የቫግነር መሪ የቭገኒ ፕሪጎዥን በአፍሪካ ያላቸውን ተግባር እንደሚቀጥሉ ገለጹ

የቫግነር መሪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሩሲያው ቅጥረኛ ወታደሮች መሪ የቭገኒ ፕሪጎዥን ባለፈው ወር በሩሲያ ጦር ላይ ያካሄዱት አመጽ ከከሸፈ በኋላ ወደ ቤላሩስ ተሻግረዋል።

ይህንን ተከትሎ የቫግነር ቡድን ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውጉዳይ አጠያያቂ ሆኖ ቆይቷል። “አፍሪካ ውስጥ ለምናከናውነው ፕሮግራም ምንም የቀነስነው ነገር አልነበረም፣ ሊኖርም አይችልም” ብለዋል ፕሪጎዥን በቅርቡ ለአፍሪክ ሚዲያ ቴቪ በሰጡት ቃለ መጠይቅ።

ቢቢሲ ይህንን ድምጽ የፕሪጎዥን መሆኑን ለማረጋገጥ የማጣራት ሥራ ሰርቷል። በማጣሪያው መሰረትም ድምጹ የእርሳቸው ነው።

የቭገኒ ፕሪጎዥን ባደረጉት ቃለ መጠይቅ በካሜራ የሰጡት የቪዲዮ መግለጫ የለም።

አፍሪካ ሚዲያ የሚባለው አፍሪካ ውስጥ ለሩሲያ ቀረቤታ ያላቸው ፕሮግራሞችን በፈረንሳይኛ የሚዘግብ ሲሆን ከቫግነር ጋር የተያያዙ ዝግጅቶችን በብዛት ያቀርባል።

የየቭገኒ ፕሪጎዥን ወታደሮች በማሊ እና በማዕከላዊ አፍሪካ በብዛት ይገኛሉ።

በእነዚህ ይዞታቸው በርካታ ወንጀሎችን ፈጽመዋል የሚል ክስ ከተባበሩት መንግሥታት እና ከሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ይቀርብባቸዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም ከቫግነር ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል 13 ግለሰቦችና የቢዝነስ ተቋማት ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

የማዕቀቡ መነሻም በማሊ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ግርፋትና ሌሎች ወንጀሎችን በመፈጸማቸውና በሱዳን የጸጥታ ስጋት በመደቀናቸው መሆኑ ተገልጿል።

ማዕቀቡ የቫግነር የማሊ እና የማዕከላዊ አፍሪካ የኦፕሬሽን ኃላፊዎች አሌክሳንድሮቪች ማስሎቭ እና ኮንስታንቲን አሌክሳንድሮቪች ፒካሎቭን ያካትታል።

አሜሪካም በአፍሪካ አህጉር ወርቅን በሕገ ወጥ መልኩ በመጠቀም ራሳቸውን በማበልጸግ የቫግነር አባላትን ትከሳለች።

ነገር ግን የቭገኒ ፕሪጎዥን የእነርሱ ሥራ የተለየ መሆኑን ይናገራሉ።

“ሥራ በጀመርንባቸው አገራት ሁሉ በቀጣይ ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን “ ብለዋል።

“እነዚህ አገራት በሽፍቶች እና በሽብርተኞች ጥቃት የሚደርስባቸው ከሆነ በሁኔታዎች ላይ ስምምነት አድርገን ወዲያውኑ ወደ ተግባር እንገባለን” ብለዋል ፕሪጎዥን።

የቫግነር መሪ የተናገሩት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከገለጹት ጋር የሚመሳሰል ነው።

ሚንስትሩ በአፍሪካ የሚኖራቸው ዘመቻ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።