በቡድን 20 ጉባኤ የቻይናው አቻቸው ዢ ዢፒንግ ስለማይገኙ ባይደን ማዘናቸውን ገለጹ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቻይናው አቻቸው ፕሬዝዳንት ዢ ዢፒንግ በሕንድ በሚካሄደው የቡድን 20 ጉባኤ ላይ እንደማይሳተፉ መግለጻቸው “እንዳሳዘናቸው” ገለጹ።

የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኩዊንግ አገሪቱን ወክለው በኒው ደልሂ ይገኛሉ።

“በቡድን 20 ጉባኤ ባለመምጣቱ በጣም አዝኛለሁ። ሆኖም ግን መገናኘታችን አይቀርም” ያሉት ባይደን ሁለቱ መሪዎች መቼ እንደሚገናኙ በግልጽ አላስቀመጡም።

አምና በኢንዶኔዥያ ሁለቱ መሪዎች በቡድን 20 ጉባኤ ላይ ተገናኝተዋል።

ዢፒንግ ወደ ሕንድ ለጉባኤው እንደሚሄዱ ቀደም ሲል ቢገልጹም ኋላ ላይ ለጋዜጠኞች ማረጋገጫ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

ስማቸው ያልተጠቀሱ ምንጮችን እንደሚጠቁሙት ፕሬዝዳንቱ በጉባኤው አይገኙም።

የቻይና እና ሕንድ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ እየሻከረ ይገኛል። ሌሎች የሚያጋጯቸው ነገሮች እንዳሉ ሆነው በሂማሊያ ግዛት በድንበርም እየተወዛገቡ ነው።

ባለፈው ሳምንት ቻይና አሩናቻል ፐርዲሽ እና አኪሲ ቺን የተባሉ አካባቢዎችን ከቻይና ግዛት ጋር የሚያጠቃልል ካርታ መልቀቋን ተከትሎ ሕንድ ተቃውሞ አሰምታለች።

የአሜሪካ እና ቻይና ፕሬዝዳንቶች የፊታችን ጥቅምት በእስያ ፓሲፊክ የምጣኔ ሀብት ትብብር ጉባኤ ሳን ፍራንሲስኮ ሲካሄድ ይገናኛሉ።

የአገራቱ ግንኙነት ጥሩ የሚባል አይደለም። የቻይና ነው የተባለ ሰላይ ፊኛ በአሜሪካ ከታየ በኋላ ነገሮች ተካረዋል።

በዢንጃንግ እና ሆንግ ኮንግ የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ፣ በታይዋን ድንበር፣ በደቡባዊ ቻያና ባሕር እና በቻይና የኢንዱስትሪ የበላይነት ሁለቱ አገራራት አይስማሙም።

የውጭ ጉዳይ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከንን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣኖች ከቻይና ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል ወደ ቻይና አቅንተዋል።

በሌላ በኩል ቻይና የታዳጊ አገራት መሪ እንደሆነች ራሷን ስትገልጽ ይስተዋላል። አሜሪካ መር የሆነ የዓለም አገራት አሰላለፍንም ትገዳደራለች።

ቻይና ባለፈው ከብሪክስ አባል አገራት ጋር ስትገናኝ የምዕራቡን ዓለም “የበላይነት” በመተቸት፣ “ከቅኝ ግዛት ሰንሰለት” ታዳጊ አገሮች መውጣት እንዳለባቸው ገልጻለች።

ብሪክስ ባለፈው ጉባኤው ኢትዮጵያ፣ አርጀንቲና፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትን በአባልነት መቀበሉ ይታወሳል።