ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመኪና ተገጭታ በሞተች ሕንዳዊት ላይ የቀለደው አሜሪካዊ ፖሊስ ከሥራው ተባረረ
ባለፈው ዓመት በመኪና ተገጭታ በሞተች ሕንዳዊት ላይ የቀለደው አሜሪካዊ የፖሊስ መኮንን ከሥራው ተባረረ።
ፖሊሱ የሕንዳዊቷ ተማሪ ሕይወት “ውስን ዋጋ” ነው ያለው በማለት በመዘባበቱ እና በመሳለቁ ነው ከሥራው እንዲባረር የተደረገው።
ዳንኤል አውደረር የተባለው ይህ የፖሊስ መኮንን ስለ ሕንዳዊቷ ጃህናቪ ካንዱላ አሟሟት የሰጠው አስተያየት “አስነዋሪ እና አሳፋሪ” ነው ሲል የሲያትል ፖሊስ ዲፓርትመንት ማውገዙን ዋቢ በማድረግ ሲያትል ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል።
የ23 ዓመቷ ጃህናቪ በዩኒቨርስቲዋ አቅራቢያ የሚገኝ ጎዳናን እያቋረጠች እያለ ነው በሌላ የፖሊስ መኪና ተገጭታ የተገደለችው።
አደጋው ከደረሰ በኋላ ለክስተቱ ቀጥታ ምላሽ የሰጠው ይህ ፖሊስ ሟቿን “ተራ ሰው ናት” የከተማው አስተዳደር “ዝም ብሎ ቼክ ጽፎ መስጠት” ብቻ ነው ያለበት እያለ በመዘባበት ሲስቅ ተቀርጿል።
ለባልደረባው ደውሎ ይህንንም ሲናገር በሰውነቱ ላይ በተገጠመው ካሜራ ተቀርጿል።
“ሞታለች” ሲል የሚሰማው ይህ ፖሊስ በሳቅ ታጅቦ ነበር የሚናገረው።
“ተራ ሰው ናት። ቼክ ብቻ መጻፍ ነው የሚያስፈልገው” በማለት እንደገና ሳቁ ይሰማል።
“አስራ አንድ ሺህ ዶላር ብቻ ነው መከፈል ያለበት። እድሜዋ 26 ነበር። ውስን ዋጋ ነው የነበራት” ሲልም ፖሊሱ በሳቅ ታጅቦ ሲሳለቅ ተደምጧል።
ይህንን የፖሊሱን ንግግር የሚያስደምጠው ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሰፊው መጋራቱን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
በዚህ ሳምንት የሲያትል ፖሊስ ዲፓርትመንት ጊዜያዊ ኃላፊ ሱ ራህር ፖሊሱ ከሥራ መባረሩን ለፖሊስ አባላት በተላከ ኢሜይል አስታውቀዋል።
የፖሊስ መኮንኑ ድርጊት አጠቃላይ በፖሊስ መምሪያው እና በሙያው ላይ “ውርደትን” ያስከተለ ነው ሲሉም ጽፈዋል።
የፖሊሱ “ጭካኔያዊ ተግባር እና አሳፋሪ ሳቅ” እንዲሁም በሟቿ ቤተሰብ ላይ ያደረሰው ህመም ዳንኤል በባልደረቦቹ ዘንድ ያለው መልካም ስም እና ለዓመታት ማኅበረሰቡን ከማገልገሉ ጋር ሊወዳደር አይችልም ብለዋል።
“ፖሊሱ በሥራው እንዲቆይ መፍቀድ በመላው ዲፓርትመንት ላይ ተጨማሪ ውርደትን ያመጣል። በዚህም ምክንያት ከሥራው ተባሯል” ብለዋል።
ዳንኤል ከክስተቱ በኋላ ምርመራ ተከፍቶበት የነበረ ሲሆን፣ የፖሊስን የሥነ ምግባር ጉድለት የሚመረምረው ተቋም ፖሊሱ ባሳየው የሙያዊ ሥነ ምግባር ጉድለት እና አድልዎ እንዲባረር መጠየቁንም ሲያትል ታይምስ ዘግቧል።
በአደጋው የሞተችው ጃሃናቪ በሲያትል በሚገኘው ኖርዝኢስተርን ዩኒቨርስቲ የድኅረ ምረቃ ተማሪ ነበረች።