የፀጥታው ምክር ቤት የእስራኤልን የጋዛ ወረራ ዕቅድ ኮነነ

የተባበሩት መንግሥታት አምባሳደሮች እስራኤል የጋዛ ከተማን "ለመቆጣጠር" ያያዘችውን ዕቅድ ሲኮንኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔተንያሁ ጦርነቱን ለማስቆም "የተሻለው መንገድ" ነው ሲሉ ተከራከሩ።

ኔታንያሁ "ውሸቱን ለማስተንፈስ" ሲሉ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ የታቀዱ ማጥቃቶች "በአመዛኙ በፍጥነት" እንደሚከናወኑ እና "ጋዛን ከሐማስ ነፃ የሚያወጣ" እንደሚሆን ተናግረዋል ።

በተጨማሪም በጋዛ ውስጥ የሚገኙ የእስራኤል ታጋቾች "ሆን ተብሎ የተራቡት እነርሱ ብቻ ናቸው" ሲሉ እስራኤል ጋዛውያንን እያስራበች ነው የሚለውን ክስ አስተባብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ወቅት ከባድ ትችት ገጥሟት የነበረ ሲሆን እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ሌሎችም ዕቅዱም "ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግን ይጥሳል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ከዴንማርክ፣ ግሪክ እና ስሎቬንያ ጋር በመሆን ዕቅዱ እንዲቀለበስ ጠይቀው፣ "ታጋቾችን ለማስለቀቅ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። እንደውም ሕይወታቸውን የበለጠ አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል" ብለዋል።

ሌሎች የምክር ቤቱ አባላትም ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

ቻይና በጋዛ የሚኖሩ ሰዎች "በጋራ መቅጣት" ተቀባይነት እንደሌለው ስትገልጽ፣ ሩሲያ ደግሞ "በግድየለሽነት ግጭትን ማባባስ" ስትል ጠርታዋለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሃፊ ሚሮስላቭ ጄንካ በስብሰባው ላይ እንደተናገሩት "እነዚህ ዕቅዶች ከተተገበሩ በጋዛ ላይ ሌላ ጥፋት ሊያስከትሉ ይችላሉ፤ ይህም በቀጣናው ላይ ቀጣይነት ያለው ቀውስ እና ተጨማሪ የግዳጅ መፈናቀል፣ ግድያ እና ውድመት ያስከትላል።"

ከተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊነት ቢሮ የተገኙት ራምሽ ራጃሲንግሃም በጋዛ ያለው ረሃብ ከአሁን በኋላ እያንዣበበ ነው ተብሎ እንደማይገለጽ ሲያስረዱ"ይህ ረሃብ ነው፣ ግልጽ እና ቀላል" ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ዶሮቲ ሺአ ግን እስራኤልን ተከላክለዋል።

አምባሳደር ዶሮቲ ሺአ በስብሰባው ላይ አሜሪካ ታጋቾችን ለማስለቀቅ እና ጦርነቱን ለማስቆም "ያለሰለሰ ጥረት" እያደረገች መቆየቷን አስረድተው ስብሰባው ይህንን ጥረት ከግምት አላስገባም ብለዋል።

"ሐማስ ታጋቾቹን ከለቀቃቸው ጦርነቱ ዛሬ ሊቆም ይችላል" ያሉት አምባሳደሯ፣ ሌሎች አባላት ስብሰባውን ተጠቅመው "እስራኤልን በዘር ማጥፋት ወንጀለዋል" በማለት ክሱም "በተጨባጭ ውሸት ነው" ሲሉ አስተባብለዋል።

እሁድ ዕለት የኔታኒያሁ ጽሕፈት ቤት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ስለእስራኤል ዕቅድ መነጋገራቸውን አስታውቋል።

በእስራኤል የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠልፈኞች የመንግሥትን ዕቅድ የታጋቾችን ሕይወት አደጋ ላይ ይጥላል በማለት ተቃውመው አደባባይ ወጥተዋል።

ኔታንያሁ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት "የሐማስ ሁለት ጠንካራ ይዞታዎችን"፣ በጋዛ ከተማ የሚገኘውን እና በአል-ማዋሲ ዙሪያ የሚገኘውን ማዕከላዊ ቦታ እንዲያፈርስ መመሪያ ተሰጥቷል ብለዋል።

በተጨማሪም ወደ ጋዛ የሚገባውን እርዳታ ለመጨመር የሚወስዷቸውን እርምጃዎች ሲያስረዱ ለሰብአዊ እርዳታ ስርጭት ደህንነታቸው የተጠበቁ ኮሪደሮችን ማዘጋጀት እንዲሁም በእስራኤል እና ሌሎች አጋሮች ከአየር ላይ ተጨማሪ እርዳታዎችን ለመጣል ማቀዳቸውን አብራርተዋል።

ዕቅዱ በአሜሪካ እና በእስራኤል የሚደገፈው በአወዛጋቢው የጋዛ ሰብአዊ ፋውንዴሽን የሚተዳደሩትን የእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያዎችንም ይጨምራል ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ይፋ እንዳደረገው ፋውንዴሽኑ እርዳታ ማከፋፈል ከጀመረበት የግንቦት ወር አንስቶ 1,373 ፍልስጤማውያን ምግብ ለመቀበል በወጡበት ተገድለዋል።

ኔታንያሁ ሐማስ "የእርዳታ መኪኖችን በኃይል ዘርፏል" በማለት በፋውንዴሽኑ ጣቢያዎች አቅራቢያ ስለተገደሉት ፍልስጤማውያን ሲጠየቁ "ሐማስ ብዙ ተኩሶችን ከፍቶ ነበር" ብለዋል።

በጋዛ ስላሉት ቀሪ እስራኤላውያን ታጋቾች የተጠየቁት ኔታንያሁ "ምንም ነገር ካላደረግን ልናስወጣቸው አንችልም" ብለዋል።

በጋዛ 20 ያህል ታጋቾች አሁንም በሕይወት መኖራቸው ይታመናል።

የእስራኤሉ መሪ ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኃን በሐማስ ፕሮፓጋንዳ ዒላማ ተደርገዋል ብለዋል።

በመላው ዓለም በጋዜጦች የፊት ገፆች ላይ የወጡትን አንዳንድ በምግብ እጥረት የተጎዱ የጋዛ ሕጻናት ፎቶግራፎችን "ውሸት" ሲል አስተባብለዋል።

እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከከፈተችበት ጊዜ አንስቶ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ገብተው በነጻነት አንዲዘግቡ አልፈቀደችም።

ኔታንያሁ ግን ጦሩ የውጭ ጋዜጠኞችን ለሁለት ቀናት እንዲገቡ አንዲፈቅድ መመሪያ መሰጠቱን ተናግረዋል።

ከቅዳሜ ጀምሮ በጋዛ በረሃብ እና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት አምስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን አጠቃላይ በረሃብ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 217 መድረሱን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከ2016 መስከረም ወር ጀምሮ እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ በድምሩ ከ61,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውንም ተነግሯል።