ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ እና ዩክሬን "በአፋጣኝ" የተኩስ አቁም ድርድር እንደሚጀምሩ ትራምፕ ተናገሩ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ሩሲያ እና ዩክሬን "በአፋጣኝ" የተኩስ አቁም ለማድረግ ንግግር እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።
ትራምፕ ይህን ያሉት ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ሁለት ሰዓት የዘለቀ የስልክ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ ነው።
ትራምፕ የስልክ ልውውጡን "እጅግ መልካም" ብለው የተኩስ አቁም ለማድረግ የሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች በሁለቱ ወገኖች መካከል ከስምምነት ሊደረስባቸው እንደሚገባ አሳውቀዋል።
ምንም እንኳ ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነት ሊደረስ እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው ቢናገሩም በቅርቡ ስምምነት ይፈፀማል የሚል ግምት የለም።
ትራምፕ ከፑቲን በተጨማሪ ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር ውይይት አድርገዋል።
ፑቲን ከዩክሬን ጋር ለመሥራት እና "ወደፊት የሰላም ስምምነት ለመድረስ" ዝግጁ መሆናቸውን ሲናገሩ ዜሌንስኪ በበኩላቸው "ይህ ወሳኝ ወቅት ነው" ብለው አሜሪካ ከስምምነቱ ራሷን እንዳታገል ጥሪ አቅርበዋል።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ያቀረቡትን የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ጉዳይ ችላ ብለውት አልፈዋል።
ከትራምፕ ጋር የስልክ ልውውጥ ያደረጉት ዜሌንስኪ "ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለሚደረስ ሙሉ የተኩስ አቁም ስምምነት" ያላቸውን ፍላጎት አስታውቀው ነገር ግን ሞስኮው ዝግጁ ካልሆነች "ቅጣት ሊጣልባት ይገባል" ብለዋል።
ትራምፕ ከፑቲን ጋር ካደረጉት የስልክ ልውውጥ ቀደም ብሎ ንግግር ያሰሙት ዜሌንስኪ ዩክሬንን በተመለከተ ሀገራቸው ያልተሳተፈችበት ምንም ዓይነት ውሳኔ እንዳይደረስ ጠይቀዋል።
ዶናልት ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያቸው "ሩሲያ እና ዩክሬን በአፋጣኝ የተኩስ አቁም ለማድረግ ውይይት ይጀምራሉ። ከተኩስ አቁም ስምምነት በላይ ጦርነቱን ለማስቆም ንግግር ያደርጋሉ" ብለው ይህን ጉዳይ ለዜሌንስኪ ማሳወቃቸውን ፅፈዋል።
"ይህን ለማድረግ በሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ዙሪያ ሁለቱ ሀገራት ውይይት ያደርጋሉ። ምክንያቱም ከሌላው በላይ ስለጉዳይ የሚያውቁት እነሱ ናቸው።"
ዜሌንስኪ የተኩስ አቁም ስምምነቱ "አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረትን ሊያካትት ይገባል" ይላሉ።
ትራምፕ አሜሪካ ከሩሲያ እና ዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት ራሷን እንደማታገል ቢያስታውቁም "ቀይ መስመሩን ካለፉ ግን" ከጉዳይ ራሳቸውን ሊያገሉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
አሜሪካ ከአደራዳሪነት ራሷን እያገለለች ነው የሚለውን ሐሳብ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል።
ትራምፕ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ሩሲያ እና ዩክሬን የሰላም ስምምነት ለመድረስ ቁርጠኝነት አለማሳየታቸውን አውስተው አሜሪካ ከጠረጴዛው ገሸሽ ልትል እንደምትችል ጠቁመዋል።
ትራምፕ የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን ጦርነቱ ስለሰለቻቸው ማቆም ይፈልጋሉ ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ፑቲን ከትራምፕ ጋር ያደረጉትን የስልክ ልውውጥ "ግልፅ፣ ገንቢ እና አስፈላጊ" መሆኑን ገልፀዋል።
ትራምፕ ከፑቲን ቀጥሎ ከዜሌንስኪ ጋር ባደረጉት የስልክ ልውውጥ ላይ የአውሮፓ ሕብረት ፕሬዝደንት እንዲሁም የፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን እና ፊንላንድ መሪዎች ተገኝተዋል።