ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የውጭ የምግብ አቀነባባሪ ኩባንያ ፍላጎት በማሳየቱ የሽሮ ወጥ ደረጃ መዘጋጀቱ ተገለጸ
የውጭ አገር የምግብ አቀናባሪ ኩባንያ ሽሮ ወጥን በኢትዮጵያ ውስጥ በፋብሪካ ደረጃ አዘጋጅቶ ለማቅረብ ፍላጎት መኖሩን ተከትሎ የሽሮ ወጥ ደረጃ ማዘጋጀት ማስፈለጉን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ ከሽሮ ወጥ በተጨማሪ ወደ ውጭ አገራት የሚላኩ የተለያዩ “አገር በቀል ምርቶችን” የምግብ ደኅንነት እና የምርቱን ምንነት እና ይዘት ለማሳወቅ ደረጃዎች እያወጣ መሆኑንም ለቢቢሲ አመልክቷል።
ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን መሠረት በማድረግ የምግብ ይዘታቸው ላይ ጥናት ተደርጎባቸው ደረጃቸው ወጥቷል የተባሉ ምርቶች ሽሮ፣ በርበሬ፣ በሶ እና ጠጅን ያካትታል።
ባለፈው ዓመት ደረጃቸው የወጣላቸው የምግብ ምርቶቹ “ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ” ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆን፣ ደረጃቸውም አስገዳጅ አለመሆኑን ኢንስቲትዩቱ ለቢቢሲ ገልጿል።
የሽሮ ዱቄት ደረጃ ሦስት ክፍሎችን የያዘ መሆኑን የተናገሩት የኢንስቲትዩቱ የደረጃዎች ዝግጅት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይልማ መንግሥቱ፤ የምግብ ይዘቱን እና እርጥበቱን፣ ሲፈጭ እና ሲታሸግ ያለው ንክኪ እንዲሁም በእሽጉ ላይ ምንነቱን እና የመጠቀሚያ ጊዜውን የሚይዝን መግለጫ ያካተተ ነው ብለዋል።
የማኅበረሰቡ አኗኗር እየተለወጠ በመሆኑ ሽሮን ከማዘጋጀት ይልቅ መግዛት በመለመዱ ደረጃውን ማውጣት “ወሳኝ” እንደሆነም ኃላፊው ገልጸዋል።
የራሱ የሆነ ምግብ ሂደትን አልፎ እና ተጨማሪ ግብዓቶችን ተጠቅሞ ለምግብነት የሚውለው ሽሮ ወጥም ጥራቱ እና ደኅንነቱ እንዲጠበቅ ደረጃ እየተዘጋጀለት መሆኑንም አስረድተዋል።
“የወጡ የምግብ ይዘት መታወቅ አለበት። ምን አለው ውስጡ? ያለው ፕሮቲን? በተመሳሳይ ሲቁላላ ወይም ሲበስል፣ ሲታሸግ ወይም በምርት ሂደቱ ላይ የሚመጡ የጤና ጎጂ ነገሮችን የምንከላከልበት [ነው]” ሲሉ ስለ ሽሮ ወጥ ደረጃ አቶ ይልማ ተናግረዋል።
ደረጃው የጨው መጠኑ፣ የመጠቀሚያ ጊዜው፣ ለማቆያ ተብለው ጥቅም ላይ የሚውሉ ንጥረ ነገሮችን ጨምሮ ወጡ ላይ የሚጨመሩ ግብዓቶች የምግብ ደኅንነትን መከተሉን የሚያረጋግጥ መሆኑን ተገልጿል።
“[እሽጉ ላይ] የምግብ ይዘቱ በትክክል መታወቅ አለበት። ያመረተው አካል፣ ግብዓቶቹ፣ የመጠቀሚያ ጊዜው (Expired Date)፣ እርጥበቱ የመሳሰሉ ነገሮች አብረው ይገለጻሉ።”
ይህም የሚሆነው የተጠቃሚውን ደኅንነት ከመጠበቅ ባለፈ አገሪቱ እሴት ጨምራ ምርቶችን ወደ ውጭ እንድትልክ ያበረታታል ሲሉ ስለ ደረጃው ኃላፊው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ደረጃ አለመኖሩ “አስቸጋሪ” ነው ያሉት አቶ ይልማ፤ የሽሮ ወጥ ደረጃ ምግብ ማቀነባበር ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችን ለመሳብ እንዲያስችል እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ጥያቄ አቅራቢነት እየተዘጋጀ ነው የተባለው የሽሮ ወጥ ደረጃ፤ ወጡን አምርቶ ለመሸጥ ከጃፓን ኩባንያ ፍላጎት እንደታየም ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“. . . አንድ የጃፓን ኩባንያ እና የእኛ ኢንዱስትሪ ፓርክ ቢሾፍቱ ላይ ማምረቻ ለማቋቋም በሂደት ላይ ነው ያሉት። ኩባንያው በዋናነት መነሻ ያደረገው ደረጃውን ያሟላ የሽሮ ወጥ ምርትን አዘጋጅቶ፤ አሽጎ ማቅረብ ነው። ስለዚህ [ደረጃው የሚወጣው] ይህን ፍላጎት ለማገዝ ነው” በማለት የነበሩ ዝግጅቶች በመጥቀስ የሽሮ ወጥ ደረጃ ማውጣት ለምን ቅድሚያ እንደተሰጠው ገልጸዋል።
ደረጃው ምግብ ኢንዱስትሪውን ለመቀየርም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኖበታል።
ከኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ባለስልጣን፣ ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከተለያዩ ተቆጣጣሪ አካላትን እና ከትምህርት ተቋማት እንዲሁም ቤተ ሙከራዎችን በአባልነት የያዘው የባለሙያዎች ኮሚቴ ረቂቅ ደረጃውን አዘጋጅቶ መጨሱም ተነግሯል።
ረቂቅ ደረጃው ለ60 ቀናት የሕዝብ አስተያት ክፍት ከተደረገ በኋላ ለደረጃዎች ምክር ቤት ቀርቦ ሲጸድቅ ለተቆጣጣሪ አካላት እንደሚቀርብ ተናግረዋል።
የደረጃውን አስገዳጅነት በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ይልማ ኢንስቲትዩቱ “አስገጃጅ አደረገውም፤ አላደረገውም በምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አዋጅ መሠረት [ግን] አስገዳጅ ነው” ብለዋል።
በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከእንጀራ ጋር በመቅረብ ዋነኛው የምግብ አካል የሆነው የሽሮ ወጥ ደረጃ እየተዘጋጀለት መሆኑ ከተነገረ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ ሽሮ ወጥን ብቻ በማዘጋጀት የሚያቀርቡ ምግብ ቤቶች በመላው አገሪቱ በስፋት የሚታዩ ሲሆን፣ ዋጋውም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ይታወቃል።