በጋምቢያ የአንድ ወር ጨቅላ በግርዛት ሳቢያ መሞቷ ከፍተኛ ቁጣ አስነሳ

የአንድ ወር ጨቅላ በግርዛት ሳቢያ መሞቷ በጋምቢያ ከፍተኛ ቁጣ አስነስቷል።

ጨቅላዋ በከፍተኛ ደም መፍሰስ ምክንያት በጋምቢያ መዲና ባንጁል ወደሚገኝ ሆስፒታል ብትወሰደም ወዲያው ሕይወቷ አልፏል።

የሞቷን ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ ቢሆንም በርካቶች ከግርዛቱ ጋር አያይዘውታል።

ውሜን ኢን ሊደርሺፕ ኤንድ ሊበሬሽን (ዊል) የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ባወጣው መግለጫ "ባህል ሰበብ አይሆንም። ወግ መከለያ አይሆንም። በቀጥታ ጥቃት ነው የተፈጸመው" ብሏል።

ፖሊስ እንዳለው ከጨቅላዋ ሞት ጋር በተያያዘ ሁለት ሴቶች ታስረዋል።

ድርጊቱ የተፈጸመበት ኮምፖ ኖርዝ አካባቢ የሕዝብ እንደራሴ አብዶሊ ሴሲይ፣ ሕጻናት ጤናቸውን ከሚያቃውስ፣ ክብራቸውን ከሚያዋርድና ሕይወታቸውን ከሚቀጥፍ አደገኛ ልማድ መጠበቅ እንዳለባቸው ጠቅሰው "የዚህች ንጹህ ልጅ ሞት መረሳት የለበትም። አገራችን ከዚህ በኋላ የምትለወጥበት ምክንያት መሆን አለበት። የሁሉንም ልጅ ሕይወት፣ ደኅንነትና ክብር መጠበቅ አለብን" ብለዋል።

ከሃይማኖትና ከባህል ጋር በተያያዘ በሚቀርቡ የተዛቡ ምክንያቶች ግርዛት በሴቶች ላይ ይፈጸማል። የሴቶችን 'ድንግልና ለመጠበቅ' በሚልና 'ለትዳር ዝግጁ' ለማድረግ የሚሉ የተሳሳቱ ምልከታዎችም ከግርዛት ጋር በተያያዘ ይነሳሉ።

ግርዛት በከፍተኛ ሁኔታ ከሚፈጸምባቸው 10 አገራት አንዷ ጋምቢያ ስትሆን፣ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 ከሆኑ ሴቶች 73% የሚሆኑት ከስድት ዓመታቸው በፊት ተገርዘዋል።

መንግሥታዊ ያልሆነው ተቋም ዊል መሥራች ፋቲ ባልዴህ ለቢቢሲ እንደገለጸችው በጋምቢያ የግርዛት መጠን እየጨመረ ነው።

"ወላጆች የሚያምኑት ሴቶች በልጅነታቸው ከተገረዙ ቶሎ እንደሚድኑ ነው። ሕጉ ስለሚከለክላቸውም ነው በለጋ ዕድሜ የሚገርዟቸው። በልጅነታቸው ከተገረዙ ለመደበቅ ይመቻቸዋል" ብላለች።

እአአ ከ2015 ጀምሮ በጋምቢያ ግርዛት ሕገ ወጥ ተድርጓል። እስከ ሦስት ዓመት እስራትና የገንዘብ ቅጣት ያስከትላል። ሴቶች ሲገረዙ ከሞቱ ደግሞ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙት ላይ እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ሊፈረድ ይችላል።

ሆኖም ግን እስካሁን ድረስ በ2023 ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው የተከሰሱት።

ግርዛት ሕጋዊ እንዲሆን ንቅናቄ የሚያደርግ ቡድን ቢነሳም በምክር ቤት ሐሳቡ ውድቅ ተደርጓል።

በመላው ዓለም ከ70 በላይ አገራት ግርዛትን በሕግ ይከለክላሉ። ሆኖም በአብዛኛው ሙስሊም በሆኑ የአፍሪካ አገራት አሁንም ድረስ ግርዛት በስፋት ይፈጸማል።