ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአርጀንቲና በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ግማሹ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ጉዳት ደረሰበት
በአርጀንቲና በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ግማሹ ብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል (ግሪድ) ጉዳት ደረሰበት።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በርካታ ከተሞች የኃይል መቋረጥ አጋጥሟቸዋል።
ዋና መዲናዋ ቦነስ አይረስን ጨምሮ በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች እና ሰፊ የገጠር አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸዋል።
እሳቱ ሜዳዎች ላይ የተነሳ ሲሆን በባህር ዳርቻ ዞን የሚገኙ ወሳኝ የኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ ጉዳት ማድረሱን እና በተጨማሪም የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያውን ከመስመር ውጭ እንዳደረገው ተነግሯል።
በአርጀንቲና ያጋጠመው ከባድ የኃይል መቋረጥ ሃገሪቱ በከፍተኛ ሙቀት በምትናወጥበትና በድርቅ ባለችበት ሁኔታ ነው።
ደቡብ አሜሪካዊቷ ሃገር በአሁኑ ወቅት የበጋ ወቅት ላይ ስትሆን በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የሙቀት መጠን ከ35 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ተመዝግቧል።
በሃገሪቱ ያለው ከፍተኛ ሙቀት ከኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ጋር ተደማምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ እንዲገታ አድርገውታል።
በዚህም ትምህርት ተቋርጧል፣ የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል እንዲሁም በርካታዎች ያለ አየር ማቀዝቀዣ ኑሮን እንዲገፉት ተገደዋል።
በኃይል አቅርቦት መቆራረጥ የከፋ ጉዳት የደረሰባቸው ዋና ዋና ከተሞች ሲሆኑ በቦነስ አይረስና አካባቢው 150 ሺህ የሚሆን ህዝብም በጨለማ ውስጥ ነው ተብሏል።
የኃገሪቱ የኢነርጂ ሚኒስቴር በቅርቡ የኃይል አቅርቦት ወደነበረበት እንደሚመለስ እርግጠኛ መሆኑን አስታውቋል።
በሃገሪቱ ውስጥ የኃይል መቆራረጥ የተለመደ ነው። በአውሮፓውያኑ 2019 በኃገሪቱ ባጋጠመው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስመር ብልሽት በአርጀንቲና እና በጎረቤት ኡራጓይ ውስጥ በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለጨለማ ዳርጓቸዋል።
እንዲሁም በአውሮፓውያኑ 2020 በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የቦነስ አይረስ ነዋሪዎች የኃይል አቅርቦት አጋጥሟቸዋል።