ደቡብ ሱዳን በሌላ የአፍሪካ አገር ዜጋ ምክንያት ዜጎቿ የአሜሪካ ቪዛ መከልከላቸውን ነቀፈች

ሳልቫ ኪር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሜሪካ የደቡብ ሱዳናውያንን ቪዛ መንጠቋን ተከትሎ ደቡብ ሱዳን ቅሬታዋን ገለጸች።

የሌላ የአፍሪካ አገር ዜጋን በተመለከተ ክስተት ምክንያት የደቡብ ሱዳናውያን ቪዛ በአጠቃላይ መነጠቁን ደቡብ ሱዳን ነቅፋለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላዲ ማርኮ ሩቢዮ ደቡብ ሱዳናውያን ቪዛ እንደሚከለከሉ አስታውቀዋል።

ውሳኔውን ያሳለፉት ደቡብ ሱዳን ከአሜሪካ የተባረሩ ዜጎቿን አልቀበልም ብላለች በሚል ነው።

ወደ ደቡብ ሱዳን ከአሜሪካ የተላከው ሰው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዜጋ በመሆኑ ምክንያት ግለሰቡን አለመቀበሉን የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቋል።

"ግለሰቡ ለተጨማሪ ምርመራ ወደተላከበት አገር ተመልሷል" ሲልም አስታውቋል።

ዶናልድ ትራምፕ መልሰው ሥልጣን ከያዙ በኋላ አሜሪካ ቪዛ በመከልከል የአንድን አገር ዜጎች ባጠቃላይ ዒላማ ስታደርግ ይህ የመጀመሪያው ነው።

ትራምፕ ስደተኞችን በጅምላ እንደሚመልሱ ሲዝቱ ቆይተዋል።

የደቡብ ሱዳን ዜጎች በአጠቃላይ አሜሪካ እንዳይገቡም የሚታገዱ ይሆናል።

አሜሪካ ያባረረችውን ግለሰብ ደቡብ ሱዳን ባለመቀበሏ ማርኮ ሩቢዮ የደቡብ ሱዳንን የሽግግር መንግሥት ወቅሰዋል።

"የሚተባበሩ ከሆነ በቀጣይ ውሳኔው ሊቀለበስ ይችላል" ብለዋል።

ደቡብ ሱዳን ግን የአገሯ ዜጋ ባልሆነ ሰው ምክንያት የጅምላ ውሳኔ መተላለፉን ተቃውማለች።

ግለሰቡ ኮንጓዊ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ ለአሜሪካ መላኩም ተገልጿል።

የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር ማይክል ማኩይ ሉት፣ ለኤፒ እንደገለጹት አሜሪካ "በውጥረት ውስጥ ሳለን ስህተት ለማግኘት እየሞከረች ነው"።

የደቡብ ሱዳን የመጀመሪያ ምክትል ፕሬዝደንት ሪክ ማቻር በቁም እስር መዋላቸውን ተክሎ ደቡብ ሱዳን ዳግመኛ ወደ እስር በእርስ ጦርነት እንዳትገባ ስጋት አለ።

ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር፣ ሪክ ማቻርን ነውጥ በማስነሳት ከሰዋል።

አሜሪካ ከአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞቿ ውጭ ያሉ ሠራተኞች ከደቡብ ሱዳን እንዲወጡ ባለፈው ወር ትዕዛዝ ሰጥታለች።

ከዚህ ቀደም ደቡብ ሱዳናውያን በአሜሪካ ለተወሰነ ጊዜ የሚቆዩበት ፈቃድ ነበራቸው።