በአባቱ ተጠቁሞበት የተያዘው የቻርሊ ከርክ ግድያ ተጠርጣሪ ታይለር ሮቢንሰን ማን ነው?

የ22 ዓመቱ ታይለር ሮቢንሰን

የፎቶው ባለመብት, FBI

ወግ አጥባቂውን አክቲቪስት ቻርሊ ከርክን በመግደል የተጠረጠረው የ22 ዓመቱ ታይለር ሮቢንሰን፣ ዩታ ግዛት ውስጥ ከወላጆቹ ጋር ለረጅም ጊዜ ይኖር የነበረ የአካባቢው ተወላጅ መሆኑን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ከከርክ ግድያ በኋላ የተሠራጨውን የደኅንነት ካሜሪ ምሥል የተመለከቱት አባቱ ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ መስከረም 2/2016 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉ በአገር አቀፍ ደረጃ ሲደረግ የነበረውን አደን ለማስቆም ወሳኝ እንደሆነ መርማሪዎች ገልጸዋል።

የተጠርጣሪው አባት የልጃቸውን ምሥል በተሠራጨው ምሥል ላይ ከተመለከቱ በኋላ እጁን እንዲሰጥ እንዳበረታቱት በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ሁለት የሕግ አስከባሪ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል። ከዚያም አባትየው ጉዳዩን ለፖሊስ ለጠቆመው የቤተሰባቸው ወዳጅ አሳውቀዋል።

ኤፍቢአይ ታይለር ሮቢንሰን በቁጥጥር ስር መዋሉን ባሳወቀበት ጊዜ ምርመራው በመቀጠሉ የተጠርጣሪውን የኋላ ታሪክ፣ የፖለቲካ አመለካከት እና ለግድያው ምክንያት ሊሆን የሚችለውን ጉዳይ ለመግለጽ ፈቃደኛ አልሆነም።

የኤፍቢአይ ቃል አቀባይ "ትክክለኛ ተፈላጊ በቁጥጥራችን ስር እንዳለ እርግጠኞች ነን፣ ነገር ግን ስለማንነቱ እና ለምን እርምጃውን እንደወሰደ ሙሉ መረጃ ለማግኘት አሁንም እየሰራን ነው" ብለዋል።

ታይለር ሮቢንሰን

የፎቶው ባለመብት, Handout

የምስሉ መግለጫ, ተጠርጣሪው ታይለር ሮቢንሰን በፖሊስ የተነሳው ፎቶ

የዩታ ግዛት አገረ ገዢ ስፔንሰር ኮክስ ለመርማሪዎች ቃላቸውን የሰጡ አንድ የቤተሰብ አባል ሮቢንሰን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ "የበለጠ ወደ ፖለቲካ እያዘነበለ" እንደመጣ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከጥቃቱ በፊት በእራት ላይ በነበረ ውይይት ወቅት ሮቢንሰን በዩታ ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ስለሚካሄደው የኪርክ ስብሰባ አንስቶ ነበር ተብሏል።

ቢቢሲ የተመለከታቸው ይፋዊ መዛግብት እንደሚያሳዩት ሮቢንሰን ቀደም ሲል በዩታ ውስጥ ለየትኛውም ፓርቲ ያልወገነ ወይም ገለልተኛ መራጭ ሆኖ ተመዝግቧል።ወላጆቹ ማቲው ካርል ሮቢንሰን እና አምበር ዴኒስ ሮቢንሰን የተመዘገቡ የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎች መሆናቸውን መንግሥታዊ ሰነዶች ያሳያሉ።

የግድያው ተጠርጣሪ የሆነው ሮቢንሰን ከርክ ለተማሪዎች ንግግር እያደረገ በተገደለበት ዩታ ቫሊ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ተማሪ አይደለም።

የዩታ የከፍተኛ ትምህርት ቦርድ ባወጣው መግለጫ ታይለር ጀምስ ሮቢንሰን በዲክሲ የቴክኒክ ኮሌጅ ውስጥ የኤሌክትሪክ ሙያ ልምምድ ፕሮግራም የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ነበር ብሏል።

የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የሮቢንሰን አባት የማዕድ ቤት መገልገያዎችን የሚሠሩ ባለሙያ ሲሆኑ እናቱ ደግሞ የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኛ ናቸው።ቤተሰቡ የሞርሞን እምነት ተከታይ ሲሆን በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ።

መርማሪዎች በግድያው የተጠረጠረው ሮቢንሰን በበይነ መረብ ረጅም ጊዜ የሚያጠፋና በዚህ ልማድ የተዘፈቀ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎችን አግኝተዋል።

በቻርሊ ከርክ ግድያ የተጠረጠረው ታይለር ሮቢንሰን መያዙን መጀመሪያ ላይ ይፋ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ናቸው። አርብ ዕለት ፐሬዝዳንቱ ለፎክስ ቴሌቪዥን ተጠርጣሪው በአባቱ ተጠቁሞበት በቁጥጥር ስር መዋሉን አሳውቀዋል።

ስፔንሰር ኮክስ በኤፍቢአይ እና በፖሊስ ባለሥልጣነት ተጅበው መግለጫ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዩታ አገረ ገዢ ስፔንሰር ኮክስ መግለጫ ሲሰጡ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ተጠርጣሪው በተያዘበት ጊዜ የለበሰው ልብስ ጥቃቱን ፈጽሞ ከዩኒቨርስቲው ሲወጣ በታየበት ቪዲዮ ላይ ያደረገው እንደነበር መርማሪዎች አረጋግጠዋል።

ተጠርጣሪው ከቤተሰቦቹ ጋር በነበረው ውይይት ወቅት ቻርሊ ከርክን "በጥላቻ የተሞላ እና ጥላቻን የሚያሠራጭ" በማለት ሲወቅሰው ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ መረጃዎች ሮቢንሰን ላለፉት አስርት ዓመታት በአሜሪካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደረጉት እና ብዙ ጊዜ በትራምፕ ፖሊሲዎች እና የቀኝ ፅንፈኛ ቡድኖችን የሚቃወሙት አክራሪ የግራ አክቲቪስቶች ስብስብ የሆነው አንቲፋ ወይም ፀረ ፋሺስት እንቅስቃሴ ደጋፊ ተደርጎ ሊታሰብ እንደሚችል ያመለክታሉ።

ባለሥልጣናት እንዳሉት ሮቢንሰን አሁን በሌሎች ማኅበረሰቦች ዘንድ ታዋቂ በሆነው በዋናነት በኢንተርኔት ጌሞች ወዳጆች የሚዘወተረው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ በሆነው ዲስኮርድ ላይ ንቁ ተሳታፊ ሳይሆን እንደማይቀር አመልክተዋል።

አብሮት የሚኖረው ጓደኛው በዚሁ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ "ታይለር" በሚል ስም ስለ ጠመንጃ አጠቃቀም እና መሳሪያውን ስለመደበቅ የሚገልጹ መመሪያዎችን በተመለከተ ተከታታይ መልዕክቶችን ለመርማሪዎች አሳይቷል።

ዲስኮርድ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ በታይለር ስም ያለው አካውንት መታገዱን ባወጣው መግለጫ አሳውቋል። ". . . ፖሊሲያችንን በመጣሱ የተጠርጣሪውን መለያ አስወግደነዋል" ብሏል።

በአሁኑ ወቅት ዐቃቢያን ሕጎች መደበኛ ክሶችን አዘጋጅተው እስኪጨርሱ ድረስ ሮቢንሰን በእስር ላይ ይገኛል።

በቅርብ ጊዜ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ከሆኑ የፖለቲካ ግድያዎች አንዱ እንደሆነ በሚነገረው ግድያ አላማ እና የታሪክ ግንኙነት ላይ የሚደረገው ምርመራ እንደቀጠለ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

በቻርሊ ከርክ ግድያ ተጠርጥሮ በተያዘው በ22 ዓመቱ ወጣት ታይለር ሮቢንሰን የኋላ ታሪክ፣ ለግድያው ያለው ምክንያት እና ፖለቲካዊ ዝንባሌውን በተመለከተ የሚደረገው ምርመራም ይቀጥላል።

ይህ የቻርሊ ከርክ ግድያ በቅርቡ የአሜሪካ ታሪክ ውስጥ በተከሰተ ጉልህ ፖለቲካዊ ግድያ ላይ የሚደረግ ምርመራ ይሆናል ሲሉ ባለሥልጣናት ገልጸውታል።