የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በምዕራብ ዳርፉር የዘር ጭፍጨፋ መፈጸማቸው ተጠቆመ

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) እንዲሁም አረብ አጋሮቻቸው በምዕራብ ዳርፉር በምትገኘው ኤል ጊኔያ በተባለች ከተማ የዘር ጭፍጨፋ መፈፀማቸውን የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ተቋም ሂውማን ራይትስ ዋች አስታወቀ።

ለተፈጠረው ቀውስ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን ሦስት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ኮማንደሮችም ይፋ አድርጓል። ይህም የቡድኑ መሪ ጀነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን (ሔሚቲ) ይጨምራል።

አምና ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባሉት ወራት እንዲሁም በያዝነው ዓመት ጥቅምት ላይ በኤል ጊኔያ ከተማ አረብ ያልሆኑ ማሳሊት የተባሉ መኖሪያ መንደሮች ውስጥ ስለሚደርሱ ጥቃቶች ብዙ ሪፖርቶች ሲወጡ ነበር።

በሂውማን ራይትስ ዋች የወጣው ሪፖርት ግን እስካሁን ከወጡት ጥልቅ ይዘት ያለው ነው።

ባለፉት 11 ወራት ከ200 በላይ ሰዎችን በአራት አገራት ቃለ ምልልስ እንዳደረገላቸውና ከ120 በላይ ምሥሎች ላይ ምርመራ እንዳደረገ በሪፖርቱ ገልጿል።

በማሳሊት እና በሌሎችም አረብ ያልሆኑ ማኅበረሰቦች ላይ የደረሰው ጥቃት “ሰፊና ስልታዊ ነው” ሲል አክሏል።

ይህም ዓላማው “ቢያንስ አካባቢውን ጥለው እንዲወጡ ማድረግ” ነው ብሏል።

ሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እና የጦር ወንጀሎች “ብሔርን በማጽዳት ዘመቻ” እንደተከናወኑም ሪፖርቱ ይጠቁማል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እንዲሁም አጋሮቻቸው ማሳሊትን ቢያንስ በምዕራብ ዳርፉር "በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የማጥፋት ዓላማ" እንዳላቸው ተገልጿል።

“ይህም የዘር ጭፍጨፋ እንደተካሄደና እየተካሄደም እንዳለም ይጠቁማል” ይላል ሪፖርቱ።

ሂውማን ራይትስ ዋች ዓለም አቀፍ መርማሪዎች የጥቃቶቹን ዒላማ እንዲመረምሩም ጠይቋል።

የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችም ፈንጂ መሣሪያዎች እንደተጠቀሙ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በዚህም ንጹኃን ዜጎች እንደሞቱና እንደተጎዱ አስታውቋል።

በተጨማሪም የማሳሊት ተዋጊዎች አረብ ነዋሪዎች ላይ ግድያ፣ ዝርፊያና ብዝበዛ እንደፈጸሙ ተገልጿል።

ሁለተኛ ዓመቱን በያዘው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ለንጹኃን ዜጎች የተሻለ ጥበቃ እንዲደረግ የመብት ተሟጋች ተቋሙ ጠይቋል።

ጀነራል ደጋሎ፣ ተዋጊዎቻቸው በዳርፉር ሆነ ብለው ንጹኃን ላይ እንዳላነጣጠሩ በመግለጽ ክሱን አጣጥለዋል።

ጭፍጨፋው የተፈፀመው “በብሔር ግጭት” ሳቢያ እንደሆነም ተናግረዋል።

ሆኖም ግን የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ጀነራል ደጋሎን እንዲሁም ወንድማቸው አብደል ራሒም ሐምዳን ደጋሎ እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ምዕራብ ዳርፉር ክንፍ ኮማንደር ጆማ ባራካላህን በስም ጠቅሷል።

ታኅሣሥ ላይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ የሱዳን ጦርና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የጦር ወንጀል መፈፀማቸውን ገልጿል።

“ፈጥኖ ደራሹ ኃይልና አጋሮቹ ሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀልና ብሔር ማጽዳት ፈጽመዋል” ሲልም ከሷል።

አብደል ራሒም ዳጋሎ ላይ አሜሪካ ማዕቀብ ብትጥልም ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ላይ ግን ማዕቀብ አልጣለችም።

የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ካሪም ካሃን፣ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በሰጡት ቃል ሁለቱም ተዋጊ ኃይሎች በዳርፉር ሰብአዊነትን የሚጥሱ ወንጀሎች ፈጽመዋል።

እነዚህ ‘Rome Statute crimes’ በሚል የተገለጹት ወንጀሎች ዘር ማጥፋትን ይጨምራሉ።