ኃይል ለመቆጠብ ዩክሬናውያን ከቻሉ ከአገር እንዲወጡ ተጠየቁ

በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት እክል የገጠማት ዩክሬን ዜጎቿ ከቻሉ አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ጠየቀች።

የዩክሬን ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋም ኃላፊ በአገሪቱ ያጋጠመውን ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ለማመጣጠን ነዋሪዎች አገሪቷን ለቀው ለመውጣት ማሰብ አለባቸው ብለዋል።

“ለመጪዎቹ ሦስት ወይም አራት ወራት የሚቆዩበት አማራጭ ቦታ ካገኙ ለአጠቃላይ የኃይል አቅርቦት ሥርዓቱ በጣም ጠቃሚ ይሆናል” ሲሉ የዲቴክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማክሲም ቲምቼንኮ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ በምታደርሰው ጥቃቶች ዩክሬን የኃይል ሥርዓት ግማሽ ያህሉ ተጎድቷል።

በአገሪቷ የክረምት ወራት እየገባና የቅዝቃዜው መጠን ከፍተኛ በሆነበት በአሁኑ ወቅት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል የላቸውም።

ሩሲያ በተደጋጋሚ በምታደርጋቸው የሚሳኤል ጥቃቶች ኃይልን ጨምሮ መሠረተ ልማቶች ላይ ኢላማ ማድረጓን ተከትሎም በበርካታ የዩክሬን አካባቢዎች የኃይል መቋረጥ የተለመደ ሆኗል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የጥቃቶቹ መቀጠል ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ ያለመሆኗ “መዘዝ” እንደሆነ ጠቁመዋል።

በርካታ ምዕራባውያን መሪዎች የሲቪል መሠረተ ልማቶችን ኢላማ ማድረግ የጦር ወንጀል ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ማክሲም ቲምቼንኮ የሚመሩት ኩባንያ አንድ አራተኛ የሆነውን የዩክሬን የኃይል አቅርቦትን ይሸፍናል።

የዩክሬን የኃይል ሽፋን በእንያንዳንዱ የሩሲያ ጥቃት አስተማማኝነቱ እየቀነሰ ይሄዳል፤ እናም የኤሌክትሪክ ፍጆታን መቀነስ ሥራውን ለማስቀጠል መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።

መንግሥት ሕዝቡ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ቁሶችን፣ እንደ የምግብ ማብሰያ እና የልብስ ማጠቢያ ማሽን አጠቃቀማቸውን እንዲገድቡ አሳስቧል።

ነገር ግን የተበላሸው የኃይል ሥርዓት አሁን ያለውን ፍላጎት ለማሟላት በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ባለመቻሉ የትኛውም አጠቃቀምን የሚቀነስበት መንገድ ታሳቢ ሊሆን እንደሚገባ ኃላፊው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይህም ዜጎች አገሪቷን ለቀው መውጣት የሚጨምር ሲሆን ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በጀመረችው ጦርነት እንድታሸንፍ ማገዝ ነው ሲሉ ኃላፊው አብራርተዋል።

“የኃይል አቅርቦት ትንሽ የምትጠቀሙ ከሆነ ጉዳት የደረሰባቸው ወታደሮች ያሉባቸው ሆስፒታሎች የኃይል አቅርቦት ዋስትና ይኖራቸዋል። ውስን ኃይል በመጠቀም ወይም ከአገር በመውጣት ለሌሎች ሰዎች አስተዋፅኦ ታደርጋላችሁ” ብለዋል።