌዴራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች ለድርድር መዘጋጀታቸውን ይፋ ቢያደርጉም ድርድሩ የትና በማን አሸማጋይነት እንደሚካሄድ ግለፅ አይደለም።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረትን፤ ህወሓት ደግሞ የኬንያ መንግሥትን ዋነኛ ምርጫቸው አድርገዋል።

ባለፈው ጥር ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኙ አወል አሎ (ዶ/ር) ከአንድ ዓመት በላይ ላስቆጠረው የኢትዮጵያ እርስ በርስ ጦርነት ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማበጀት የኬንያው ፕሬዝዳንት የሚያደርጉት ጥረት የተሻለ ዕድልና ተስፋ አለው ሲሉ ገልጠው ነበር።

ኬንያ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲመጣ የምታደርገው ጥረት እንደ አሜሪካና የአፍሪካ ኅብረት ትኩረት የተሰጠው አልነበረም።

አወል እንደሚሉት የአፍሪካ ኅብረት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በተሻለ በኬንያ እየተደረገ ያለው ሙከራ ሁሉን አቀፍና ተስፋ ሰጪ ነው የሚል እምነት አላቸው።

ተንታኙ፤ የኬንያ ተነሳሽነት የአሜሪካ መንግሥት እና የአውሮፓ ኅብረትም ስለሚደግፉት የተሻለ ዕድል አለው ማለታቸው ይታወሳል።

“ኬንያ ጠንካራ የፖለቲካ መረጋጋት ያላት ጎረቤት አገር ስለሆነች ብቻ ሳይሆን፣ ባስቀመጠችው የእርቅ ሐሳብ ጭምር ነው የተሻለች አማራጭ የምትሆነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

ወደ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ የምክክር ጉባዔ የሚመራና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር ከመሠረቱ የሚፈታ አካሄድ ነው ሲሉም ገልጠው ነበር።