በአለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት የተከሰሰው ኬንያዊ ጠበቃ ሞቶ ተገኘ

ጠበቃ ፖል ጊቼሩ

በአለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በምስክሮች ጣልቃ ገብነት ክስ ቀርቦበት የነበረው ኬንያዊው ጠበቃ ፖል ጊቼሩ ሞቶ ተገኘ።

ፖሊስ እንዳስታወቀው ጠበቃው ፖል ጊቼሩ ሰኞ ምሽት በመዲናዋ ናይሮቢ በሚገኘው ቤቱ ሞቶ መገኘቱን አረጋግጧል።

ጠበቃው በአውሮፓውያኑ 2007 ምርጫ ማግስት ከተፈጠረው ሁከት ጋር በተያያዘ ለምስክሮች ጉቦ በመስጠት ነው ክስ የቀረበበት።

ምስክሮቹ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በአይሲሲ ተከሰው በነበረበት ወቅት ምስክርነት የሚሰጡ ግለሰቦች ምስክርነት የሚሰጡ ግለሰቦች እንደነበሩም ተገልጿል።

በዚህ ሁከት ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።ጠበቃው የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።

ጠበቃው የአይሲሲ የእስር ማዘዣ ካወጣበት ከአምስት ዓመት በኋላም በአውሮፓውያኑ 2020 ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል።

አቃብያነ ህግ እንደሚሉት ጠበቃው ፈጸመው በተባለው ተግባር ምክንያት ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በፍርድ ቤቱ የቀረቡባባቸውን ክሶች ውሃ እንዳይቋጥር አድርጎታል ብለዋል።

ዊሊያም ሩቶ በኬንያ ምርጫ ማግስት በተቀሰቀው ሁከት በተፈጸሙ ግድያዎች፣ ስወራ እና ማፈናቀል በአለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ተከሰው ነበር።

ዊሊያም ሩቶ እነዚህን ወንጀሎች አልፈጸምኩም በማለት በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

አይሲሲ በዊሊያም ሩቶ ላይ በቂ ማስረጃ ባለማግኘቱ ክሱን አቋርጧል።

በጠበቃው አሟሟት ላይ አንዳንድ ዝርዝር መረጃዎች እየወጡ ባለበት በአሁኑ ወቅት በአሟሟቱ ላይ ፖሊስ ፈጣን እና የተረጋጋጠ ምርመራ እንዲያደርግ የኬንያ የመብት ተቋማት ጠይቀዋል።