ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ በዩክሬን ዙሪያ ለመነጋገር ከፑቲን ጋር ዳግም እንደሚገናኙ ተናገሩ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት "ትልቅ እመርታ" መገኘቱን እና ሐንጋሪ ውስጥ በአካል ለመገናኘት መስማማታቸውን ተናገሩ።
ከነሐሴ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው የስልክ ውይይት "ውጤታማ ነበር" ያሉ ሲሆን፤ የዋሽንግተን እና የሞስኮ ተወካዮች በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚገናኙም ተናግረዋል።
ትራምፕ በቡዳፔስት ከፑቲን ጋር የሚገናኙበትን ትክክለኛ ቀን አላረጋገጡም።
ክሬምሊን "እጅግ ግልጽ እና ታማኝነት" ከነበረው የስልክ ውይይት በኋላ መሪዎቹ ስለሚገናኙበት ሁኔታ "በፍጥነት" የዝግጅት ሥራ ይጀምራል ብሏል።
ውይይቱ የተካሄደው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ዋይት ሐውስን ከመጎብኘታቸው ከአንድ ቀን በፊት ነው።
ትራምፕ ለዩክሬን የቶማሃውክ ሚሳኤሎች ስለማስታጠቅ እያሰቡ ነው። ሚሳኤሉ ሩሲያ ድንበር ውስጥ ዘልቆ ሊመታ ይችላል።
ዜሌንስኪ አሜሪካ እንደደረሱ ሞስኮ "ስለ ቶማሃውክ እንደሰማች ውይይቱን ለመቀጠል እየተጣደፈች ነው" ብለዋል።
የስልክ ጥሪው መጠናቀቅን ተከትሎ ትራምፕ ትሩዝ በተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ "ከዩክሬን ጋር ያለው ጦርነት ማብቃት በኋላ በሩሲያ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ስለሚኖረው የንግድ ልውውጥ በስፋት ተነጋግረናል" ሲሉ ጽፈዋል።
የሁለቱም አገራት "ከፍተኛ አማካሪዎች" በሚቀጥለው ሳምንት ትክክለኛው ስፋራው ባልተገለጸ ቦታ እንደሚገናኙ ገልጸው፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የአሜሪካን ልዑካንን ይመራሉ ብለዋል።
ትራምፕ አርብ ዕለት ከፑቲን ጋር ስላደረጉት ንግግር ዜሌንስኪን እንደሚያወያዩ ተናግረው "በዛሬው የስልክ ውይይት ትልቅ እመርታ እንደተገኘ አምናለሁ" ሲሉ አክለዋል።
በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "በሁለት ሳምንታት ውስጥ" ከፑቲን ጋር እንደሚገናኙ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።
ከፑቲን ጋር ካደረጉት የስልክ ጥሪ በኋላ ሚሳኤሎቹን ለዩክሬን የመስጠት ዕድልን በተመለከተ የተጠየቁት ትራምፕ፤ "አሜሪካ የቶማሃውክስ ክምችቷን ማሟጠጥ አይገባትም። እኛም እንፈልጋለን...ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ምን ማድረግ እንደምንችል አላውቅም" ብለዋል።
በአሜሪካ የዩክሬን አምባሳደር ኦልጋ ስቴፋኒሺና በበኩላቸው ከሁለቱ መሪዎች የስልክ ውይይት በፊት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ጥቃት "ሞስኮ ለሰላም ያላትን ትክክለኛ አመለካከት የሚያጋልጥ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ በሰጡት መግለጫ "እነዚህ ጥቃቶች የሞስኮ ስትራቴጂ የሽብር እና የማዳከም መሆኑን ያሳያሉ። ብቸኛው ውጤታማ ምላሽ በጠንካራ ማዕቀብ፣ በተጠናከረ የአየር መከላከያ እና የረጅም ርቀት ሚሳኤል አቅርቦት ግፊት ማድረግ ነው። "
የሐንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ኤክስ ላይ የታቀደው የቡዳፔስት ስብሰባ "ሰላም ወዳድ ለሆኑ የዓለም ሕዝቦች ታላቅ የምስራች" ነው ሲሉ ጽፈዋል።
ቀደም ብለውም "ሰላም ትዕግስትን፣ ጥንካሬን እና ትህትናን ይጠይቃል። አውሮፓ አቋሟን መቀየር አለባት። የማያልቅ ጦርነትን ከማባባስ ይልቅ ከሩሲያ ጋር ድርድር ያስፈልገናል። በአህጉራችን ሰላም የሚያመጣው ውይይት ብቻ ነው።"
በነሐሴ ወር በአላስካ በተካሄደው የመሪዎች ስብሰባ ሰላም ስምምነትን ለመድረስ የተደረገው ጥረት ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ ትራምፕ ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ ተገደዋል።
ሁለቱ መሪዎች አሜሪካ በተገናኙበት ወቅት የአሜሪካው ፕሬዝደንት የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም የሩስያው ፕሬዚደንት ወደ ሁለንተናዊ የሰላም ድርድር እንዲገቡ ለማሳመን እንደሚችሉ ተስፋ አድርገው ነበር። ሩሲያ እአአ ከየካቲት 2022 ጀምሮ በዩክሬን ላይ ወረራዋን ጀምራለች።
ከቀናት በኋላም ትራምፕ ፑቲንን ለማናገር ከዜሌንስኪ እና ከአውሮፓ መሪዎች ጋር ያደረጉትን ስብሰባ እስከማቋረጥ ደርሰው ነበር።
ከዚያን ወዲህ ዋይት ሐውስም ሆነ ክሬምሊን በሁለቱ መሪዎች መካከል ግንኙነትን ስለመኖሩ በይፋ አላረጋገጡም።
ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው በቀናት ውስጥ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ማስቆም እንደሚችሉ ቢገልጹም፤ በኋላ ላይ ግን ጉዳዩ ፈታኝ መሆኑን አምነዋል።
ትራምፕ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበለጠ ለሩሲያ አዛኝ ሆነው ይታዩ ነበር። ከዜለንስኪ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሻከሮ እአአ የካቲት 28 ምክትል ፕሬዝዳነቱ ጄዲ ቫንስ ባሉበት ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን ከዜለንስኪ ጋር ያላቸው ግንኙነት በጣም ተሻሽሏል።
ትራምፕ መስከረም ላይ በግጭቱ ላይ ያላቸው ዕይታ መቀየሩን ጠቁመው ኪዬቭ "ዩክሬን ሁሉንም ግዛቶቿን ወደ ቀድሞ ሁኔታ መመለስ ትችላል" ብለው እንደሚያምኑ ገልጸው ነበር። ይህም ቀደም ሲል ኪዬቭ በሩሲያ የተወሰዱባትን ግዛቶች እንደማታገኝ አምና ትቀበል ካሉበት በእጅጉ የራቀ ነው።
ከጥር ወዲህ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ዋሽንግተን ያቀኑት ዜለንስኪ፤ በውይይታቸው የቶማሃውክ ሚሳኤሎች ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሊሆን ይችላል።
ዜለንስኪ 2,500 ኪሜ የሚጓዙ ሚሳኤሎች ለዩክሬን እንድትሰጣቸው ዩናይትድ ስቴትስን ጠይቀዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሚሳኤሎቹን ለዩክሬን ለመስጠት አስበው እንደሆነ ሲጠየቁ"እናየዋለን... ሊሆን ይችላል" ብለዋል።