ተቃውሞን ተከትሎ ሕንድ የበርካታ ታዋቂ ሙስሊሞችን ቤት አፈረሰች

በነብዩ መሐመድ ላይ የተቃጡ ናቸው በተባሉ አሉታዊ አስተያየቶች ምክንያት ከተቀሰቀሰ ረብሻ ጋር ግንኙነት አላቸው ያሏቸውን የበርካታ ሙስሊሞች ቤቶችን የሕንድ የፀጥታ ኃይሎች አፍረሱ።

በኡታር ፕራዴሽ ግዛት የሚገኙት የቤቶቹ ባለቤቶች ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ተስጥቷቸው ነበር።

ሁለት የሕንድ ገዢ ፓርቲ ቢጄፒ ፓርቲ አመራሮች ፀረ እስልምና አስተያየቶችን ከሰጡ በኋላ ባለፈው ሳምንት ሕዝበ ሙስሊሙ ተቃውሞውን ሲያሰማ ቆይቷል።

ከሁከቱ ጋር በተያያዘ ፖሊስ ከ300 በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

እነዚህ አስተያየቶች የተሰጡት በግንቦት ወር በቲቪ ክርክር ወቅት የቢጄፒ ቃል አቀባይ በሆኑት ኑፑር ሻርማ ነው። የግለሰቧ አስተያየት አጸያፊ በመሆኑ ምክንያት ቢቢሲ ላይደግመው ወስኗል።

አስተያየቱ በሕንድ ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮችንና በርካታ እስላማዊ መንግሥታትን አስቆጥቷል። የፓርቲው የደልሂ ሚዲያ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ናቪን ኩማር ጂንዳል ይህንን አሉታዊ አስተያየት በትዊተር ገጻቸው በማጋራታቸው ተባረዋል።

የሁለቱ አስተያየት (በተለይም የሻርማ) በአንዳንድ የሕንድ ግዛቶች ተቃውሞ አስነስቷል።

የኡታር ፕራዴሽ ግዛት ዋና ሚኒስትር ዮጊ አድትያናት በባለፈው ሳምንት ሁከቱ ተሳትፈዋል የተባሉ ግለሰቦች እና ሕገ-ወጥ ቤቶች እንዲፈርሱ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን የግዛቱ የቢጄፒ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

ታዋቂው 'ሂንዱስታን ታይምስ' ጋዜጣ እንደዘገበው ቤታቸው ከፈረሰባቸው አንዱ ታዋቂ የሆኑት ጃቪድ አሕመድ የተባሉ ፖለቲከኛ ናቸው። ሴት ልጃቸው አፍሪን ፋጢማ ደግሞ ታዋቂ የሙስሊም መብት ተሟጋች ነች።

ባለፈው ሳምንት ከጁምአ ሶላት በኋላ ድንጋይ ወርውረዋል የተባሉ የሁለት ግለሰቦች ንብረትም ፈርሷል።

የዮጊ አድቲያናት የሚዲያ አማካሪ ምሪትዩንጃይ ኩማር በትዊተር ገጻቸው ላይ ቡልዶዘር ህንፃን ሲያፈርስ የሚያሳይ ፎቶግራፍ ለጥፈው “ሕገወጦች ሁሌም ያስታውሱታል፣ ከእያንዳንዱ አርብ በኋላ ቅዳሜ ይከተላል" ሲሉ አስፍረዋል። 

የቤቶቹን መፍረስ ሰፊ ውግዘትን አስከትሏል።

ተቺዎች ሻርማ እና ጂንዳል የሰጡት አስተያየት አገሪቱ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየገጠማት ያለውን ጥልቅ የሃይማኖት ጽንፍ ያሳያል ይላሉ።

እአአ በ2014 ቢጄፒ ወደ ሕንድ የመሪነት ሥልጣን ከመጣ በኋላ ሙስሊሞች ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ንግግርና ጥቃቶች ጨምረዋል።