የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን ለሚያጣራው ኮሚሽን አዲስ ሊቀ መንበር መረጠ

የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን ለሚያጣራው የባለሙያዎች ቡድን አዲስ ሊቀ መንበር መምረጡን አስታወቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ታህሳስ 12፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ታንዛኒያዊው መሃመድ ቻንዴ ኦትማንን አዲሱ ሊቀ መንበር ሆነው ተሹመዋል ብሏል።

አዲሱ ሊቀ መንበር የተሾሙት ኮሚሽኑን ሲመሩ የነበሩት ኬንያዊቷ ካሪ ቤቲ ሙሪንጊ መልቀቃቸውን ተከትሎ እንደሆነም አስታውቋል። 

ኬንያዊቷ ካሪ ቤቲ ለምን እና መቼ እንደለቀቁ መግለጫው ያለው ነገር የለም።

ታንዛንያዊው ጠበቃ እና የቀድሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ መሃመድ ቻንዴ አትማን ለኮሚሽኑ ሶስተኛው ሊቀመንበር ናቸው።

በኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች፣ የስደተኛ ሕጎችና ሌሎች ጥሰቶችን የሚያጣራና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያካሂድ የተቋቋመው ቡድን የደረሰበትን ግኝት በዚህ ዓመት መስከረም ላይ አውጥቷል።

ሁለት ዓመት በዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላማዊ ዜጎች ላይ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

19 ገጾች ያሉትን የመጀመሪያ ግኝት ሪፖርት ይፋም በተደረገበት ወቅት ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሆን ተብለው የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች እንደ ጦር መሳሪያነት ጥቅም ላይ ስለመዋላቸው ምክንያታዊ የሆኑ ማስረጃዎች አሉ ብሏል።

ኮሚሽኑ እነዚህ የተፈጸሙ ጥሰቶች የጦር ወንጀሎች እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንደሆኑም ያምናል ብሏል።

የኮሚሽኑን ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግሥት እንደማይቀበለው አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መርማሪ እንዲቋቋም የተላለፈውን ውሳኔን ጨምሮ የኮሚሽኑን ጊዜ ማራዘም ስትቃወም መቆየቷ ይታወሳል።

የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤን ለፖለቲካ ዓላማ ማራመጃነት እየተጠቀሙበት ነው እንዲሁም በሃገር ውስጥ ጉዳይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነት ነው በማለት የወቀሰችው ኢትዮጵያ በቅርቡም የኮሚሽኑ የተራዘመለት ጊዜ እንዲቋረጥም መጠየቋን የሃገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ሆኖም ከሰሞኑ ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት ዕድል (አጎዋ) ተጠቃሚነት እንድትመለስ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን ለሚያጣራው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሰብዓዊ ባለሙያዎች ቡድን ፍቃድ ስትሰጥ መሆኑ ተዘግቧል።

ሪፖርተር እንግሊዝኛው ጋዜጣ እንደዘገበው የባለሙያዎቹ ቡድን ወደ አገር ውስጥ ገብተው መመርመር እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡን በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ ባለሥልጣን መናገራቸውን ነው።

ኮሚሽኑ ጦርነቱ ወደተካሄደባቸው የትግራይ ክልል አካባባቢዎች እንዲሄዱ አለመፈቀዱን መግለጹ ይታወሳል።

አሜሪካ ከትግራዩ ጦርነት ጋር በተያያዘ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅመዋል በሚል አጎዋ ከተሰኘው የቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት ኢትዮጵያ መታገዷ ይታወሳል።

የምርመራ ቡድኑ ባለፈው ዓመት የካቲት ሲቋቋም የቀድሞ የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ ሊቀ መንበር ሆነው ተሹመው ነበር።

ፋቱ ቤንሱዳ በዩናይትድ ኪንግደም የጋምቢያ ከፍተኛ ኮሚሽነርነትን ስልጣን መቀበላቸውን ተከትሎ ከኮሚሽኑ ሊቀመንበርነት ለቀዋል።

በሳቸውም ፈንታ በመጀመሪያ አባል ሆነው የተሰየሙት ኬንያዊቷ ጠበቃና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ በሊቀመንበርነት እንዲመሩ መወሰኑ ይታወሳል።

 በሚቺጋን የሕግ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት አሜሪካዊ ስቲቨን ራትነር በጦርነቱ ተፈፅመዋል ለተባሉ ዓለማቀፍ ወንጀሎች መርማሪ ቡድን አባል ናቸው።

በተጨማሪ የፋቱን መልቀቅ ተከትሎ የሲሪላንካ ዜግነት ያላቸው ራዲካ ኩማራስዋሚ በኮሚሽን አባልነት መሾማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ገልጿል።