ለ68 ሕጻናት ሞት ምክንያት ከሆነ ሽሮፕ ጋር በተያያዘ 23 ሰዎች ተፈረደባቸው

ተከሳሾች እና ጠበቆች ባለፈው ዓመት ፍርድ ቤት በቀረቡበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ተከሳሾች እና ጠበቆች ባለፈው ዓመት ፍርድ ቤት በቀረቡበት ጊዜ

ለ68 ህጻናት ሞት ምክንያት ነው ከተባለው የተመረዘ የሳል ሽሮፕ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 23 ሰዎች ኡዝቤክስታን ውስጥ ተፈረደባቸው።

ከመድኃኒቱ ጋር በተያያዘ ተከሰው ፍርድ ቤት የቀረቡት ግለሰቦች ታክስ በማጭበርበር፣ ደረጃውን ያልጠበቀ ወይም ሐሰተኛ መድኃኒት በመሸጥ፣ ኃላፊነትን አላግባብ በመጠቀም፣ በግድየለሽነት፣ ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም እና ጉቦ በመቀበል ጥፋተኛ ተብለዋል።

ለእነዚህ ጥፋቶችም የኡዝቤክስታን ፍርድ ቤት በተከሳሾቹ ላይ ከሁለት አስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስር ፈርዶባቸዋል።

በዋና ከተማዋ ታሽኬንት ባለ ፍርድ ቤት ጉዳዩ በተሰማበት ጊዜ በመርዛመው ሽሮፕ የሞቱት ህጻናት ቁጥር ቀደም ሲል ከተነገረው ከፍ ብሎ ቀርቧል።

ከስድስት ወራት በፊት ክሱ በተከፈተበት ጊዜ 65 ህጻናት መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ግን የሟቾች ቁጥር በሦስት ከፍ ማለቱን ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

ይህ አደገኛ ነው የተባለው የህጻናት የሳል ሽሮፕ ማሪዮን ባዮቴክ በተባለ የሕንድ ፋብሪካ የተመረተ ሲሆን፣ ኳራማክስ ሜዲካል የተባለው ድርጅት ደግሞ ኡዝቤክስታን ውስጥ ለተጠቃሚዎች አሰራጭቷል።

ረጅሙ የ20 ዓመት የፍርድ ቤቱ የእስር ቅጣት የተላለፈውም የመድኃኒቱ አከፋፋይ በሆነው ኩባንያ ዋና ዳይሬክተር ላይ መሆኑ ታውቋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ወደ አገር ውስጥ ለሚገቡ መድኃኒቶች ፈቃድ የሚሰጠው የመንግሥት ተቋም ከፍተኛ ባለሥልጣንም የበርካታ ዓመታት የአስር ቅጣት ተፈርዶበታል።

ኡዝቤክስታን ውስጥ መድኃኒቶቹን የተጠቀሙ የ18 ህጻናት ሕይወት ካለፈ በኋላ የዓለም ጤና ድርጅት በሕንዱ ማሪዮን ባዮቴክ የሚመረቱ ሁለት ሽሮፖች “ከደረጃ በታች ናቸው” ብሎ አስታውቋል።

ድርጅቱ እንዳለው አምብሮኖል እና ዶክ-1 ማክስ የተባሉት ሁለት ሽሮፖች ከሚጠበቀው መጠን በላይ አደገኛ ንጥረ ነገሮች በውስጣቸው ይዘዋል።

በወቅቱ የመድኃኒቶቹ አምራች ማሪዮን ባዮቴክ የቀረበውን ክስ በማስተባበል ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ፣ በዓለም ጤና ድርጅት ግኝት “እንደማይስማማ” አሳውቆ ነበር።

ነገር ግን የሕንድ ጤና ሚኒስቴር የመድኃኒቶቹ ምርት እንዲቋረጥ ያደረገ ሲሆን፣ አምራቹ ያለበት የኡታር ፕራዲሽ ግዛት የምግብ ደኅንነት ባለሥልጣን ደግሞ የፋብሪካውን ፈቃድ ካገደው በኋላ መጨረሻ ላይ “አስከወዲያኛው” ሰርዞታል።

የኡዝቤክስታን ፍርድ ቤት በተከሳሾቹ ላይ እስር ከመበየኑ በተጨማሪ በሳል ሽሮፑ ምክንያት ሕይወታቸው ላለፈው የ68ቱ ህጻናት ቤተሰቦች እያንዳንዳቸው የ80 ሺህ ዶላር ካሳ እንዲከፈላቸው ወስኗል።

እንዲሁም ተመሳሳይ መጠን ያለው የገንዘብ ካሳ ሽሮፑን ወስደው የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው የአራት ህጻናት ቤተሰቦች እንዲሰጥ አዟል።