ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለቦይንግ የሚቀርቡ የአውሮፕላን አካላት 'ከባድ ግድፈቶች' ነበሩባቸው ተባለ
በቦይንግ ትልቁ አቅራቢ የተዘጋጁ ፊውዝላጆች (አውሮፕላን ሰዎችን እና እቃዎችን የሚጭንበት ክፍል) ከባድ ግድፈቶች አዘውትረው እንደሚገኙባቸው የኩባንያው የቀድሞ የጥራት ተቆጣጣሪ ገለጹ።
በካንሳስ በሚገኘው ስፕሪት ኤሮሲስተም ይሠራ የነበረው ሳንቲያጎ ፓሬዴስ ለቢቢሲ እንደተናገረው ቦይንግ እንዲረከባቸው ዝግጁ በሆኑ የአውሮፕላን አካላት ላይ እስከ 200 የሚደርሱ ግድፈቶችን በተደጋጋሚ እንዳገኘ ተናግሯል።
ችግሩን ለመፍታት ሲሞክር የምርት ሂደት ስለሚቀንስ “አቆርቋዥ” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶኝ ነበር ሲል ተናግሯል።
ስፕሪት ኤሮሲስተም በበኩሉ ጉዳዩን "አልስማማበትም" ሲል አስተባብሏል።
የቦይንግ ትልቁ አቅራቢ ሆኖ የቀጠለው የስፕሪት ኤሮሲስተም ቃል አቀባይ “ክሱን አጥብቀን እየተከላከልን ነው” ብሏል።
ፓሬዲስ ከቢቢሲ እና ከአሜሪካው ሲቢኤስ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ እአአ በ2010 እና 2022 መካከል በድርጅቱ ውስጥ ሲሠራ ያጋጠሙትን ችግሮች ስፕሪት ኤሮሲስተም ላይ አቅርቧል።
ወደ ቦይንግ እንዲጓጓዝ ከተዘጋጀ ፊውዝላጅ "ከ50 እስከ 1200" ችግሮችን ማግኘቱ የተለመደ መሆኑን ተናግሯል።
"ብዙ የጎደሉ ማጣበቂያዎችን፣ ብዙ የታጠፈ አካላትን፣ አንዳንዴም የጎደሉ ክፍሎች አገኝ ነበር።"
ቦይንግ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
'መሳለቅ'
በጥር ወር ለመብረር ከተነሳ በኋላ በሩ የተገነጠለው አዲስ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ስፕሪት ኤሮሲስተም እና ቦይንግ ላይ በከፍተኛ ጫና ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል።
እንደ መርማሪዎቹ ገለጻ ከሆነ በሩ መጀመሪያ ላይ ስፕሪት ኤሮሲስተም ቢገጠምም የተበላሹ ነገሮችን ለማስተካከል በሚል በቦይንግ ቴክኒሻኖች ተከፍቶ የተገጠመ ነው።
ክስተቱ የአሜሪካው የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር የሁለቱንም ተቋማት የምርት ሂደት እንዲመረምር ምክንያት ሆኗል። ኩባንያዎቹ የምርት ቁጥጥር አሠራሮችን ማክበር ያልቻሉባቸው በርካታ አጋጣሚዎችንም አግኝቷል።
ፓሬዲስ ለቢቢሲ እንደተናገረው ከሆነ ስፕሪት ኤሮሲስተም ውስጥ ሲሠራ ያያቸው አንዳንድ ጉድለቶች ቀላል ሲሆኑ ሌሎቹ ግን በጣም ከባዶች ናቸው።
ምርቱን በትኩረት እንዳይመለከትም ጫና እንደተደረገበትም ተናግሯል።
"ለምን እንደማገኘው እና ለምን እንዳየሁት እያነሱ ሁልጊዜ ይሳለቃሉ" ብሏል።
"እነሱ የሚፈለጉት ምርቱ እንዲላክ ብቻ ነው። መጥፎ ፊውላጆችን ማስረከባቸው የሚያስከትለው መዘዝ ላይ አያተኩሩም። እነሱ ያተኮሩት ቁጥሮችን፣ ቀጠሮን እና በጀቱን በማሟላት ላይ ብቻ ነበር… ቁጥሩ ጥሩ መስሎ ከታየ የፊውላጆች ሁኔታ ምንም አያሳስብም" ሲል ተናግሯል።
መረጃ ማውጣት
ብዙዎቹ ፓሬዲስ በስፕሪት ኤሮሲስተም ዙሪያ ያነሳቸው ጉዳዮች በተቋሙ ቅር የተሰኙ ባለአክስዮኖች የመሰረቱትን ክሶችን ተከትሎ የሰጠው ምስክርነት አካል ነው።
በህጋዊ ሰነዶች ላይ ግን "የቀድሞ ሰራተኛ 1" ተብሎ ተጠቅሷል። የአየር ሃይል ቴክኒሻን የነበረው ፓሬዲስ በይፋ ሲናገር ይህ የመጀመሪያው ነው።
ፓሬዲስ ከድርጅቱ ከመልቀቁ በፊትም የ737 ማክስ የመጨረሻው የምርት ሂደት ተቆጣጣሪዎችን ቡድን ለመምራት በቅቷል።
በክሱ ላይ ተሳተፈው ሌላኛው የጥራት ተቆጣጣሪ የነበረው ጆሽ ዲን በከባድ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ምክንያት ባለፈው ሳምንት ከዚህ ህይወቱ አልፏል።
ኩባንያው ሆን ብሎ ከባድ እና ሰፊ የጥራት ጉድለቶችን ለመሸፋፈን በመሞከር እና ጥፋቶቹ ሲጋለጡም ባለአክሲዮኖች ለገንዘብ ኪሳራ ተዳርገዋል የሚል ክስ ነው የቀረበበት። ስፕሪት ኤሮሲስተም የተነሱበትን ጉዳዮች "በጽኑ አስተባብሏል”።
የቦይንግ ድጋፍ
ስፕሪት ኤሮሲስተም በአንድ ወቅት የቦይንግ አካል የነበረ ሲሆን አሁንም የአውሮፕላን አምራቹ ዋና አቅራቢ ሆኖ ቀጥሏል።
ለእያንዳንዱ 737 ማክስ ፊውዝላጅ ዊቺታ፣ ካንሳስ ከሚገኘው ፋብሪካው በማምረት ሲያትል፣ ዋሽንግተን አቅራቢያ ለሚገኘው ቦይንግ ያስረክባል። የ787 ድሪምላይነርም ትላልቅ አካላትን ያመርታል።
ኩባንያው አሁን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው። በዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ 617 ሚሊዮን ዶላር አጥቷል።
ቦይንግ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ከመስማማት ባለፈ የቀድሞ ድርጅቱን መልሶ ለመግዛት እየተነጋገረ ነው።
የአውሮፕላን አምራቹ ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ በስፕሪት ኤሮሲስተም ያለውን የጥራት ስጋት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው።
በዚህም ከዊቺታ ፋብሪካ የሚወጡትን የአውሮፕላን አካላት 80 በመቶ ያህል ጉድለቶችን በመቀነስ ረገድ ተሳክቶላቸዋል።
ሁለቱም ኩባንያዎች የችግሩን ስፋት እንደሚያውቁ እና በሁለቱም ኩባንያዎች የጥራት ተቆጣጣሪዎች መካከል በሚደረጉ ሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ ውይይት መደረጉን ፓሬዲስ ተናግረዋል።
'እርዳታ ጥሪ'
ጉድለቶች የሚመዘገቡበት መንገድ እንዲለውጥ በማድረግ የአጠቃላይ ግድፈቶችን ቁጥር ለመቀነስ በአለቃው መታዘዙን ፓሬዲስ አስታውቋል።
በዚህ ምክንያት ተቃውሞውን በማሰማቱ ከደረጃው ዝቅ ተደርጎ ወደ ሌላ የፋብሪካው ክፍል እንዲየር መደረጉን ተናግሯል።
"ዛቻ እየተፈፀመብኝ እንደሆነ እና ስጋቶችን በማሳየቴ የበቀል እርመጃ እንደተወሰደብኝ ተሰማኝ" ብሏል።
ፓሬዲስ በመቀጠል ለኩባንያው የሰው ሃይል ክፍል “የሥነ ምግባር ቅሬታ” በጽሑፍ አቀረበ። ለወቅቱ ስፕሪት ኤሮሲስተም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቶም አሳወቀ።
በጻፈው ኢሜይል ውስጥ “በስፕሪት ኤሮሲስተም ባለው ጥራት ላይ እምነት አጥቻለሁ። ይህም የእርዳታ ጥሪዬ ነው” ብሏል።
ፓሬዲስ ባቀረበው አቤቱታ ወደቀድሞ ኃላፊነቱ ተመልሶ ያልተከፈለው ገንዘብም ተሰጥቶታል። ብዙም ሳይቆይ ግን ኩባንያውን ለቆ ወጣ።
በዊቺታ ፋብሪካ ውስጥ የተከሰቱ ጉድለቶች ሊኖሩት ስለሚችል አሁን በ737 ማክስ ለመብረር ፈቃደኛ እንዳልሆነ ተናግሯል።
"በስፕሪት ኤሮሲስተም እስክሠራ ድረስ ለመብረር የሚፈሩ ብዙ ሰዎች አጋጥመወኝ አያውቅም ነበር" ብሏል።
ስፕሪት ኤሮሲስተም በነበርኩበት ጊዜ ግን ለመብረር የሚፈሩ ብዙ ሰዎችን አገኘሁ። ምክንያታቸው ደግሞ አውሮፕላኑ አካላት እንዴት እንደሚመረቱ ስላዩ ነው።