"ካንሰር ሁላችንንም ይነካል" ፕሬዚዳንት ባይደን

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በካንሰር በሽታ መያዛቸውን ተከትሎ ከአለም ዙሪያ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቀረቡ።

ፕሬዚዳንቱ ወደ አጥንታቸው ተዛምቷል በተባለ የፕሮስቴት ካንሰር መጠቃቸውን ተከትሎ የብሪታንያው ንጉስ ቻርለስ የግል ደብዳቤን ጨምሮ ከጎንዎት ነን የሚሉ መልዕክቶች እየተዥጎደጎዱላቸው ይገኛል።

"ካንሰር ሁላችንንም ይነካል" በማለት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባይደን ሰኞ ዕለት በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስፍረዋል።

"እንደ ብዙዎቻችሁ እኔ እና ባለቤቴ ጂል የተማርነው ነገር ቢኖር በተሰበርነበት ወቅት ጥንካሬ እንደሚመጣ ነው። በፍቅር እና በድጋፋችሁ ስላነሳችሁን እናመሰግናለን" ሲሉ መልዕክታቸውን አስፍረዋል።

የባይደን ጽህፈት ቤት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ወደ አጥንታቸው ዘልቆ በተዛመተ ኃይለኛ የፕሮቴስት ካንሰር መጠቃታቸውን ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ፣ እሁድ እለት አስታውቆ ነበር።

የባይደን በካንሰር ህመም መያዛቸው የተሰማው የቀድሞው ፕሬዚዳንት በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የጤና ሁኔታቸው ላይ አዳዲስ ጥያቄዎች እየተነሱ ባለበት ወቅት ነው።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በባይደን የካንሰር ህመም መያዝ ዜና ኃዘናቸውን ቢገልጹም፤ በኋላ ላይ ግን ባይደን በስልጣን በነበሩበት ወቅት ቡድናቸው ስለ ህመማቸው ቀደም ብሎ አውቆ ዜናውን ከህዝብ ደብቆ ይሆን የሚል ጥያቄን አቅርበዋል። ትራምፕ ላነሱት ጥያቄ ምንም አይነት ማስረጃ አላቀረቡም።

"ህዝቡ ቀደም ብሎ እንዲያውቅ አለመደረጉ አስገርሞኛል። አሁን ለደረሱበት ካንሰር ዘጠኝ ደረጃ ለመድረስ በጣም ረዘም ያለ ጊዜ ይወስዳል" ሲሉ ሰኞ ከሰዓት በኋላ በዋይት ሃውስ ተናግረዋል።

ትራምፕ አክለውም "ወደዚህ የከፋ ደረጃ ለመድረስ አመታትን ሊወስድ ይችላል። በጉዳዩ በጣም አዝኛለሁ። እናም ሰዎች ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ መሞከር አለባቸው ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።

የካንሰር ህምም የከፋ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ መታወቁ አዲስ ጉዳይ አይደለም። አንድ በአውሮፓውያኑ 2014 በዩናይትድ ኪንግደም የተሰራ ጥናት እንዳመለከተው 46 በመቶ የካንሰር በሽታዎች የሚታወቁት ወደ ከፋ ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ መሆኑን አሳይቷል።

የባይደን ጽህፈት ቤት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ወደ አጥንታቸው በዘለቀ የፕሮስቴት ካንሰር መያዛቸውን አርብ ዕለት ይፋ ባደረገበት ወቅት ግሌሰን በሚባለው አመዳደብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን አክሏል።

"ይህም በሽታውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚስፋፋ ቢያደርገውም ካንሰሩ ለሆርሞን ካለው ስስነት ጋር ተያይዞ በሽታውን ለመቆጣጠር አማራጭ ሁኔታዎችን የሚፈቅድ ነው" ተብሏል።

ግሌሰን ዘጠነኛ ደረጃ ማለት ህመሙ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳይ እና ካንሰሩም በሰውነት ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት ሊሰራጭ የሚችል መሆኑን የዩናይትድ ኪንግደም የካንሰር ምርምር ተቋም አስታውቋል።

ባይደን እንዳሉት በሽንታቸው ላይ ምልክቶችን መታየታቸውን ተከትሎ በተደረገ ምርመራ በፕሮስቴት ካንሰር መጠቃታቸው ታውቋል።

በካንሰር ህመም መያዛቸውን ተከትሎ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እና የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሐሪስን ጨምሮ በርካታቸው ከበሽታቸው እንዲያገግሙ መልካም ምኞታቸውን እንዲሁም ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

የብሪታንያው ንጉስ ቻርለስ ለባይደን በግል በጻፉት ደብዳቤ መልካም ምኞታቸውን ማስተላለፋቸውን የባኪንግሃም ፓላስ አስታውቋል።

የ76 ዓመቱ ንጉስ ከባይደን ጋር ለበርካታ ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን እሳቸውም አይነቱ ባልተገለጸ የካንሰር በሽታ ህክምናቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

በዚያን ወቅትም ባይደን በበኩላቸው "ህመሙ አሳሰስቦኛል። አምላክ ከፈቀደ አነጋግረዋለሁ" በማለት መልካም ምኞታቸውን ማስተላለፋቸው በወቅቱ ተዘግቦ ነበር።

የትራምፕ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከህመማቸው እንዲያገግሙ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸው፤ እሳቸውም ቢሆን ባይደን በስልጣን በነበሩበት ወቅት የአሜሪካ ህዝብ ስለጤናቸው ግልጽ የሆነ መረጃ ነበረው ወይ? የሚል ጥያቄን አንስተዋል።

የ82 አመቱ አዛውንት ጆ ባይደን በአውሮፓውያኑ 2021 እስከ 2025 ድረስ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።