የልማት ድርጅቶች ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መክፈል ያልቻሉትን 845 ቢሊዮን ብር ዕዳ መንግሥት ሊከፍል ነው

የንግድ ባንክ ዋና መስርያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው መክፈል ያልቻሉትን 845 ቢሊዮን ብር ዕዳ መንግሥት በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊከፍል ነው።

የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ዶ/ር እዮብ ተካልኝ “በአገር ውስጥ ካለው ኢኮኖሚ ገቢ ሰብስበን የምክከፍለው ነው የሚሆነው” ሲሉ ዕዳውን ለመክፈል የሚውለው ገንዘብ የሚገኝበትን ምንጭ ለምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ተጠቃሚው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሆነበት 900 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው የመንግሥት ዕዳ ሰነድ እንዲያወጣ ስልጣን የሚሰጥ አዋጅ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 26/ 2017 ዓ.ም በተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል።

አዋጁ የገንዘብ ሚኒስቴር ከሚያወጣው የመንግሥት ዕዳ ሰነድ ውስጥ 845 ቢሊዮን ብሩን “የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ያልከፈሉትን እዳ ለመክፈል እንዲያውል” ስልጣን ይሰጣል።

የመንግሥት ዕዳ ሰነድ አዋጅ የተሰኘው ሕግ ቀሪው 54 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል ክፍያ እንደሚውል ያትታል።

በአንድ ተቃውሞ እና በአብላጫ ድምጽ የጸደቀው ይህ አዋጅ፤ በሦስት ክፍሎች እና በስድስት አንቀጾች የተዘጋጀ ነው።

የመንግሥት ልማት ድጅቶቹ ባለፉት ዓመታት “ለሜጋ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ” ከንግድ ባንክ ብድር መውሰዳቸውን የአዋጁ ማብራሪያ ላይ ሰፍሯል።

ከመንግሥት የልማት ድርጅቶቹ ውስጥ ከፍተኛ ዕዳ ያለበት የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ነው። በአዋጁ ማብራሪያ መሰረት ወለዱን ጨምሮ የኮርፖሬሽኑ ዕዳ 191.79 ቢሊዮን ብር ነው።

ሌላኛው የመንግሥት የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ደግሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለት ዙሮች የተወሰደ እና ያልተከፈለ 110 ቢሊዮን ብር ዕዳ አለበት።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንም እንዲሁ በሁለት ዙሮች የወሰደው ብድር እና ከእነ ወለዱ 80 ቢሊዮን ብር ገደማ ነው።

ይህ ብድር “ለሜጋ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ” ቢወሰዱም “እነዚህ ሜጋ ፕሮጀክቶች ከጥናት ጀምሮ በርካታ የተወሳሰበ ችግር ያለባቸው በመሆኑ የውጭ አገርም ሆነ የአገር ውስጥ እዳቸውን ለመክፈል ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል” ሲል የአዋጁ ማብራሪያ ያትታል።

ይህ አዋጁ ማብራሪያ ሃሳብ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ላይ በገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ተስተጋብተዋል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች “ከፍተኛ የሆነ አሰራር ችግር የነበረባቸው [ነበሩ]” ያሉት ዶ/ር እዮብ፤ “ፕሮጀክቶች በአግባቡ ሳይጠኑ ወደ ሥራ የተገባባት ሁኔታ ነው የነበረው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህን ተከትሎም መንግሥት የልማት ድርጅቶቹ “በእዳ ጫና ምክንያት ያጋጠማቸውን ችግር በማቃለል አትራፊ ሆነው ስራቸውን መቀጠል እንዲችሉ” የወሰዱትን ብድር ተረክቦ የሚከፍል የእዳ እና የሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን መቋቋሙን የአዋጁ ማብራሪያ አስታውሷል።

ከአራት ዓመታት በፊት 2013 ዓ.ም. ዕዳ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የተቋቋመው ኮርፖሬሽኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱትን ብድር ከእነ ወለዱ የተከበው በሁለት ዙር ነበር።

ኮርፖሬሽኑ በ570 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል እንዲሁም በብር 142 ቢሊዮን የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመ ቢሆንም፤ መንግስት ከተከፈለው ካፒታል ውስጥ ማሟላት የቻለው 44 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑ ማብራሪያው ላይ ሰፍሯል።

ይህን ተከትሎም “ኮርፖሬሽኑ በታቀደው መሰረት ለእዳ ክፍያ ሊውል የሚችለውን ገንዘብ ባለማግኘቱ ሃላፊነቱን ሊወጣ ካለመቻሉም በላይ በብድሩ ገንዘብ ላይ ሊከፈል የሚገባው ወለድ እየተጠራቀመ ሄዷል” ይላል።

በዚህም ምክንያት “ያልተከፈለው ከፍተኛ እዳ ብድሩን ለመንግስት የልማት ድርጅቶች በሰጠው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፋይናንስ ገጽታ ላይ አሉታዊ ውጤትን በማስከተሉ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ይሆናል” ሲል ማብራሪያው ያትታል።

ዶ/ር እዮብ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, HoPR

የምስሉ መግለጫ, “ከውጭ የሚመጣ ብድር የለም በአገር ውስጥ ካለው ኢኮኖሚ ገቢ ሰብስበን የምክከፍለው ነው የሚሆነው” ዶ/ር እዮብ ተካልኝ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶ/ር አብዱልመናን መሐመድ “ፍጹም አግባብ ያልሆነ አሰጣጥ ነው የተሰጠው የብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች ፍጹም ለንግድ ባንክ እንዳይሰሩ ተደርገው” ሲሉ የልማት ድርጅቶቹ ብድሩን የወሰዱበትን አግባብ ተችተዋል።

ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ፓርላማ የተገኙት ዶ/ር እዮብ፤ “የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለእነዚህ የልማት ድርጅቶች ያበደረውን ገንዘብ የልማት ድርጅቶቹ ሰርተው መመለስ ስላልቻሉ ባንኩን በዚህ ደረጃ ከተውነው ከፍተኛ የፋይንስ ቀውስ ሊያመጣ የሚችል ነው የነበረው” ብለዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው አክለውም፤ “ይህ የኢኮኖሚ [እና] የፋይናንስ ቀውስ እንዳይፈጠር ለማድረግ እና ባንኩን ጠንካራ መሰረት ላይ ለመጣል ይሄንን እርምጃ መውሰድ አስፈልጓል” ሲሉ የውሳኔውን አመክንዮ አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ፓርላማ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ ንገድ ባንክን ጉዳይ አንስተውት ነበር።

“ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዚህ [የኢኮኖሚ] ሪፎርም በጣም ተጠቃሚ ከሆኑ ተቋማት አንዱ ነው” ያሉት ዐቢይ፤ “በህዳሴ ምክንያት በቦንድ ምክንያት በጣም አስጊ ጉዳይ ውስጥ ከነበሩ ተቋማት አንዱ ንግድ ባንክ ነው” ብለው ነበር።

“ይሄ ሪፎርም ባይሰራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይፈርስ ነበር” ሲሉም ተደምጠዋል።

“ባንኩ ያለበትን ዕዳ በቀላሉ ማኔጅ የሚያደርገው አልነበረም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “በዚህ ሪፎርም 900 ቢሊዮን ብር የተራዘመ ቦንድ አግኝቷል ባንኩ በከፍተኛ ደረጃ የነበረበትን ድርስ [immediate] አደጋ መከላከል የሚያስችል ሀብት አግኝቶ ስራ ጀምሯል” ብለዋል።

መንግሥት የልማት ድርጅቶቹን ዕዳ ለመክፈል መወሰኑ የሚኖረውን እንድምታ በተመለከተ ጥያቄ የቀረባለቸው ዶ/ር እዮብ፤ “ይህ የፊስካል ጫና በመንግስት ላይ ያመጣል ምንም ጥያቄ የለውም “ ሲሉ መልሰዋል።

“የገንዘብ ሚኒስቴር ነው ይህን [ዕዳ} በ10 ዓመት ውስጥ የሚከፍለው” ያሉት ዶ/ር እዮብ፤ “የፊስካል ጫና ይኖረዋል” ብለዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው አክለውም “ግን ይሄ ፊስካል ጫና በዓመታት ተከፋፈለ ስለሆነ [እና] በአጠቃላይ ደግሞ የገቢ አቅማችንን የማሳደግ ሥራ እየሰራን ስለሆነ አጠቃላይ ፊስካል ማዕቀፉን ስናየው የተረጋጋ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ከሚያወጣው የመንግሥት ዕዳ ሰነድ ውስጥ 54 ቢሊዮን ብር የሚሆነው የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ የሚውል ነው።

የአዋጁ ማብራሪያ “መንግሥት ለካፒታል ማሳደጊያ የሚውለውን ሀብት በጥሬ ገንዘብ መልክ ለመመደብ የሚያስችል ሀብት በአሁኑ ጊዜ የሌለው በመሆኑ የካፒታል ማሳደጊያውን በመንግሥት ዕዳ ሰነድ መልክ መክፈል አማራጭ የሌለው ሆኖ ተገኝቷል” ሲል ያትታል።

መንግሥት ይህን ዕዳ ለመክፈያ የሚያውለውን የገንዘብ ምንጭ በተመለከተ ሌላ ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር እዮብ፤ “ከውጭ የሚመጣ ብድር የለም በአገር ውስጥ ካለው ኢኮኖሚ ገቢ ሰብስበን የምክከፍለው ነው የሚሆነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶ/ር አብዱልመናን መንግስት ዕዳውን ለመክፈል ከአገር ውስጥ ኢኮኖሚ ሊሰበስብ ያሰበው ገቢ በኅብረተሰቡ ላይ ጫና እንደሚያሳድር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለሙያው አክለውም “በትንሹ [ዕዳው] ሰባት በመቶ ወለድ ቢኖረው በሦስት ዓመታት ውስጥ 200 ቢሊዮን ብር ይመጣል ወለዱ ብቻ ስለዚህ የእፎይታ ጊዜው ሲጠናቀቅ ዕዳው ከአንድ ትሪሊዮን ብር ያልፋል” ይላሉ።

ክፍያን በተመለከተ በአዋጁ መሰረት የሚወጥት የመንግስት የዕዳ ሰነዶች ከሦስት ዓመታት የችረፎታ ጊዜ በኋላ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍለው እንደሚጠናቀቁ አዋጁ ያትታል።

የገንዘብ ሚኒስትር በሚያወጣው የመንግስት የዕዳ ሰነዶች ላይ የሚከፈለው ወለድ በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በብሔራዊ ባንክ እና በንግድ ባንክ መካከል በሚደረግ ስምምነት እንደሚወሰን አዋጁ ላይ ሰፍሯል።

ዶ/ር አብዱልመናን ከእፎይታ ጊዜው በኋላ የሚኖረውን የአንድ ትሪሊዮን ዕዳ በአስር ዓመት ለመክፈል “በየዓመቱ ከአንድ መቶ ቢሊዮን ብር በላይ ለንግድ ባንክ መክፈል ይኖርበታል የኢትዮጵያ መንግስት” ይላሉ። ዶ/ር አብዱልመናን “ምናልባት ትልቁ የአገሪቱ በጀት ሊሆን ይችላል ይህ ክፍያ” ሲሉ ያክላሉ።

ይህን ዕዳ ከአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ገቢ ለመሰብሰብ መታሰቡን ተከትሎም፤ “ከኢኮኖሚው እንሰበስባለን ማለት ግብር ከኅብረተሰቡ እንሰበስባለን ማለት ነው አሁን ያሉት የታክስ አይነቶች ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ የታክስ ምንጭ ይፈለጋል። መንግስት ይሄን ዕዳ ለመቀነስ [እና] ገቢውን ለመጨመር ሌሎች የታክስ አይነቶችን ሊጥል ይችላል፤ ይሄ ደግሞ የህብረተሰቡን ኑሮ በጣም ከባድ ነው የሚያደርገው” ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተዋል።