ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ ውስጥ ሴቶች ከወንዶች እና ሌሎች ማንነቶች በበለጠ በማኅበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር ያስተናግዳሉ - ጥናት
ኢትዮጵያ ውስጥ በፌስቡክ፣ በቴሌግራም እና ትዊተር (ኤክስ) ላይ ሴቶች ከወንዶች እንዲሁም ከብሔር እና የሃይማኖት ማንነቶች በበለጠ የጥላቻ ንግግር ሰለባ እንደሚሆኑ መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው 'ሴንተር ፎር ኢንፎርሜሽን ሪዚሊየንስ' የተባለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ያደረገው ጥናት አመለከተ።
ቴሌግራም በተሰኘው የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ላይ የሚታዩት የጥላቻ ንግግሮች በጾታ ንጽጽር ሲደረግባቸው 96.9 በመቶው ሴቶች ላይ ያነጣጠሩ ሆነው እንደተገኙ የተቋሙ ጥናት አሳይቷል።
ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ. ም. ይፋ የተደረጉትን ሁለት ጥናቶች ያካሄደው ሴንተር ፎር ኢንፎርሜሽን ሪዚሊየንስ፤ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን፣ የሐሰት መረጃን እና በኦንላይን የሚደርሱ ጥቃቶችን መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ተቋም ነው።
ተቋሙ ይፋ ያደረጋቸው ባለ 64 እና 54 ገፅ የጥናት ሪፖርቶች በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው።
ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰነዘሩ የጥላቻ ንግግሮች ወንዶች ከሚያጋጥሟቸው የተለዩ እንደሆኑ እና በብዛትም እንደሚበልጡ በጥናቶቹ መረጋገጡ በሪፖርቶቹ ማጠቃለያ ላይ ሰፍሯል።
ሴቶች የሚያጋጥሟቸው የጥላቻ ንግግሮች “የበታች እንደሆኑ የሚጠቁሙ፣ ጾታዊ ጥቅል ፍረጃን የያዙ ወይም ምፀት (irony) እና ስላቅ” ያለባቸው እንደሆኑ ሪፖርቱ አመልክቷል።
ተቋሙ የሰራው የመጀመሪያው ጥናት ሴቶች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያጋጥማቸውን ጥቃት በተመለከተ በመገናኛ ብዙኀን እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ ከሚሰሩ 14 ሴቶች በቃለ መጠይቅ መረጃ የተሰበሰበበት ነው።
በዚህ ጥናት የተደረሰባቸው ግኝቶችን መሰረት ያደረገው ሁለተኛው ጥናት ደግሞ በፌስቡክ፣ ትዊተር እና ቴሌግራም ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች ንጽጽር የተደረገበት እንደሆነ ሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።
ሪፖርቱ እንደሚያስረዳው ንጽጽሩን ለማካሄድ ጾታ፣ ብሔር፣ ሃይማኖት እና አካል ጉዳተኝነት ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ ንግግርን ያዘሉ 2,058 የአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ እና እንግሊዘኛ ቃላት በባለሙያዎች እንዲዘጋጁ ተደርገዋል።
ሌሎች ማንነቶች ላይ ያተኮሩ የጥላቻ ንግግር ቃላት በጥናቱ ውስጥ እንዲካተቱ የተደረገው፤ ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በሌሎች ማንነቶች ላይ ከሚደርሰው ጋር ለማነጻጸር እንዲቻል በማሰብ እንደሆነ ቢቢሲ ከአጥኚዎቹ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
እነዚህን ቃላት የያዙ ልጥፎች ከሶስቱ ማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ እንደተሰበሰቡ የሚጠቅሰው ሪፖርቱ፤ ከእነዚህ ልጥፎች ውስጥ ከሰባት ሺህ በላይ ተመርጠው ትንተና እንደረተደረገባቸው ይገልጻል።
የተደረገው ትንተና ውጤት በሦስቱም የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ሴቶች ከወንዶች በይበልጥ ለጥላቻ ንግግር ተጋላጭ እንደሆኑ እንዳሳየ ሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።
ቴሌግራም ላይ ከተሰበሰቡት ጾታን መሰረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች ውስጥ 96.9 በመቶው ሴቶች ላይ ያተኮሩ እንደሆኑ ሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።
በሁለተኛ ደረጃ፤ ሴቶች ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ ንግግሮች በከፍተኛ መጠን የተገኙነት የማኅበራዊ ሚዲያ ትዊተር ነው።
ከትዊተር ላይ ከተሰበሰቡት ልጥፎች ውስጥ ወንዶች ላይ የሚያተኩሩት 17.7 በመቶው ብቻ ናቸው። 82.3 በመቶው ሴቶች ላያ ያነጣጠሩ እንደሆኑ ጥናቱ አሳይቷል ተብሏል።
ወንዶች ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ ንግግሮች ከፍ ተብሎ በታየበት ፌስቡክ፤ 40.1 በመቶው ልጥፎች ወንዶች ላይ ያተኮሩ ሆነው እንደተገኙ ሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
ይሁንና በዚህኛው የማኅበራዊ ሚዲያም ቢሆን አብላጫው 59.9 በመቶው ጾታዊ የጥላቻ ንግግር ሴቶች ላይ የተሰነዘረ ነው።
አጥኚዎቹ ጥናቱን በሚያዘጋጁበት ወቅት ለንጽጽር ከወሰዷቸው የብሔር እና ሃይማኖት ማንነቶች መካከልም ሴቶች ላይ የሚደርሰው የጥላቻ ንግግር ከፍ ያለ መሆኑን ጥናቱ እንዳሳየ በሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።
ለንፅፅር ከቀረቡት ማንነቶች ውስጥ “ሴት፣ ወንድ፣ ሙስሊም፣ ኦርቶዶክስ እና ጥቁር” የሚሉት ይገኙበታል። አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ የሚሉትም የብሔር ማንነቶች በንጽጽሩ ላይ የተካተቱ ሲሆን ሌሎች ጥቅል ማንነቶችም በአንድ ቡድን ተጠቅሰዋል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚሰነዘርባቸው የጥላቻ ንግግር ብዛት ለንጽጽር ከቀረቡት ከእነዚህ ዘጠኝ ማንነቶች ውስጥ ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት 21.1 በመቶ በመሆን ከፍተኛውን ደረጃ እንደያዘ የጥናቱ ውጤት አሳይቷል።
በሁለተኛ ደረጃ ብዛት ያለው የጥላቻ ንግግር ተሰንዝሮበት የተገኘው የኦሮሞ የብሔር ማንነት ሲሆን የአማራ የብሔር ማንነት በ16.8 በመቶ ተከታይ እንደሆነ ሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
ባለ 64 ገፁ ሪፖርት ሴቶች ላይ የሚደርሱ የጥላቻ ንግግሮችን አይነትም በደረጃ አስቀምጧል።
በሦስቱ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ሴቶች ላይ ከሚሰነዘሩ የጥላቻ ንግግሮች ውስጥ 46.2 በመቶው አጸያፊ (offensive) በሚለው ምድብ ውስጥ የሚወድቁ ናቸው።
26.3 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ጥቅል ጾታዊ ፍረጃ የሚል ምድብ ውስጥ የሚጠቀሱ የጥላቻ ንግግር እንደሆኑ ሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።
የጥናት ውጤቱ፤ ወንዶች ላይ ከሚደርሰው የጥላቻ ንግግሮ ውስጥ 72.7 በመቶው አጸያፊ የሚለው ምድብ ውስጥ የሚካተቱ እንደሆነ አመልክቷል።
ይህ የጥናቱ ውጤት ሴቶች እና ወንዶች የሚሰነዘሩባቸው የጥላቻ ንግግር አይነቶች ያላቸውን ልዩነት ያሳየ እንደሆነ ሪፖርቱ ጠቅሷል።
ይህ ልዩነት የጥላቻ ንግግርን ላይ ያለን አረዳድ የተዛባ እንዲሆን ማድረጉን የገለጸው ሪፖርቱ፤ ይህም አንዳንድ የጥላቻ ንግግር አይነቶች ትኩረት ሳይሰጣቸው እንዲታለፉ ማድረጉን አስፍሯል።
ሪፖርቱ በድምዳሜው፤ “እንደ ጥቅል ጾታዊ ፍረጃ፣ ስድብ፣ አዋራጅ ቋንቋ ወይም ሴቶች እና ልጃገረዶች ከሌሎች ጾታዎች ያነሱ [እንደሆኑ የሚገልጹ ንግግሮች] ያሉ [የጥላቻ ንግግር] ቅርጾች ብዙውን ጊዜ ‘ከዛቻ’ ወይም ‘ጠበኛ’ ንግግሮች ጋር ሲነጻጸሩ አነስተኛ ጉዳት ያላቸው ተደርገው ይወሰዳሉ ወይም ጭራሹኑ የጥላቻ ንግግር ተድረገው ላይቆጠሩ ይችላሉ” ብሏል።
የተለያዩ ማንነቶች ላይ የሚደርሰውን የጥላቻ ንግግር ልዩነት መረዳት ይህንን መሰረት ያደረገ የፖሊሲ መፍትሔ ለመቅረጽ እንዲሁም ሴቶች እና ልጃገረዶች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከሚደርስባቸው ጥቃት ለመጠበቅ እንደሚረዳ ጥናቱ በምክረ ሐሳቡ ላይ አስቀምጧል።