ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያቀረበችውን ጥያቄ የትግራይ አባቶች ሳይቀበሉት ቀሩ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በጦርነቱ ወቅት ከትግራይ አብያተ ክርስቲያናት አባቶች ጋር ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት መልሶ እንዲጀመር ያረበችው ጥያቄን እንዳልተቀበሉት ገለጹ።
ለሁለት ዓመታት በተደረገው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል ተለይቶ በቆየው ትግራይ ውስጥ የነበሩ አባቶች፣ በክልሉ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት እና ምዕመናን ላይ በደል ሲፈጸም ማዕከላዊቷ ቤተክርስቲያን ምንም ባለማለቷ መውቀሳቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም ከአንድ ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በመለየት የትግራይ ጠቅላይ ቤተክህነት ለመመስረት መወሰናቸውን ይፋ ማድረጋቸው አድርገዋል።
በክልሉ በሚገኙ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የበላይ አባቶች ተፈርሞበት በተሰራጨው እና የክልሉ መገናኛ ብዙኃን በዘገቡት ደብዳቤ መሠረት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በኩል የቀረበውን ግንኙነትን መልሶ የመጀመር ጥያቄን አለመቀበላቸው ተገልጿል።
አባቶቹ በባለ ስድስት ገጽ ደብዳቤያቸው ላይ ግንኙነቱ እንዲቋረጥ አድርገውታል ያሏቸውን ምክንያቶቻቸውን በዝርዝር ያረቡ ሲሆን፣ በዋናነት በጦርነቱ ወቅት በክልሉ ባለው ሕዝብ እና አብያተክርስቲያናት ላይ የደረሰውን “ጭፍጨፋ እና ውድመትን” ቤተክርስቲያኗ አላወገዘችም ከጎናችንም አልቆመችም የሚል ነው።
በዚህም ሳቢያ መንበረ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን የተባለ ጠቅላይ ቤተክህነት ማቋቋማቸውን እና ይህም በክልሉ እና በተለያዩ ዓለማት ባሉ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ጥያቄ ውስጥ እንደማይገባ እና በጀመሩት መንገድ እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በዚህም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የተቋረጠውን ግንኙነት መልሶ ለማደስ የቀረበው ጥያቄ በአሁኑ ወቅት የክልሉ የቤተክርስቲያን አባቶች ብቻ የሚመልሱት ባለመሆኑ እንደማይቀበሉት በደብዳቤያቸው ላይ ገልጸዋል።
ለቤተክርስቲያኗ ጥሪ ምላሽ በመስጠት ፊርማቸውን ያኖሩት የሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ የምሥራቃዊ ትግራይ፣ የማዕከላዊ ትግራይ እና የመቀሌ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ የሆኑት አቡነ ማትያስ በተለያዩ አጋጣሚዎች ላይ እንዲሁም በሰጡት ቃለ ምልልስ በትግራይ ውስጥ ከባድ በደሎች እንደተፈጸሙ በይፋ በመናገር እና ጦርነቱ እንዲቆም በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ነበር።
ላቀረበችው ጥሪ የተሰጣትን ምላሽ በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስካሁን ያለችው ነገር የሌለ ሲሆን፣ ነገር ግን ደብዳቤው ለቤተክርስቲያኗ ሲደርስ ምላሽ እንደምትሰጥ ተዘግቧል።
ባለፈው ጥቅምት ላይ በጦርነት ላይ በነበሩት በመንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል በዘላቂነት ግጭትን ለማቆም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በጦርነቱ እና በፖለቲካ ምክንያት ከትግራይ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የተፈጠረውን መራራቅ በይቅርታ በማደስ ግንኙነቱ መልሶ እንዲጀመር በደብዳቤ ጥያቄ ማቅረቧ መገለጹ ይታወሳል።
በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ውስጥ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት የደረሰ ሲሆን፣ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞም በአብያተ ክርስቲያናት እና ምዕመናን ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱ ሲዘገብ ቆይቷል።
ይህንንም ተከትሎ ጦርነቱ በተባባሰበት ጊዜ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ በትግራይ የሚገኙ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእምነት አባቶች ከማዕከላዊቷ ቤተክርስቲያን በመነጠል የትግራይ ጠቅላይ ቤተክህነት ለመመስረት መወሰናቸው ይታወሳል።
በክልሉ እንዲህ ያለውን ውሳኔ ያሳለፉት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እምነት አባቶች ብቻ ሳይሆኑ በሌሎችም የእምነት ተቋማት መሪዎች ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ መድረሳቸው ይታወቃል።