ከሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ስደተኝነት በአፍሪካ ቅጥረኛ ተዋጊ እስከመሆን

አቡ ሞሐመድ ከ10 ዓመታት በላይ በቆየው የሶሪኣ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በሰሜን የአገሪቱ ግዛት ከቤተሰቦቹ ጋር በድንኳን ለመኖር ተገዷል። ቤተሰቦቹን ለመደገፍ የሚሆን በቂ ገቢ ማግኘት አልቻለም።

ልክ በመቶዎች እንደሚቆጠሩ ሶሪያውያን በቱርክ በኩል ወደ ኒጀር አቀና። ዓላማው ደግሞ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይ ሆኖ ለመሥራት ወስኖ ነው።

የ33 ዓመቱ አቡ ሞሐመድ (ስሙ የተቀየረ) እና ባለቤቱ አራት ትንንሽ ልጆች አሏቸው። የባንቧ ውሃም ሆነ መጸዳጃ ቤት አልነበራቸውም። የስልካቸውን ባትሪ ለመሙላት የፀሐይ ኃይል ይጠቀማሉ። የሚኖሩባት ድንኳን በበጋ እሳት፣ በክረምት በረዶ፣ በዝናብ ወቅት ደግሞ የምታፈስ ነበረች።

“ሥራ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ሆኗል” ይላል አቡ ሞሐመድ። በቱርክ የሚደገፉ የተቃዋሚ ኃይሎች አባል ነው። ይህ ኃይል ከአስር ዓመታት በላይ ከፕሬዚዳንት ባሻር አል አሳድን ጋር ሲዋጋ ቆይቷል።

በወር 50 ዶላር የማይሞላ ገንዘብ ብቻ ይከፍለዋል። ኒጀር ውስጥ በመሥራት በወር አንድ ሺህ 500 ዶላር እንደሚከፈል የቱርክ ቀጣሪዎች ሲነግሩት የተሻለ ሕይወቱን የሚመራበት አጋጣሚ መሆኑን በማሰብ ለመቀበል አላመነታም።

የሶሪያ ቡድን መሪዎች ሂደቱን ለማመቻቸት እንደሚረዱት እና ከተለያዩ ወጪዎች የተረፈውን ቢያንስ ሁለት ሦስተኛውን ገንዘብ እንደሚያገኝ ተናግሯል። “[ኒጀር] ውስጥ በጦርነት ላይ ከሞትኩ ቤተሰቤ 50 ሺህ ዶላር ካሳ ያገኛሉ” ሲል ያክላል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምዕራብ አፍሪካ በሚገኘው የሳህል ቀጠና ከጂሃዲስቶች ጋር በተፈጠረ ግጭት ምክንያት ቀውሱ ተባብሷል። ኒጀርን ጨምሮ ጎረቤቶቿ ማሊ እና ቡርኪናፋሶ በዚህ ምክንያት ተጎድተዋል።

ሦስቱም አገራት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አጋጥሟቸዋል። ለዚህ ምክንያት ከሆኑት መካከል አንዱ በቀጠናው የተፈጠረው አለመረጋጋት ነው።

ወደ ኒጀር የመሄድ ፍላጎት ያሳየው አቡ ሞሐመድ ብቻ አይደለም።

በኢድሊብ ገጠራማ አካባቢው በድንኳን ውስጥ የሚኖረው አሊ (ትክክለኛ ስሙ አይደለም) የሶሪያን ተቃዋሚ ኃይሎች የተቀላቀለው ከ10 ዓመት በፊት በ15 ዓመቱ ነበር። እሱም በወር ከ50 ዶላር ያነሰ ደሞዝ እንደሚከፈለው ተናግሯል። ይህም ለአምስት ቀናት ብቻ የሚበቃው ነው።ቤተሰቡን ለመደገፍ ብድር ውስጥ መዘፈቅ ነበረበት።

የተጠራቀመ ዕዳውን ለመክፈል ደግሞ ወደ ኒጀር መጓዝ ብቸኛ አማራጩ ሆነ። “የውትድርና ሙያዬን አርግፍ አድርጌ ትቼ የራሴን ቢዝነስ መጀመር እፈልጋለሁ” ይላል።

የ22 ዓመቱ ራኤድ (ስሙ የቀየረ) የተቃዋሚው ኃይል ተዋጊ ነው። ወደ ኒጀር መሄዱ “የማግባት እና ቤተሰብ የመመሥረት ህልሜን ለማሳካት” የሚያስችለውን በቂ ገንዘብ ለማሰባሰብ ብቸኛው መንገድ ሆኖ ይሰማዋል።

ከአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2023 ጀምሮ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ የሶሪያ ተዋጊዎች በቱርክ በኩል ወደ ኒጀር ተጉዘዋል ሲል መቀመጫውን ብሪታኒያ ያደረገው የሶሪያ የሰብአዊ መብቶች ታዛቢ (ኤስኦኤችአር) አስታውቋል።

ተቋሙ የሶሪያን ግጭት በቦታው ባሉ የመረጃ ምንጮች አማካኝነት ይከታተላል። ለስድስት ወራት ብለው ቢመዘገቡም አንዳንዶቹ ግን ውሉን ወደ አንድ ዓመት አራዝመዋል።

የሚገባላቸው ቃል

ከመሄዳቸው በፊት የሚነገራቸው ኦፊሴላዊው መረጃ ኒጀር የሚገኙ የቱርክ ፕሮጀክቶችን እና ቢዝነሶችን ትጠብቃላችሁ የሚል ነው።

ቱርክ በአካባቢው ያላትን ፖለቲካዊ ተጽእኖ እና የንግድ እንቅስቃሴ አስፋፍታለች። ለኒጀር ታጣቂ የጂሃዲስቶችን ለመዋጋት የሚረዳትን እንደ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ያሉ የጦር መሳሪያዎችን ትሸጣለች።

በተጨማሪም እንደ ወርቅ፣ዩራኒየም እና የብረት ማዕድን ያሉ የአገሪቱን የተፈጥሮ ሃብቶችን በማውጣት ላይም ትገኛለች።

ነገር ግን የተነገራቸው እና ኒጀር ሲደርሱ የሚያገኙት እውነታው ለየቅል ይሆንባቸዋል።

ኤስኦኤችአር እና በኒጀር ሠርተው የሚያውቁ የቅጥረኞቹ ጓደኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ ሶሪያዊያኑ በኒጀር፣ በማሊ እና በቡርኪናፋሶ መካከል ባለው የድንበር አካባቢ በሚንቀሳቀሰው እና በሩሲያ ዕዝ ስር በመሆን ጂሃዲስቶችን እንዲዋጉ ይደረጋል።

በኒጀር በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዞም ከአንድ ዓመት በፊት ከሥልጣን ተወግደዋል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የአገሪቱ ጦር ከምዕራባውያን ጋር ያለውን ግንኙነት አቋርጧል።

በኦክስፎርድ አናሊቲካ የሳህል ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ናትናኤል ፓውል “ኒጀር አዳዲስ አጋሮችን ስትፈልግ ሩሲያ ጥሩ አማራጭ ሆና አገኘቻት” ብለዋል።

“የሩሲያ የጦር መሳሪያዎች ከምዕራባውያን አንጻር ርካሽ ናቸው። ሩሲያ ወታደራዊ ድጋፍ እና ሥልጠናም ትሰጣለች። ከምዕራቡ ዓለም በተለየም ከባድ መስፈርት ሳይደረድሩ አብረው ይሠራሉ” ሲሉ አክለዋል።

ሩሲያ - ቱርክ - ሶሪያ

ሩሲያ የፕሬዚዳንት አሳድን ጠንካራ ደጋፊ ናት። ከሶሪያ መንግሥት ጋር ሲፋለሙ ለነበሩት ቅጥረኞች አሁን በሩሲያ ስር መሆን ሌላ አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል።

“እኛ እዚህ ቅጥረኞች ነን፤ እዚያም ቅጥረኞች ነበርን። አሁን የቱርክ ተልዕኮ ላይ ነኝ። ከሩሲያውያን ትዕዛዝ አልቀበልም” ብሏል አቡ ሞሐመድ።

ራኤድ እንደሚለው ደግሞ ምንም ምርጫ ላይኖረው ይችላል። “እነዚህን ኃይሎች ብጠላም ግን በኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች መሄድ አለብኝ” ይላል።

ሁሉም ውላቸውን ለመፈረም እየጠበቁ ናቸው። ውሉ መፈረም ያለበት “ከጉዞ በፊት ወይም በጉዞ ወቅት” መሆኑን ራኤድ ይናገራል። ሂደቱ ምሥጢራዊ እንደሆነ እና “በአፍሪካ ስላለው ዘመቻ እና የምዝገባ ዘዴ አንዳንድ ጉዳዮችን በማውጣቱ” ምክንያት በሶሪያ ተቃዋሚ ቡድን የታሰረ አንድ ሰው እንደሚያውቅም ያስረዳል።

ያነጋገርናቸው ተቀጣሪዎች መሪዎቻቸው ሳዳት የተባለ የቱርክ ኩባንያ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ እንደሚጠብቃቸው እና ሌሎች የጉዞ ሎጂስቲክስ ዝግጅት እንደሚያመቻች እንደነገሯቸው ገልጸዋል።

የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ አቡ መሐመድ ወደ ሊቢያ ሄዶ ለስድስት ወራት በቅጥረኛ ተዋጊነት ሲሠራም በሳዳት ሁሉ ነገር ተዘጋጅቷል ብሏል።

ኤስኦኤችአር አክሎም ወደ ኒጀር ከሄዱ ሌሎች ቅጥረኞች ባገኙት መረጃ መሠረት ሳዳት በሂደቱ ውስጥ እንደሚሳተፍ ገልጿል።

ቢቢሲ ይህንን ማረጋገጥ አልቻልንም። ቢቢሲ ሳዳትን ጠይቆ የሶሪያ ተዋጊዎችን ወደ ኒጀር መመልመሉን ወይም ማሰማራቱን አጥብቆ ክዷል። ክሶቹ “ከእውነት ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም… ኒጀር ውስጥ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አናደርግም” ሲል አክሏል።

ከአስር ዓመታት በፊት በሊቢያ ከነበረው “ወታደራዊ ስፖርት” ፕሮጀክት ውጪ ሊቢያ ውስጥ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንደሌለው ተናግሮ በአገሪቱ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት መውጣትን አስታውቋል።

ኩባንያው አክሎም "መንግሥታዊ ላልሆኑ አካላት አገልግሎት አልሰጥም” ከማለት በተጨማሪ “በቱርክ ሕግ መሠረት በመከላከያ እና በደኅንነት መስክ ለታጣቂ እና ለፀጥታ ኃይሎች የምክር፣ የሥልጠና እና የሎጂስቲክስ አገልግሎቶችን እሰጣለሁ” ብሏል።

የሶሪያን ቅጥረኞች ወደ ኒጀር ለመመልመል እና ለመላክ በአንካራ የሚገኘው መንግሥት የግል ኩባንያዎችን ይጠቀማል ሲል ኤስኦኤችአር ገልጿል። የድርጅቱ ዳይሬክተር ራሚ አብዱል ራህማን የቱርክ መንግሥት ሶሪያውያንን ያለ ምንም ገንዘብ እና በአስከፊ የኢኮኖሚ ተስፋ እየበዘበዘ ነው ሲል ይከሳል።

ቢቢሲ እነዚህን ክሶች ለቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።

የቱርክ መንግሥት የሶሪያ ተዋጊዎችን ወደ ውጭ በመላክ ሲከሰስ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትርን ጨምሮ በርካታ ሪፖርቶች በሊቢያ በቱርክ የሚደገፉ የሶሪያ ተዋጊዎች መኖራቸውን ዘግበዋል።

ቱርክ ቀደም ሲል የሶሪያ ተዋጊዎች ቢሊቢያ እንደነበሩ አምና በምልመላው መሳተፏን ግን አልተቀበለችውም። በካውካሰስ ወደሚገኘው አወዛጋቢው የናጎርኖ ካራባክ ክልል የሶሪያ ቅጥረኞችን መልምላ ማሰማራቷንም አስተባብላለች።

አስቸጋሪው ሁኔታ እና የቤተሰብ ፍላጎት

በኒጀር ሲሰማሩ በሶሪያ ካሉ ቤተሰቦች ጋር መገናኘት በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል። ቅጥረኞቹ ኒጀር ሲደርሱ ስልኮቻቸው ይወሰድባቸዋል ሲል የኤስኦኤችአር ባልደረባ የሆኑት አብዱል ራህማን ተናግረዋል።

አቡ ሞሐመድ በበኩሉ በአፍሪካ ያሉ ጓደኞቹ “በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ቤተሰቦቻቸውን ማነጋገር ይችላሉ። አንዳንዴም በሁለት ሳምንት አንዴም ላይሳካ ይችላል” ብለዋል።

ከሚስቶቻቸው ወይም ከወላጆቻቸው ጋር ራሳቸው መነጋገር እንደማይችሉ እና ለመነጋገር በኒጀር ውስጥ ባሉ አለቆቻቸው በኩል መሄድ ያለበት ሲሆን አለቆቹም “የተዋጊዎቹን ቤተሰቦች ደህና መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።”

አሊ አክሎም ወደ ኒጀር የተጓዙ አንዳንድ ጓደኞቹ አብዛኛውን ጊዜያቸውን “በወታደራዊ ካምፖች ውስጥ፣ ለመዋጋት ትዕዛዝ በመጠባበቅ” እንደሚያሳልፉ ነግረውታል።

ሁሉም ወደ አገራቸው በሕይወት አይመለሱም። እንደ ኤስኦኤችአር ዘገባ ከሆነ ከታኅሣሥ 2023 ጀምሮ በኒጀር ዘጠኝ ሶሪያውያን ተገድለዋል። የአራቱ አስከሬኖች ወደ ኢድሊብ ቢመለሱም ግን እስካሁን ማንነታቸው አልተለየም።

ራኤድ እና አሊ ቤተሰቦቻቸው እዚህ ውስጥ እንዲገቡ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ በመግለጽ በቱርክ ውስጥ ለጥቂት ወራት ሥልጠና እንደሚሄዱ ሊዋሹ ይችላሉ።

የአቡ ሞሐመድ ቤተሰቦችም ሃሳቡን አይደግፉትም። “ጥሩ ኑሮ ለመኖር የሚያስችል አቅም ቢኖረኝ ኖሮ አንድ ሚሊዮን ዶላር ብታቀርብልኝ እንኳን እንዲህ ዓይነት ሥራ አልሠራም ነበር” ሲል ተናግሯል። ሆኖም “ልጄ ብስክሌት ቢጠይቀኝ የመግዛት አቅም የለኝም። እንድሄድ የሚገፋፉኝ እነዚህ ነገሮች ናቸው” ሲል አክሏል።