በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የአፍሪካ ኅብረት የሩዋንዳ ጭፍጨፋን ለማሰብ ካዘጋጀው ስብሰባ እንዲወጡ ተደረጉ

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አቭራም ንጉሤ

የፎቶው ባለመብት, ena

የምስሉ መግለጫ, በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አቭራም ንጉሤ

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት አቭራም ንጉሤ ሰኞ ዕለት በአፍሪካ ኅብረት የሩዋንዳውን የዘር ጭፍጨፋ ለማሰብ ከተዘጋጀ ስብሰባ ላይ ተገድደው እንዲወጡ ተደረጉ።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ አምባሳደር አቭራም ንጉሤ አባል አገራት በስብሰባው ላይ አብረዋቸው ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እንዲወጡ መደረጋቸውን ጠቅሷል።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው አምባሳደሩ ከስብሰባው ተገድደው መውጣታቸውን ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማሕሙድ አሊ ዮሱፍ በስብሰባው ላይ የሰጡትን አስተያየት አውግዟል።

"በሩዋንዳ ቱትሲዎች ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋትን ለማሰብ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ተጋብዘው በተገኙት በአዲስ አበባ የእስራኤል አምባሳደር ላይ፣ ፀረ እስራኤል የሆኑ የፖለቲካ ይዘቶችን ማስተዋወቃቸው ያሳዝናል" ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ አክሎም "በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ተቀባይነት የሌለው እርምጃ ነው፤ በትልቁ ደግሞ የተጎጂዎችን መታሰቢያ ክብር የሚያሳጣ ነው። እንዲሁም የሩዋንዳን እና የአይሁድ ሕዝቦችን ታሪክ በመሠረታዊነት ካለመረዳት የመጣ ነው" ብሏል።

በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2021 እስራኤል የአፍሪካ ኅብረትን ዳግም በታዛቢነት ተቀላቅላለች።

አምባሳደር አቭራም ንጉሤ በኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ከመሾማቸው በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ፓርቲ ለሆነው ሊኩድ የሕግ አውጪ በመሆን አገልግለዋል።

የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "... ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ እንወስዳለን" ብሏል።

በየካቲት ወር 2023 የእስራኤል ዲፕሎማት የአፍሪካ መሪዎች ከተገኙበት እና በአዲስ አበባ ከተካሄደው 36ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በተመሳሳይ እንዲወጡ ተደርገው እንደነበር ይታወሳል።

ይህ የአፍሪካ ኅብረት እርምጃ የተሰማው ጋብ ብሎ የነበረው እስራኤል በጋዛ ውስጥ የምታካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ አጠናክራ በቀጠለችበት ወቅት ነው።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ50 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸው ተገልጿል።

እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሦስተኛው የጋዛ ሕንጻዎች መውደማቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።

የአፍሪካ ኅብረት አባል የሆነችው ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደው ጥቃት የዘር ማጥፋት ድርጊት ነው በሚል በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ክስ መመሥረቷ ይታወቃል።