"ምርጫ በመጣ ቁጥር እፈራለሁ"

ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ ሊረብሽ የሚችል ይዘት አለው

የ42 ዓመቷ ታንዛኒያዊት ሜሪያም ስታፎርድ ምርጫ በተቃረበ ቁጥር የቀደመ ቁስሏ ይቀሰቀሳል።

በሙዚቃ የታጀበ የምርጫ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደ ሜሪያም ላሉ ሰዎች የመርዶ ያህል ነው።

በሰውነት ቆዳ፣ በፀጉር እና በዐይን ሜላኒን ሳይኖር ሲቀር የሚከሰተው አልባይኒዝም (albinism) ያለባቸው ታንዛኒያውያን አገር አቀፍ ምርጫን የሚፈሩት ያለ ምክንያት አይደለም።

"በተለይ በምርጫ ወቅት አልባይኖዎች ጥቃት ይደርስብናል። ከአልባይኒዝም ጋር በተያያዘ ብዙ የጥንቆላ ዕሳቤዎች አሉ። በጣም ስለምፈራ በምርጫ ቅስቀሳ አልሳተፍም" ትላለች ሜሪያም።

ታንዛኒያውያን የፊታችን ረቡዕ ፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ ድምጽ ይሰጣሉ።

በአገሪቱ ወደ 30,000 ሰዎች አልባይኒዝም አለባቸው። የአልባይኖዎች የሰውነት ክፍሎች ሃብት፣ መልካም ዕድል እና የፖለቲካ ስኬት ያመጣል የሚል ሐሰተኛ ምልከታ ስላለ ጥቃት እና ግድያ ይደርስባቸዋል።

የፖለቲካ የበላይነት ለማግኘት በሚደረገው ፉክክር አልባይኖዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይባባሳል።

እአአ በ2008 የተካሄደው ምርጫ ለአልባይኖዎች ከመቼውም በላይ የከፋው ነበር።

ለምርጫው ቅድመ ዝግጅት እየተካሄደ ሳለ ገጀራ የያዙ ወንዶች የሜሪያምን መኝታ ክፍል ሰብረው ገቡ።

ሜሪያም የምትኖረው በታንዛኒያ ሰሜን ምዕራብ በምትገኘው ካጌራ ግዛት ነበር።

"ምሽት ላይ መጥተው ቀኝ እና ግራ እጆቼን ቆርጠው ወሰዱ። በነጋታው ሆስፒታል ስወሰድ ራሴን ስቼ ነበር። ዶክተሩ 'ሞታለች፤ ወስዳችሁ ቅበሯት' አለ።"

ሜሪያም ባልተጠበቀ ሁኔታ አገገመች። ጥቃቱ ሲደርስባት የአምስት ወር ነፍሰ ጡር ነበረች። ልጇ በሕይወት ሊተርፍ አልቻለም።

ካጌራን ጥላ ከመውጣት ውጭ አማራጭ አልነበራትም። አካባቢው አልባይኖዎች ላይ በሚደርስ ጥቃት ይታወቃል።

ሜሪያም አንጻራዊ ሰላም በሰፈነበት የኪሊማንጃሮ ግዛት ኑሮዋን እንደ አዲስ መሠረተች።

የአልባይኖዎች ሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆነው 'አንደር ዘ ሰን' ቤት ሠራላት። ሹራብ ሥራም ተማረች።

ከሰሞኑ የምርጫ ቅስቀሳ ሲደረግ ከ17 ዓመታት በፊት የደረሰባትን አስታውሷታል።

"አሁንም ድረስ በሕልሜ ይመጣል። ነቅቼ ክንዴን ስዳብስ እጄ አለመኖሩን አስታውሳለሁ። ስሜቱ መቼም አይለቀኝም።"

'አንደር ዘ ሰን' እንደሚለው ከ2008 ወዲህ አልባይኖዎች ላይ 211 ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

79 አልባይኖዎች ሲገደሉ 100 የሚደርሱት አካላቸው ጎድሎ በሕይወት ተርፈዋል።

ሁለት አልባይኖዎች እስካሁን ድረስ አልተገኙም። ከ27 መቃብሮች የሰውነት ክፍሎች ተሰርቀዋል።

የተገደሉ አልባይኖዎችን ለመዘከር በሰንጊርማ ግዛት ሐውልት ቆሟል። በዚህ ሐውልት ላይ የሜሪያም ስም ተጽፏል።

ስማቸው ከተጻፉት አንዷ በአምስት ዓመቷ የተገደለችው ማሪያሙ ኢማኑኤል ናት።

አሁን 25 ዓመት የሆነው ወንድሟ ማንያሺ ኢማኑኤል ያንን ቀን ሲያስታውስ በጥልቅ ሐዘን ይዋጣል።

"ስምንት ዓመቴ ነበር። የእህቴ እግሮች፣ እጆች እና ምላስ ተቆራርጦ አይቻለሁ። ከዛን ቀን ጀምሮ እፈራለሁ። ምርጫ በደረሰ ቁጥር ጥቃት ተፈጸመ ሲባል ያንን ቀን አስባለሁ።"

ማኅበረሰባዊ የግንባዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄዎች ቢካሄዱም ጥቃቶች ቀጥለዋል።

ያለፈው ሰኔ በሲሙዩ ግዛት ጥቃት ተፈጽሟል።

ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሁሉ ሐሰን፤ ባህላዊ ዕሳቤን የተመረኮዙ ጥቃቶች "በታንዛኒያ ምርጫ ቦታ የላቸውም" ብለዋል።

አልባይኖዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ከፍተኛ የሆነበት ግዛት አስተዳዳሪ ሰኒ ንጋጋ እንደሚሉት፤ በተለይም በገጠር የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች ይሰጣሉ።

"በቅርቡ ባህላዊ ሐኪሞችን አሰባስበን ፌስቲቫል አዘጋጅተናል። አልባይኖዎች ላይ ጥቃት እንዳይፈጸም ማኅበረሰቡን እንዲያስተምሩ መልዕክት አስተላልፈናል" ይላሉ አስተዳዳሪዋ።

የሲቪል ማኅበራት ንቅናቄ እና በትምህርት ቤቶች አልባይኖዎችን ያካተቱ እንቅስቃሴዎች መካሄዳቸው የተወሰነ ለውጥ አምጥቷል።

ሆኖም አምና የሁለት ዓመቷ አስሚዌ ኖቫታ መገደሏ ችግሩ አሁንም እንዳልተቀረፈ ያሳያል።

ሕጻኗ ከእናቷ ጋር እየተጫወተች ሳለ ነበር በሁለት ወንዶች ታፍና የተወሰደቸው።

ከ17 ቀናት በኋላ የሕጻኗ የሰውነት ክፍሎች ተቆራርጠው፣ ድልድይ ሥር አስከሬኗ ተጥሎ ተገኝታለች።

ከግድያዋ ጋር በተያያዘ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ሜሪያም የሕጻኗን ግድያ ስትሰማ የደረሰባትን ጥቃት አስታውሷታል።

"ያንን ሕመም አውቀዋለሁ። እናቷ መቼም አትረሳውም" ትላለች።

ሜሪያም ብቻዋን ከቤት አትወጣም። ሰው በተሰበሰበበት ቦታ ስትሆንም ምቾት አይሰማትም።

ረቡዕ ዕለት ድምፅ የመስጠት ፍላጎት የላትም። በሕይወቷ ላይ ለውጥ ያመጣል ብላ አታስብም።

ቀኑን የምታሳልፈው ኪሊማንጃሮ ካለው ቤቷ ሳትወጣ ነው።