ዜሌንስኪ ከሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጦርነቱን ለማቆም ለመነጋገር ሐሙስ ዕለት ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በኢስታንቡል ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ።

ዶናልድ ትራምፕ ፑቲን በሁለቱ ሀገራት መካከል በቱርክ ቀጥተኛ ውይይት ለማድረግ ያቀረቡትን ጥሪ ዩኬሬን እንድትቀበል ከጠየቁ በኋላ ነው ዜሌንስኪ በኤክስ ገጻቸው ላይ ዝግጁነታቸውን የገለጹት።

"ግድያውን ማራዘም ምንም ፋይዳ የለውም፤ ሐሙስ በቱርክ ፑቲንን እጠብቃለሁ" ሲሉ ዜሌንስኪ ጽፈዋል።

የዩክሬኑ መሪ ቀደም ሲል አገራቸው ከሩሲያ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗን ነገር ግን የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ እንደሚሆን ተናግረው ነበር።

"የፈቃደኞች ጥምረት" እየተባለ የሚጠራውን የአውሮፓ መሪዎች ቅዳሜ በኪየቭ ከተገናኙ በኋላ የምዕራባውያን ኃያላን ጦርነቱ ከሰኞ ጀምሮ ለ30 ቀናት እንዲቆም ጠይቀዋል።

ፑቲን በቀጥታ ለመነጋገር ጥሪ ያቀረቡት ይህንን የምዕራብውያንን ጣልቃ ገብነት ተከትሎ ነበር።

እሁድ ዕለት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ዩክሬን ለዚህ ጥሪ "ወዲያውኑ" መስማማት እንዳለባት እና ጦርነቱን የሚያበቃበት መንገድ ስለመኖሩ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

"ቢያንስ ስምምነት ይቻል እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ለመወሰን ይችላሉ፤ ይህ ካልሆነ የአውሮፓ መሪዎች እና አሜሪካ ሁሉም ነገር የት ምን ላይ እንደሚገኝ ያውቃሉ፤ እናም በዚህ መሠረት መቀጠል ይችላሉ" ያሉት ትራምፕ፤ "አሁን ስብሰባው ይደረግ!" ብለዋል።

ዜሌንስኪ በኤክስ ላይ ባጋሩት ልጥፍ ሩሲያ ከንግግሮቹ በፊት የተኩስ አቁም ስምምነትን እንደምትሰጥ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

"ለዲፕሎማሲው አስፈላጊ መሰረት ለመስጠት ከነገ ጀምሮ ሙሉ እና ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም እንጠብቃለን" ሲሉ አክለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፑቲን ቅዳሜ ለሊት ባደረጉት ንግግር በ2022 ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ከወረሩ በኋላ በተጀመረው ጦርነት ላይ "ትርጉም ባለው ድርድር" እንድትሳተፍ ዩክሬንን ጋብዘዋል።

ፑቲን ውይይቱ ሩሲያ እና ዩክሬን "በአዲስ እርቅ" እንዲስማሙ ሊያደርግ ይችላል የሚለውን ነገር "ከምርጫ ውጭ አይደለም" ብለዋል።

ለ 30 ቀናት የተኩስ አቁም ጥሪ ግን በቀጥታ ምላሽ አልሰጡም ።

የሩሲያው መሪ "ይህ የዩክሬን ታጣቂ ኃይሎች አዳዲስ ትጥቅና የሰው ሃይል ካገኙ እና አዲስ ኮማንድ ፖስቶች ከተቋቋሙ በኋላ ወደ ተጨማሪ ጦርነቶች ሳይሆን የረጅም ጊዜ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የመጀመሪያው እርምጃ ይሆናል" ብለዋል።

ሞስኮ ቀደም ሲል ሩሲያ የተኩስ አቁም ስምምነት ከማድረጓ በፊት ምዕራባውያን በመጀመሪያ ለዩክሬን የሚሰጡትን ወታደራዊ እርዳታ ማቆም አለባቸው ስትል ተናግራለች።

ቅዳሜ እለት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታርመር፣ የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን፣ የጀርመኑ ፍሪድሪክ መርዝ እና የፖላንዱ ዶናልድ ቱስክ በኪየቭ አስተናግደዋል፤ በኋላም ከትራምፕ ጋር በእቅዳቸው ላይ ተወያይተዋል።

በኋላ ላይ ሰር ኬር ለቢቢሲ እንደተናገሩት የዩኤስ ፕሬዝዳንት ለአፋጣኝ የተኩስ አቁም ያቀረቡት ሀሳብ "መሟላት ያለበት ጥያቄ" ስለመሆኑ "ግልጽ ናቸው" ብለዋል።

ከዜለንስኪ ጋር በተደረገው የጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፑቲን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለ30 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት "በአየር፣ በባህር እና በመሬት" ካልተስማሙ "አዲስ እና ግዙፍ" ማዕቀቦች በሩሲያ የኃይል እና የባንክ ዘርፎች ላይ እንደሚጣሉ አስጠንቅቀዋል።

ሩሲያ እና ዩክሬን ለመጨረሻ ጊዜ ቀጥተኛ ድርድር ያደረጉት እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2022 በሞስኮ ወረራዋን ከጀመረች በኋላ ኢስታንቡል ውስጥ ነበር።

ከሦስት ዓመታት በኋላ ሁለቱም ወገኖች በመርህ ደረጃ ድርድሩን ለመቀጠል ተስማምተዋል። ግን ንግግሮች እና ስምምነት በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ሁለቱም ወገኖች እንደ ቀድሞው የተራራቁ ቀይ መስመሮቻቸውን ያቆዩ ይመስላል።