ሕንድ 70 ለሚጠጉ ህጻናት ህልፈት ምክንያት ሆኗል የተባለውን የሽሮፕ አምራች አገደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሕንድ የጤና ባለስልጣናት በጋምቢያ ወደ70 የሚጠጉ ህጻናት ህይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል በሚል የታመነውን የሳል መድሃኒት የሚያመርተው ተቋም ምርቱን እንዲያቆም አገደች።
ማይደን ፋርማሱቲካልስ የተሰኘው ለህጻናቱ ህልፈት ምክንያት ሆነዋል የተባሉትን አራት ፈሳሽ መድሃኒቶች የሚያመርት ሲሆን የሕንድ የጤና ተቆጣጣሪዎች “በምርት እና በሙከራ ተግባራቱ ውስጥ መከተል የነበረበትን ደንቦችን ጥሷል” ሲሉ ወቅሰዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ባሳለፍነው ሳምንት ፕሮመታዚን ኦራል ሶሉሽን (Promethazine Oral Solution)፣ ኮፌክስማሊን ቤቢ ካፍ ሲረፕ (Kofexmalin Baby Cough Syrup)፣ ማኮፍ ቤቢ ካፍ ሲረፕ (Makoff Baby Cough Syrup) እና ማግሪፕ ኤን ኮልድ ሲረፕ (Magrip N Cold Syrup) የሚባሉት መድሃኒቶችን ወላጆች ለልጆቻቸው ከመስጠት እንዲቆጠቡ አሳስቦ ነበር።
የህጻናቱን ህልፈት በተመለከተም በአሁኑ ወቅት በሕንድ እና በጋምቢያ ምርመራዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ።
የሕንድ የጤና ተቆጣጣሪዎች እንዳሉት በኒው ደልሂ በሚገኘው የማይደን ፋርማሱቲካልስ ፋብሪካ ውስጥ በርካታ የደህንነት ደንቦችን ተጥሰዋል ብለው በማመናቸው ሁሉንም የምርት እንቅስቃሴዎች አግደዋል።
"በተደረጉ ምርመራዎች ወቅት ከታዩት ተቃርኖዎች አሳሳቢነት እና በሚመረተው የመድኃኒት ጥራት፣ ደህንነት እና ውጤታማነት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው" ሲሉም የጤና ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።
አምራቹ ኩባንያ ሜይደን ከቢቢሲ አስተያየት እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
ባለፈው ሳምንት ኩባንያው "የህጻናቱን ህልፈት በተመለከተ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችን መስማቱን እና ይህም በጣም አስደንጋጭ መሆኑን ብሎም በክስተቱ ማዘኑን" ገልጿል።
የአለም ጤና ድርጅት ምርቶቹ በሽሮፖቹ ላይ በተደገረ ምርመራ ዳይታይለን ግላይኮል እና ኢታይለን ግላይኮል የተሰኙ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ንጥረ ነገሮች እንደተገኙ እና ንጥረ ነገሮቹም ኩላሊት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርሱ ይፋ አድርጓል።
ሽሮፖቹ ከጋምቢያ በተጨማሪ “መደበኛ ባልሆኑ ገበያዎች ወደ ሌሎች ሀገራት እና ክልሎች ተሰራጭተው ሊሆን ይችላል” ሲል አስጠንቅቋል።
የጋምቢያው ፕሬዝዳንት አዳማ ባሮው ባለስልጣናት በምርመራቸው "ምንም የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም" ብለዋል።
ጋምቢያዊያን የፍትህ ጥያቄ እያቀረቡ ሲሆን የጋምቢያ ፖሊስ የሕጻናቱን ህልፈት በማጣራትላይ ይገኛል።
የጋምቢያ ፖሊስ ማክሰኞ ዕለት ይፋ ባደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ የሳል ሽሮፑ ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር የሚያስመጣው ድርጅት ተቀማጭነቱ አሜሪካ መሆኑን አስታውቋል።
ወደ አገር ውስጥ ከገቡት የተበከሉ 50 ሺህ የሽሮፕ ጠርሙሶች መካከል አብዛኞቹ በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ዘገባው አመልክቷል።












