ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሴቶች ከወንዶች ያላነሰ አቅም እንዳላቸው የሚያወሳው “ማክዳ” የሙዚቃ አልበም
ገብርኤላ ጋሄርማንዲ በውጪ መንግሥታት በገንዘብ ይደገፍ የነበረውን “የኛ” የተባለውን የሙዚቃ ቡድን የኢትዮጵያን ሴቶችን ትርክት በሙዚቃ ለመቀየር ይሰራል መባሉን ስትሰማ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል” ስትል እራሷን ጠይቃ ነበር።
በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ዝነኛ የነበረው የኛ የተባለው የአምስት ሴት ሙዚቀኞች ቡድን በዩናይትድ ኪንግደም መነጋጋሪያ ሆኖ ነበር።
“የኢትዮጵያ ስፓይስ ገርስልስ” የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ቡድን ከፍተኛውን የገንዘብ ድጋፍ ያገኝ የነበረው ከዩኬ መንግሥት ስለነበረ፤ ብዙዎች የግብር ከፋዮች ገንዘብ በሚገባው ቦታ ወጪ እየሆነ ነው የሚል ጥያቄ ሲያነሱ ነበር።
በገብርኤላ አእምሮ ውስጥ ግን የተፈጠረው ዋነኛ ጥያቄ ኢትዮጵያውያንን ከውጪ በመጡ ሰዎች ለማንቃት የሚደረገው ጥረት ትክክል ነው ወይ የሚለው ነበር።
ገብርኤላ በዩኬ “የኢትዮጵያ ስፓይስ ገርልስ” ጉዳይ መነጋገሪያ መሆኑን ስትሰማ፤ “ምን? ሴቶችን እንዴት ማብቃት እንዳለብን ለኛ ሊያስተምሩ? ኢትዮጵያን ሊያስተምሩ? እነዛ ሁሉ አስደናቂ ሴቶች እያሉን?” ስትል ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቃለ መጠይቅ ጠይቃለች።
ትውለደ ኢትዮጵያዊቷ የጣሊያን ዜጋ ገብርኤላ ሙዚቀኛ እና የሙዚቃ ፕሮዲዩሰር ነች።
“በታሪካችን ከወንዶች ያላነሰ አቅም ያላቸው ጀግና የሆኑ ሴቶች እንዳሉን ለዓለም የሚገልጽ ነው” ያለችውን አልበም በቅርቡ አውጥታለች።
9 ሙዚቃዎችን የያዘው አልበም መጠሪያውን ያገኘው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ከሚሰጣት ማክዳ ነው።
በአልበሙ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ዘፈን ምሳሌ የሚደረጉ ሴቶችን እና የማኅብረሰብ ክፍሎችን የሚያወድስ ነው።
ገብርኤላ ብዙዎች ይህን አልበም “ኢትዮ-ጃዝ” ነው ይሉታል ትላለች። እርሷ ግን አልበሟ ከኢትዮ-ጃዝ በላይ ነው ትላለች።
“መሠረቱን በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ያደረገ ነው። ነገር ግን ሌሎች ስልቶችም ተካተዋል። የሮክ ስታይልንም ይዟል። አልበሙ ውስጥ ሁሉንም ነገር ማግኘት ይቻላል” ትላለች።
የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ሙዚቀኞች አራት ዓመታትን ወስደው ማክዳ አልበምን ሰርተዋል።
ሁለቱ አገሮቼ (ኢትዮጵያ እና ጣሊያን) አንድ እንዲሆኑ በጣም ስለፈለኩ በአልበም ስራው የተሳተፉ ሙዚቀኞች በሙሉ በሙዚቃ አሬንጅመንት ስራው ላይ እንዲሳተፉ አድርጊያለሁ ትላለች።
ከጣሊያዊ አባት እና ከኢትዮጵያዊት እናት እአአ በ1965 በአዲስ አበባ የተወለደችው ገብርኤላ በአዲስ አበባ የነበራትን የልጅነት ጊዜ ስታስታውስ፤ “እያንዳንዱ ሰፈር በሙዚቃ እና ጭፈራ የተሞላ ነበር። በደሜ ውስጥ የቀረውን የሙዚቃ ስልት የተዋወቅኩት በዚያ ይመስለኛል” ትላለች።
ገብርኤላ ልጅ ሳለች ከታላላቅ ውንድሞቿ ጋር ትሄድ በነበረበት የመዝናኛ ስፍራ እውቁ ናይጄሪያዊ ፌላ ኩቲን ጨምሮ በርካቶች የሙዚቃ ስራቸውን ያቀርቡ ነበር።
ገብርኤላ ምንም እንኳ መደበኛ የሆነ የሙዚቃ ትምህርት ባትማርም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ስልት በፍቅር የወደቀችው በዕለት ተዕለት ሕይወቷ ከታደመችባቸው ሠርግ ቤቶች እና ከቤተ-ክርስቲያን ውሎ መሆኑን ታስረዳለች።
ከዚህ በተጨማሪ ገብርኤላ በአባቷ ምክንያት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውራ መኖሯ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ስልት እንድትረዳው ረድቷታል።
የገብርኤላ አባት እአአ 1935 በጣሊያን ቅኝ ግዛት ስር ወደ ነበረችው ኤርትራ ለሥራ ይመጣል። እአአ 1955 ላይ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ይዘዋወራል። በዚያም ከገብርኤላ እናት ጋር ይተዋወቃል።
በግንባታ ስራ ላይ የተሰማራው የገብርኤላ አባት ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍል መዘዋወሩ ገብርኤላ በርካታ የኢትዮጵያን ክፍሎች በልጅነት ዕድሜዋ እንደትጎበኝ እድል ሰጥቷታል።
የገብርኤላ አባት እአአ 1978 ያርፋል። ወቅቱ የደርግ መንግሥት ኢትዮጵያን የሚያስተዳድርበት ጊዜ ነበር። በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የነበረችው ገብርኤላ ወደ ጣሊያን ተሰደደች።
ይሁን እንጂ በልጅት እድሜዋ በፍቅር የወደቀችለት የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሁሌም በልቧ እንዳለ ነው። ማክዳ የተሰኘው አልበሟን ስትሰራ ወደ ገጠማራ የኢትዮጵያ ክፍል አምርታለች።
አንደኛ መዳረሻዋ ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የዶርዜ ማኅብረሰብ ነው። በዚህ ማኅብረሰብ ውስጥ መሪ የሆኑ ሴቶች በጋሞኛ አስደናቂ የሆነ ኅብረ ዝማሬን ታስታውሳለች።
በገብርኤላ አልበም ውስጥ ከተካተቱ ሙዚቃዎች አንዱ ‘ሴት ናት’ የሚለው ዘፈን ይገኘበታል። ገብርኤላ በዚህ ሙዚቃዋ “ለመላው ዓለም ሴት መሆን ብቻ ከበቂ በላይ መሆኑን መናገር እፈልጋለሁ” ትላለች።
ሌላኛው በዚህ አልበም የተካተተው ሙዚቃ ደግሞ ኮትሊዳ የተባለው የኩናማ ሙዚቃ ነው። በሙዚቃው ውስጥ የኩናማ ሕዝብ የሚጠቀምበት አቫብጋላ የተባለ የሙዚቃ መሳሪያን ተጠቅማለች።
“የኢትዮጵያን ባሕላዊ ሙዚቃ መሳሪያ ከዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪዎች ጋር አደባልቆ መስራትን በጣም እፈልጋለሁ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቴ የኢትዮጵያን ባሕላዊ የሙዚቃ መሳሪያ ከአገር ውጪ ለማስተዋወቅ የሚደረገው ጥረት በጣም አስተኛ ስለሆነ ነው” ትላለች።
ሳባ የሚለው ሙዚቃዋ ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ስሟ በስፋት የሚነሳውን ንግሥተ ሳባ፤ ንጉሥ ሰለሞንን ለማግኘት በግመል ያደረገችውን ጉዞ ያወሳል።
የሙዚቃው ማሲንቆ ከአይሁድ የሙዚቃ ዜማ ጋር ተዋህዷል።
“በሙዚቃዎቼ የጉዞ፤ የመራመድ ሃሳብ አለ - በጉዟችን ወቅት የሚገጥሙን ነገሮችን በሙዚቃ የማዋሃድ ሃሳብ” ትላለች ገብርኤላ።